Skip to main content

ሐ ገ ር 

ሐገር የእሚለውን ቃል ለአንባቢ ለመተርጎም የእማያስፈልግ እስኪ መስል ድረስ ኹላችንም በእየ እለት የእምንጠቀምበት ቃል ነው ። ቃሉ የእለት ተእለት ምልልሳችን ውስጥ በስፋት የእምንጠቀምበት እና ኹላችንም ሐገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ የእየ ራሳችን ግንዛቤ የአለን ቢሆንም ፤ አንድ ግዜ ግን ፦ ሐገር ምንድ ነው? ብለን የጠየቅን ወይንም ተብለን የተጠየቅን እንደሆን ፤ ሐገር የእሚለው ቃል በእየለት ምልልሳችን ከእምንጠቀምበት በላይ ሰፋ ያለ ኃሳብ ያዘለ መሆኑን እየተረዳነው እንመጣለን ።


ሐገር ምንድ ነው?


አንድ የተከለለ መልከዓ ምድር? በእዚያኽ የተከለለ መልክዓ ምድር ላይ የእሚኖሩት ሕዝብ? በአንድ የተከለለ መልክዓ ምድር ላይ የእሚኖሩ እና የጋራ መንግሥት የአላቸው ሕዝብ?


በአንድ የተከለለ መልክዓ ምድር ላይ የእሚኖሩ እና የጋራ መንግሥት የአላቸው ሕዝብ ከሆነ ሐገር ፥ ምን ዓይነቱ መንግሥት ነው ሐገርን ሐገር የእሚያስብለው? ኹሉም ዓይነት መንግሥት?


በእየ እለት የእምንጠቀምበት እና ምንም ትርጓሜ የእሚያስፈልገው የእማይመስለው ሐገር የእሚለው ቃል ፤ በእነ እዚኽ እና መሰል ጥያቄዎች አውድ ስናስበው ፤ ቃሉ ምንም እጅግ የተለመደ እና ትርጓሜውም ከሞላ ጎደል ለአብዛኛዎቻችን ግልፅ የሆነ ቢመስልም ፤ በተለይ የተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮቶች ሐገርን በእየራሳቸው መንግድ ለመተርጎም የእሚያደርጉት እሽቅድድም ስንአክልበት ፤ ልማዳዊውን የሐገር ትርጓሜ ወይንም ግንዛቤ በእሚያጠራ እና በእሚያጠናክር ትርጉም ፤ በሐገር ላይ የእሚደረግን ውይይት መጀመር ተገቢ ይመስላል ። ይኽም በመሆኑ ይኽንን መጽሐፍ ሐገር የእሚለውን ቃል በመተርጎም እንጀምራለን ።


ሐገር ማለት ፦ በአንድ በተከለለ አከባቢ የእሚኖሩ ፤ የራሳቸው መንግሥት የአላቸው እና መንግሥታቸው ፥ ሐገራዊ ድንበራቸው እና አንድ የጋራ ሕዝብነታቸው ዓለም ዓቀፋዊ እውቅና የአላቸው ሕዝብ ናቸው ።

ይኽን ትርጉም እንደ መነሻ ወስደን ስንነሳ ፤ ሐገር ቁሳዊ እና መዋቅራዊ (ኃሳባዊ ፣ መንፈሳዊ ወይንም ምናባዊ) አካል ወይንም ክፍል እንደ አላት እንገነዘባለን ።

ሠንጠረዥ  1፡ አካላዊ እና ወዋቅራዊ/ኃሳባዊ የሐገር ክፍላት።


ቁሳዊው የሐገር ክፍል ፦ በአንድ በእሚታወቅ እና በተከለለ አከባቢ የእሚኖሩ ሕዝብ ፣  መኖሪያቸውን ስፍራ እና መንግሥታቸውን የእሚያካትተው ነው ። በእዚኽም መሠረት ፤ ቁሳዊው የሐገር ትርጉም ፦ የጋራ መንግሥት ኖሯቸው ፤ በአንድ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በእሚታወቅ እና በተከለለ አከባቢ የእሚኖሩ ሕዝብ ናቸው ፤ የእሚለው ነው የእሚሆነው ።


ወደ መዋቅራዊው (ኃሳባዊ ፣ መንፈሳዊ ወይንም ምናባዊ) የሐገር ክፍል ስንመጣ ፤ መዋቅራዊ የሐገር ክፍል የእሚገለፅበት አግባብ ወይንም መዋቅራዊ የኾነው የሐገር ትርጉም ፤ በፖለቲካዊ አስተሳሰብ ወይንም አመክንዮ አውድ የተወሰነ በመሆኑ እንደ አካላዊ ትርጉሙ አንድ የጋራ ትርጉም ማስቀመጥ የእሚቻልበት አይደለም ።


