
የዴሞክራሲ ፅንሰ ኃሳብ ምን አልባት በብዙ ሰዎች ዘንድ ፤ ዴሞክራሲ ሲባል መጀመሪያ ወደ ዓይነ ህሊናቸው ከእሚመጣው ኃሳብ በላይ የጠለቀ ቁም ነገር ያነገበ ይመስላል ።
ዴሞክራሲ ምንድን ነው ?
በተሟላ ኹኔታ ዴሞክራሲን ለመተርጎም ፤ እነዚኽን እና መሰል ጥያቄዎች ይዘን ፤ ዴሞክራሲን ከልማዳዊው ግንዝቤው በአለፈ ፤ ጠለቅ በአለ እና በተሻለ ኹኔታ ለመተርጎም ወይንም አካታች እና ገላጭ የሆነ ፤ የዴሞክራሲን ትርጉም ለማስቀመጥ ፤ የጥያቄያችንን አውድ ቀይረን ፤ የእሚከተሉትን ሦሥት ጥያቄዎች ጠይቆ መመለስ ፤ የተሻለ ኹኔታ ይፈጥርልናል ብዬ አስባለኹ ፦
የእሚታወቀው ዴሞክራሲ የእሚለው የግሪክ ቃል ትርጉም እንደ እሚነግረን ፤ ዴሞክራሲ ፦ “ዴሞ” እና “ክራሲያ” ከእሚሉ ኹለት የግሪክ ቃላት ውህደት የተፈጠረ ቃል እንደ ሆነ እና ቃላቱም ፤ በቅደም ተከተል ፦ ሕዝብ ወይንም መንደር እና አመራር ወይንም አገዛዝ የእሚል ትርጉም የአላቸው እንደ ሆኑ ፤ በእዚኽም መሠረት ፥ ዴሞክራሲ ማለት ፦ የሕዝብ ገዢነት ፣ የሕዝብ መሪነት ወይንም ሕዝባዊ መንግሥት የእሚል ትርጓሜ እንደ አለው ነው ።
ዴሞክራሲም ፤ በተመዘገበ ታሪክ ፡ እንደ ፖለቲካዊ ስረዓት የተዋወቀው እና የሕዝብ መንግሥት መመሥረቻ የሆነው ከዛሬ 2,500 ዓመታት ገደማ ቀደም ብሎ ፤ በግሪኳ የአቴንስ ግዛት ሲሆን ፤ ይኽንንም አሰራር ያመጣው ፤ ክሌስቴነስ የተባለ ከአቴንስ መኳንንት አንዱ የኾነ ሰው ነው ።
ክሌስተነስ ዴሞክራሲን ያመጣበትም ምክንያት ፦ በአቴንስ ፤ ከክርስቶስ ልደት 500 ዓመት ገደማ ቀደም ብሎ ፤ በተለያዩ የመኳንንት ቤተሰቦች መካከል የእሚደረገው የስልጣን ሽኩቻ ፤ በከተማቸው ውስጥ የሴራ እና የአመፅ ፖለቲካን በማፋፋም ፤ በጋራ በሰላም የመኖራቸውን ኹኔታ ፤ ማብቂያ የሌለው የደህንነት ስጋት ውስጥ ስለ ጨመረው ፤ የፖለቲካ ስልጣን የእሚያዝበትን መንገድ ማሻሻል ወይንም ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ፤ የሰላማቸው ጠንቅ የሆነውን የሴራ እና የአመፅ ፖለቲካ እንዲያስቀር በማሰብ ነው ተብሎ ይታመናል ።
በእዚኽም ፥ ስልጣን ፤ ጥቂት የመኳንንት ዘሮች የእሚኖራቸው ልዩ መብት ሰአይሆን ፤ የሕዝብ እንዲ ሆን እና ሕዝቡ ወይንም የአቴንስ ነዋሪ ፤ በአቴንስ ጉዳይ በቀጥታ እየተሰበሰበ ፤ የተለያዩ ከሚቲዎችን ከማዋቀር አንስቶ ፣ የጦር ጀነራሎችን መሾም ፣ የበጀት መጠን መወሰን ፣ ወዘተ ፤ መሰል በአጠቃላይ የጋራ ጉዳያቸውን በሙሉ በጋራ የእሚወስኑበት አካኼድን አስተዋወቀ ።
አዲሱ የክሌስተነስ ዴሞክራሲም ፤ በአቴንስ እየጎለበተ ኼዶ ፤ በአቴንስ ዴሞክራሲ ወይንም ሕዝባዊ መንግሥት ውስጥ በቀጥታ ለመሳተፍ እምቢ ወይንም ችላ የእሚለው ሰው ፤ ግለኛው ወይንም ብቸኛው እየተባለ ለዛሬው የእንግሊዘኛ ቋንቋ idiot ለእሚለው እና መኃይም ወይንም አላዋቂ የእሚል ትርጉም ለአለው ቃል መሠረት በሆነው idios በእሚለው የግሪክ ቃል እንዲ ሰየም የአደረገ ጉልህ ማሕበራዊ ክስተት እስከ መሆን ደረሰ ።
ምንም እንኳን ፤ የአቴንስው ክሌስተኒስ ዴሞክራሲ ፤ ዛሬ በዓለም ላይ በክብር ለናኘው ዴሞክራሲ ለእሚለው ቃል ምንጭ እና የፅንሰ ኃሳቡም መሠረት ቢሆንም ፤ የእዚያኽን ወቅት የአቴንስ ዴሞክራሲ ፤ በእዚኽ ዘመን ቢመጣ ፤ አግላይ ፣ ኋላ ቀር ፣ ለትግበራ አስቸጋሪ እና አሳሪ ተብሎ የእሚወቀስ መሆኑ ግን የእማያጠያይቅ ነው ።
ለምሳሌ ፦ ምንም እንኳን የአቴንስ ዴሞክራሲ ፤ የአቴንስ ነዎሪዎችን በቀጥታ አሳታፊ ነው ቢባልም ፤ የነዋሪዎች ተሳትፎ ፦ በንብረታቸው መጠን ፣ በፆታቸው ዓይነት ፣ ባሪያ እና ነፃ በመሆናቸው ፤ የተወሰነ ነበር ።
በእዚኽም መሠረት ፤ ንብረት የሌላቸው ነዋሪዎች ፣ ሴቶች እና ባሪያ የሆኑ ሰዎች ፣ በዴሞክራሲው እንዲሳተፉ አይፈቅድም ። ይኽ ማለት ደግሞ ፤ በአቴንስ ዴሞክራሲ ዜጎች በሰብዓዊነታቸው የእማይከበሩበት ፤ ስለ እዚኽ ፦ ሴቶች እና ወንዶች የእኩል ዴሞክራሲያዊ መብት ባለቤት መሆናቸውን የእማይቀበል ፣ ሰዎችን እንደ እቃ መግዛትን እና መሸጥን እውቅና የእሚሰጥ ፣ የነዋሪዎችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ በንብረታቸው መጠን የእሚገድብ ፤ ኢሰብዓዊ ዴሞክራሲ ወይንም የሕዝብ ገዢነት/አምባገነንነት ወይንም ሕዝባዊ ነገር ግን ነጻነት የሌለበት መንግሥት ነበር ።
ከእዚኽም በአሻገር ፤ የአቴንስ ዴሞክራሲ ፤ ቀጥታ የእሚባለው ዴሞክራሲ በመሆኑ ፤ በውልደቱ አቴናዊ የሆነ (ባሪያ የአልሆነ)ወንድ እና የራሱ ንብረት የአለው ማንኛውም ሰው የእሚሳተፍበት ጉባኤ ስለ አላቸው ፤ ይኽ ጉባኤ ወደ መንጋነት በተደጋጋሚ ይቀየር ነበር ።
ለምሳሌ ፦ በወቅቱ በነበራቸው ልምድ ፤ ሰውን ንብረቱን ቀምቶ ከሐገር ማባረር አንድ የቅጣት ዓይነታቸው የነበረ ሲሆን ፤ በእዚኽም መሠረት አንድ ጉባኤተኛ እጁን አውጥቶ ፤ በቅናት ይኹን በግብታዊነት ፡ እገሌ የእሚባል ሰው ከአቴንስ ይባረር ብሎ የውሳኔ ኃሳብ አቅርቦ ጉባኤው በኃሳቡ ተስማምቶ ከወሰነ ፤ ለተባራሪው ሰው ምንም ሕጋዊ የመብት ከለላ ሳይደረግ ፤ ማለትም ፦ ለእዚኽ የመባረር ቅጣት የእሚያበቃው ወንጀል ወይንም ጥፋት ሳይገኝበትም ጭምር ፤ በቅናት ፤ በጥላቻ ወይንም በበቀል በተነሳሱ ሰዎች ግፊት ፤ ሰውየውን ንብረቱን ቀምተው ከሐገር ሊያባሩት ይችላሉ ።