በመዋቅሩ ረገድ ፦ ለአንዳንዱ ሐገር ማለት እገሌ የእሚባሉት ዘሮች የእሚኖሩበት ነው ፣ ለሌላኛው እገሌ የእሚባሉት ነገዶች የእሚኖሩበት ነው ፣ ለሌላኛው ሐገር ማለት በሶሻሊስታዊ መርሕ የእሚመራ መንግሥት የአለባት ነች እንደገና ለሌላው የነዋሪዎቹ የዘር እና የነገድ ማንነት ሰአይሆን የእሚከተሉት ኃይማኖት ከአንዱ ወገን የመሆኑ ጉዳይ ነው ሐገሩን ሐገር የእሚያስብለው ።


በአጭሩ ፤ የሐገር ምናባዊ መዋቅር ትርጉም ፤ ሰዎች በእሚከተሉዋቸው የፖለቲካ ርዕዮት የእሚወሰን ነው ። እነ እዚኽን ሐገርን በተለያየ መልኩ የእሚተረጉሙ ርዕዮቶችን ለመረዳት ፤ ርዕዮቶችን በኹለት ዋነኛ ጎራዎች ከፍሎ መጀመር ይቻላል ።


በእዚኽ መሠረት ፤ በጠቅላላ ክፍፍል (General Classification) የፖለቲካ ርዕዮቶችን ዴሞክራሲያዊ እና ፅንፈኛ ብለን ለኹለት ልንከፍላቸው እንችላለን ።


ዴሞክራሲያዊያን የእምንላቸው ፤ የሐገር ስለ እዚኽም አንዲት ሐገር የእሚኖራት የፖለቲካ ስረዓት ፤ የመጨረሻው ግብ ፦ ለማሕበራዊ እድገት መሠረት የሆኑትን ዜጎችን ፤ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የእሚያከበር እና የእሚያስከበር መንግሥት የአለባት መኖሪያቸው ነች ብለው የእሚያምኑትን ነው ።


ፅንፈኞች የእምንላቸው ደግሞ ፤ የሐገር ስለ እዚኽም አንዲት ሐገር የእሚኖራት የፖለቲካ ስረዓት ፤ የመጨረሻ ግብ ፦ ለማሕበራዊ እድገት መሠረት የሆኑትን ዜጎችን ፤ የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ከማክበር እና ከማስከበር በፊት   ፦


              • ፖለቲካዊ ርዕዮት ( ሶሻሊዝም ፣ ፋሺዝም … )
              • ኃይማኖታዊ
              • የማንነት
              • የጥንታዊ ባህል እና ልማድ ፣ ወዘተ


ሕልውና የማክበር እና የማስከበር ሥራ የእሚሰራ መንግሥት የአለባት የሕዝብ መኖሪያ ነች የእሚሉትን ነው።

እንደ እምንመለከተው ፅንፈኛ የአልናቸው ፖለቲካዊ ርዕዮቶች ፤ የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ማክበር እና ማስከበር የእሚለውን ኃሳብ ፤ እንደ ኹለተኛ ወይንም ዝቅተኛ ግብ ማየታቸው ሲያመሳስላቸው ፤ በርዕዮታቸው መሠረት የእሚቋቋመው መንግሥት ቀዳሚ ግብ ምን መሆን አለበት በእሚለው ላይ የተለያዩ ናቸው ። ለአንዳንዶቹ የሊቀመንበር ማዖ ፍልስፍና ዋነኛው እና ቀዳሚው ነው ፣ ለሌላኛዎቹ ‘አንዲቷ እና እውነተኛዋ’ ኃይማኖት ቀዳሚ ነች ፣ እንደገና ለአንዳንዶቹ ከአያት ቅድመ አያቶቻቸው የመጣው ጥንታዊ ባሕላቸው ቀዳሚ ነው ።


ርዕዮቶችን ዴሞክሪሲያዊ እና ፅንፈኛ ርዕዮቶች በእሚል በእዚኽ መልኩ ከከፋፈልን ፤ የርዕዮቶቹን አራማጆች ወይንም ፖለቲከኞቹን ፤ ዴሞክራሲያዊነትን ይዘው የእሚታገሉትን አርበኞች ከዴሞክራሲ ውጭ የአለውን ሌላ ማንኛውም ርዕዮት ይዘው የእሚታገሉትን ፅንፈኞች ብለን እንከፍላቸዋለን ።