ታዋቂውን ፈላስፋ ሶቅራጠስን ፤ ወጣቶችን ኃይማኖት አስካድኽ በእሚል የሐሰት ክስ ፤ የሞት ፍርድ የፈረደበት ይኽ ዓይነቱ የአቴንስ ዴሞክራሲ ነው ። ይኽ ዓይነቱ የክልስተነየስ ዴሞክራሲ ያስቆጣው ፕሌቶ ፤ ስለ ዲሞክራሲ ሲጽፍ ፤ መንጋ አምባገነን የእሚሆንበት ስረዓት መሆኑ የዴሞክራሲ አንዱ ችግር ነው የአለውም ፤ የወቅቱ የአቴንስ ዴሞክራሲ አስተማሪውን ሶቅራጠስን የአል አግባብ የሞት ፍርድ ያስፈረደበት የዴሞክራሲ መዋቅራዊ ስህተት ነው ብሎ ስለ እሚያምን ነው ።
እንዲኽ እንዲኽ እያልን እንግዲኽ ፤ ቀዳሚውን የአቴንሱን ዴሞክራሲ ችግሮች በመዘርዘር ፤ ከአኹኑ ዘመን የዴሞክራሲ ፅንሰ-ኃሳብ ጋር ሲነጻጸር ቀዳሚው የአቴንስ ዴሞክራሲ ፤ ኢሰብዓዊ የመንጋ አምባገነንነት እንጂ በዘመናዊ መመዘኛ ዴሞክራሲ ተብሎ ሊጠራ አይገባም የእሚያስብሉትን ብዙ ችግሮች መዘረዘር እንችላለን ።
ስለ እዚኽም ፦ በክለስቴኒየስ አመንጪነት ፤ ዴሞክራሲያዊ ስረዓትን በተመለከተ ፤ አቴንስ ለዓለም ያበረከተችው ዋናው ቁምነገር (የእሚጣለው ተጥሎ) ፤ ለዛሬው ማሕበረሰባዊ እድገታችን የእሚመጥነው ፤ የመጀመሪያው የዴሞክራሲ ፅንሰ-ኃሳብ ፤ የፖለቲካ ስልጣን የሕዝብ ነው የእሚለው እና ሕዝብም ይኹንታውን ወይንም አይኹንታውን በግልፅ ምርጫ ያስታውቃል የእሚለው ፤ ግርድፍ ነገር ግን ትልቅ ቁም ነገር የጨበጠ ኃሳብ ነው ።
ከእዛያኽ በተረፈ ግን ዘመናዊ ዴሞክራሲን ፦
መርሆች ውጭ ማሰብ አይቻልም ። ይኽም በመሆኑ ፤ ዘመናዊው ዴሞክራሲ የክሌስተነስን ዴሞክራሲ በበጎ መልኩ በብዙ አሻሽሎታል ።
በፅንሰ-ኃሳብ ደረጃ ፤ በዘመናዊ ዴሞክራሲያዊ ሐገራት ፤ ከሕግ አግባብ ውጪ ፤ የአንድን ዜጋ ህይወት ወይንም ንብረት በ99.9% የሐገሬው ሰው ድጋፍ እንኳን ፤ ያለ ሕግ አግባብ መቀማት ወይንም መውረስ አይቻልም ።
ይኽም በመሆኑ ፤ በዘመናዊው ዴሞክራሲ የድምፅ ብልጫ ፤ ከሕግ አግባብ ውጭ የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት መሻር አይችልም ፤ ስለ እዚኽ ፦ በዘመናዊ ዴሞክራሲ የሕዝብ ምርጫ ለሕግ የበላይነት የተገዛበት ዴሞክራሲ ነው ፤ በፅንሰ-ኃሳብ ደረጃ ።
በዘመናዊ ዴሞክራሲ ፤ አንድ ግለሰብ ወይንም አንድ ማሕበር ፡ ሕግ አውጪ ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ሕግ ተርጓሚ ራሱ መሆን የእማይችልበት ነው ። ያም ማለት የፖለቲካ ስልጣን ፤ በሕዝብ ምርጫ የእሚገኝ ቢሆንም ፤ ቡድናዊም ሆነ ግለሰባዊ አምባገነንነትን እንዲ ከላከል እና የማስፈፀም አቅምን እንዲ ጨምር ሆኖ ፤ የፖለቲካ ስልጣን ሳይማከል ተከፋፍሎ እና እርስ በእርሱ ተያይዞ ፥ እርሱ በእርሱ አንዱ አካል ሌላው ላይ እንዲ ደገፍ እንዲኹም እርስ በእርሱ እንዲ ቆጣጠር ሆኖ የተዋቀረ ነው ።
ከእዛኽ በአሻገር ፤ ሐገራት ሳይሆኑ ከተሞች እንኳን በሚሊዮን የእሚቆጠሩ ሰዎች በእሚይዙበት በእዚኽ ዘመን ፤ የተወካይን ሰአይሆን የቀጥታ ዴሞክራሲ በሥራ ላይ እናውል ቢባል ፤ በመቶ ሺዎች እና በሚሊዮን የእሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ቀጥታ እየተወያያችሁ ፤ ሕግ አፅድቁ ፣ ሹመት አፅድቁ ፣ ምርመራ አካኺዱ ፣ ከሚቲ አቋቁሙ ፣ ወዘተ ፤ ቢባል ፤ ከአስተዳደር ፣ ከብቃት እና ከቅልጥፍና አንፃር ሊተገበር የእማይችል አክሳሪ አካኼድ እንደ እሚሆን ግልፅ ነው ።
ከእዚኽም የተነሳ ፤ በክሌስተነስ ዴሞክራሲ ላይ ፤ ከላይ የዘረዘርናቸውን ዘመናዊ የፖለቲካዊ ሳይንስ እውቀት የጨመራቸውን አዳዲስ ማሻሻያ እና ማጠናከሪያ ኃሳቦች ያካታተው ዴሞክራሲ ፤ በእንግሊዘኛው Liberal Democracy የእሚባለው ወይንም የነጻነት ዴሞክራሲ ነው ።
ይኽም ፤ የነፃነት (Liberal) የእሚለው ገላጭ መለያ (Qualification) የአስፈለገበት ምክንያት ፤ ዴሞክራሲ በነጻነት ሕግ ከአልተገደበ ወይንም በግለሰቦች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት መዓከልነት ከአልተገነባ ፤ ወደ መንጋ አምባገነንነት በቀላሉ የእሚለወጥ እና ከሌሎቹ ፦ እንደ ዘውድ እና የመኳንንት ከአሉ ፖለቲካው ስረዓቶች በላይ የከፋ አውሬ ስረዓት ሊሆን የእሚችል በመሆኑ ነው ።
በግለሰቦች ሰብዓዊ መብት መዓከላዊነት ያልተገነባ ዴሞክራሲ ወይንም የነጻነት ዴሞክራሲ (Liberal Democracy) ያልሆነ ዴሞክራሲ ፤ ጥቂት የተደራጁ ኃይላት ወይንም የመንጋ አስተሳሰብ ፤ ሐገርን እና ሕዝብን ወደ ፈለጉበት ግብታዊ ዓላማዎች መምራት የእሚችሉበት ፤ እጅግ ጋጠወጥ ስረዓት የመፍጠር አቅም የአለው ነው ።
ለእዚኽም ነው ፤ ነባራዊው እና የመጀመሪያው የአቴናው ቀጥተኛ ዴሞክራሲ ፤ ምንም እንኳን ዘመን ተሻጋሪውን የሕዝባዊ መንግሥት ፅንሰ-ኃሳብ ቢያስተዋውቅም ፤ ያልዳበረ መፍትሔ በመሆኑ ፤ በክሌስተነስ የተጀመረበትን የመጀመሪያውንም ግቡን ማሳካት ሳይችል ቀርቶ ፤ ዴሞክራሲ በአውሮፓ ህዳሴ ትንሳኤ እስኪ ያገኝ ለ 2,000 ዓመታት ገደማ ተዘግቶ የቆየ የስነ መንግሥት ፅንሰ ኃሳብ የሆነው ።