በእርግጥ ፤ በጣም በተወሰነ የስነ ልቦና መቃወስ ምክንያት የፖለቲካ ኃይላት ፅንፈኝነትን መርጠውት ሊይዙ የእሚችሉበት ወቅት ቢኖርም ፤ ፅንፈኞች ራሳቸውን እንደ ጽንፈኛ ሰአይሆን የእሚገነዘቡት ፤ ለሐገራቸው ፣ ለኃይማኖታቸው ፣ ለባህላቸው ፣ ወዘተ ፤ ክብር በቆራጥነት እንደ እሚታገሉ ወይንም አርበኛ እንደ ሆኑ አድርገው ነው ።


ሆኖም ግን ፤ ምንም እንኳን ፅንፈኞች እና አርበኞች ፤ የከበረ ለእሚሉት ዓላማ ራሳቸውን እና ማንኛውንም ሰውም ሆነ ቁስ መስዕዋት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸው ቢያመሳስላቸውም ፤ የአርበኞች ትግል ማዕከሉ የሰውን ህይወት እና ንብረት ከኢፍትኃዊ ጥቃት መከላከል የእሚለው ዓላማ ሲሆን ለፅንፈኞች ደግሞ የሰውን ህይወት እና ንብረት ከኢፍትኃዊ ጥቃት መከላከል ከእሚል የተለየ ኃይማኖታዊ ፣ ብሔራዊ ፣ ርዕዮታዊ ፣ ወዘተ ፤ ዓለማ የትግሉ ማዕከል የሆነ በመሆኑ ፤ በመኻከላቸው ትልቅ ልዩነት አለ ።


አርበኞች ፤  ከሰው ተፈጥሮ የእሚመነጩ ወይንም ለሰዎች ተፈጥሮ ያጎናፀፈቻቸውን ፤ ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ መብቶቻቸውን ፤ ተወስዶባቸው ከሆነ ለማስመለስ ይዘውትም ከሆነ ከጥቃት ለመከላከል የእሚታገሉ ናቸው ።

ስለ እዚኽም አርበኝነት ፦ ታሪካዊ መኖሪያ ስፍራህን ልቀቅ ፣ ያፈራኸው ኃብት የአንተ አይደለም የእሚልህን ወይንም ኃብት ማፍራት አትችልም የእሚልህን ፣ ኃሳብህን መግለፅ የእምትችለው እኔ ስፈቅድልህ ነው ወይንም ኃሳብህን ስለ ገለፅኽ እቀጣኃለሁ ፣ ወዘተ ፤ የእሚልን አጉራ ዘለል እምቢ የእሚል ትግል ማድረግ ነው ።


በተቃራኒው ፥ ፅንፈኞች ከሰው በላይ የከበረ ነው ብለው የእሚያምኑትን ፤ አንድ የሆነ ፦ ፖለቲካዊ ፣ ኃይማኖታዊ ፣ ባህላዊ ፣ ወዘተ ፤ ርዕዮት (ideology) ፤ ለማስከበር ወይንም በኃይል ለማስፋፋት የእሚታገሉ ናቸው ።  


ለፅንፈኛው ፤ ‘ቅዱስ’ የእሚባለው ዓላማ ፤ የሰዎችን የመኖር እና አለመኖር መብትን ፣ ንብረት የማፍራት እና ያለ ማፍራት መብትን ፣ የመናገር እና የአለመናገር መብትን ፣ ወዘተ ፤ የእሚወስነው እርሱ ስለ ሆነ ፤ ያንን ‘ቅዱስ’ ዓላማ እስከ አሳካ ድረስ የዜጎችን ፦ በህይወት የመኖር መብት ፣ በነጻነት የመንቀሳቀስ ፣ ኃሳብን የመግለጽ ፣ የወደዱትን የመልበስ ፣ ንብረት የማፈራት መብት ፣ ወዘተ ፤ በአጠቃላይ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብቶች ፤  መከልከል ከአለበት ይከለክላል ።


በሌላ አገላለጽ ፅንፈኝነት ፦ ከዜጎች ተፈጥሮዋዊ ፣ ሰብአዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ተጠቃሚነት በአሻገር ላሉ ፦ ኃይማኖታዊ ፣ ነገዳዊ ፣ ፖለቲካዊ ፣ ወዘተ ፤ ‘ቅዱስ’ ኃሳቦች ልዕልና በውድም በግድም ለማስቀጠል የእሚደረግ ተጋድሎ ሲሆን ፤ አርበኝነት ግን የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ መብቶችን ለማስከበር እና ከጥቃት ለመከላከል የእሚደረግ ትግል ነው ።


በእዚኽም ሐገር በእሚለው ምዕራፍ ፤ የሐገር ኃሳባዊ አካል የሆነውን ፤ እነ እዚኽ አርበኞች እና ፅንፈኞች የእሚከተሉዋቸውን እንዲኹም እንደ ርዕዮቶቻቸው ሐገር ምንድነች የእሚሉበትን አግባብ በዝርዝር የእምናይበት ነው ።