የአቴንስ ዴሞክራሲ ፤ የነጻነት ስለ አልሆነ ወይንም የዛሬው ዘመን ዴሞክራሲያዊ መንግሥትን ያስቻሉትን ማዳበሪያ ኃሳቦች ስለ አል አካተተ ወይንም liberal democracy ስለ አልነበረ ፤ ዴሞክራሲው እጅግ በረብሻ የተሞላ ፣ የተጠላው የሴራ እና የስልጣን እሽቅድድም መልኩን ቀይሮ በመምጣት ግጭትን ያበራከተበት ፤ በአጠቃላይ ይፈታዋል ተብሎ ታሶቦ የተፈጠረውንም ችግር መፍታት ያልቻለ እና በራሱ የማሕበራዊ ቀውስ ምክንያት የሆነ ነበር ።
ዛሬ ላይ ፤ ከዴሞክራሲያዊ መንግሥታዊ አወቃቀር የተሻለ አካኼድ የለም ብለን የእምናምን ሰዎች ፤ የክሌስተነስ ዴሞክራሲ ችግር ፤ የዴሞክራሲ ፅንሰ-ኃሳባዊ ችግር ሰአይሆን ፤ ፅንሰ-ኃሳቡ ፤ ትክክለኛ ሆኖ ሳለ በሳይንሳዊ መልኩ ያለ መዳበሩ ችግር እንደ ነበር እንረዳለን ።
ከእዚኽም የተነሳ ፤ ዴሞክራሲ በጣም ጥንታዊ ከእሚባሉት የመንግሥት አወቃቀር መላምቶች መካከል አንዱ ቢሆንም በተጓዳኝነት ከእሚያመጣቸው ችግሮች የተነሳ ፤ በአውሮፓ ሕዳሴ ማግስት ትንሳኤ አግኝቶ ዛሬ የደረሰበት ገናናነት ላይ እስኪ ደርስ ወይንም የሰው ልጅ ከክሌስተነስ ጀምሮ ዴሞክራሲን በሕዳሴው የሳይንስ አብዮት በተለያየ መንገድ አዳብሮ የማሕበራዊ ቀውስ መፍትኼ ወይንም ማሳደቢያ እስኪ ያደርገው ተዳፍኖ የቆየ መንግሥታዊ አወቃቀር ቀመር ነበር።
መልካም ጅማሮ የነበረው የክሌስተነስ ዴሞክራሲ ፤ በእዚኽ መልኩ ለረዥም ዘመን ተዳፍኖ እንዲቆይ ከአደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ ፤ ከጥንታዊው ፕሌቶ እስከ መካከለኛው ዘመን ሮበርት ፊልመር እና ሌሎች ስመ ጥር የፖለቲካ ሳይንቲስቶች ፤ ይኽን የክሌስተነስ ዴሞክራሲ የነበረበትን የአመክንዮ እና የአውቃቀር ክፍተት መሙላት ይቻላል እና መሙላቱስ ይጠቅማል የእሚለውን ሰአይሆን ፤ የክሌስተነስ ዴሞክራሲ በነበረበት አፍላ ደረጃ የነበረበትን ችግር በመተችት እና በማጣጣል ላይ በማተኮራቸው ነው።
ዴሞክራሲ ከእዚኽ መሰል የቀደመው ዓለም ስረዓት አልበኝነትን እና መሰል ጎጂ ማሕበራዊ ቀውሶችን ያስከትላል በእሚል ከተዳፈነበት አሉታዊ ፍረጃ መውጣት የጀመረውም ፤ በ13ኛው ምዕተ ዓመት ፤ በቤተ ክህነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ እየገነነ የመጣው የሰው ተፈጥሮዋዊ እኩልነት አስተሳሰብ አነቃቅቶዋቸው ፤ የእንግሊዝ መኳንንቶች ፦ ድንገተኛ ግብር የእሚጥልባቸውን ፣ ምክንያቱን ሳያውቁ የእሚያሥራቸውን ፣ ወዘተ ፤ ፍፁማዊው የንጉሳቸውን ስልጣን ላይ ነፍጥ ማንሳት በመጀመራቸው ነው።
የክሌስተነስ ዴሞክራሲ በነበረበት አፍላ ደረጃ የነበረበትን ችግር በመተችት እና በማጣጣል ዳግም እስከ አንሰራራበት የ13ኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ተዳፍኖ እንዲቆይ በእየ ዘመኑ የነበሩ የተለያዩ የፖለቲካ ሊህቃን ጸረ ዴሞክራሲ ትችት ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
በእዚኽ ረገድ ራሱን የዴሞክራሲ ኃያሲ በማድረግ ቀዳሚው ሊህቅ ፕሌቶ ነበር ብእንል ብዙም አንሳሳትም ።
እንደ እሚታወቀው ፤ የግሪኮቹን ፕሌቶ እና አርስታትል ያኽል ፤ በትኩረት እና በስፋት ፖለቲካን ያጠና ጥንታዊ ፈላስፋ የለም ። በእዚኽ ረገድ የእሚስተካከላቸው በአለ መኖሩ ፤ የፖለቲካዊ ፍልስፍና ‘አባቶች’ ሊባሉ ይችላሉ ።
በፕሌቶ የተጻፈው ‘ሪፐብሊክ’ ተብሎ የተተሮገመው እና በአርስታትል የተጻፈው ‘ፖለቲካ’ የእሚሉት መጽሐፍት ፤ በፖለቲካዊ ፍልስፍና አጥኚዎች ፣ በፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪዎች ፣ በስነ ምግባር ሳይንስ ተመራማሪዎች ፣ ወዘተ ፤ እስከ ዛሬ ድረስ በዓለማችን ትልልቅ ዩንቨርስቲዎች በስፋት ይጠናሉ ።
እነ እዚኽ መጽሐፍት እንደ ፋና ወጊነታቸው ፤ በጣም ብዙ የእሚያስተምሩን ቁምነገር ቢኖራቸውም ፤ አንዳንድ ሰዎች እንደ እሚመስላቸው ፤ እንከን የለሽ የፖለቲካ ኃሳብ የተንፀባረቀባቸው መጽሐፍት ግን አይደሉም ።
እንዲያውም በውስጣቸው ብዙ ኋላ ቀር እና ጎጂ ኃሳቦች ይዘው ይገኛሉ ። ከእዚኽም የተነሳ ፤ መጽሐፍቱ ብዙ የእሚያስገርም እውቀት የያዙ እና ብዙ የእሚያስተምሩት ነገር ቢኖርም ፤ ማንኛውም የእነ እዚኽ መጽሐፍት አንባቢ ፤ እንደ መለኮታዊ ቃል ፤ እንከን የሌለባቸው ናቸው ብሎ እንደ ወረደ ሊቀበላቸው አይገባም ። ግዜ የእማይሽራቸው እና ድንቅ ኃሳብ የያዙትን ያኽል ፤ ምንም ተቀባይነት የሌላቸው ደካማ ኃሳቦችንም ይዘው ይገኛሉ ።
በፕሌቶ እና በኋላም አርስታትል ፤ ፍፁም (Utopian) እና እንከን የለሽ ዓይነት መንግሥት ብለው ፤ ያስቀመጡትን የማሕበረሰብ እና መንግሥት አወቃቀር ምክር በመከተል ፤ አንድ ማሕበረሰብ በእዚኽም ዘመን ይኹን ከእዚኽ በፊትም በነበረው ዘመን ማሕበረሰቡን ወይንም መንግሥቱን በእዚያኽ አግባብ ላዋቅር ቢል ፤ ‘ጭራቅ’ (Monstrous) የሆነ ማሕበረሰብ ወይንም መንግሥት ነው የእሚያዋቅረው ።
ለምሳሌ ፦ ፕሌቶ ሪፐብሊክ በእሚለው መጽሐፉ ፤ ሐገርን የእሚመሩ ወይንም የፖለቲካ ስልጣንን የእሚጨብጡ ሰዎች ፤ ከሕብረተሰቡ መካከል ተመርጠው ይውጡና ፤ እንደ ማደጎ ልጅ በመንግሥት በጀት የእሚያድጉ እና የእሚኖሩ ይኹኑ ይላል ።
እነ እዚኽ የማደጎ ልጆችም ፤ ኹሉን ነገር በጋራ ይጠቀሙ ፤ ሴቶቹ የኹሉም ሚስት ይኹኑ ፤ የእሚወለዱት ልጆች አባት እና እናታቸው አይታወቅ ፣ ወዘተ ፤ እያለ ፤ የአንድ ሐገር የፖለቲካ መሪዎች የእኔ የእሚሉት ነገር ሳይኖራቸው በጋራ ኖረው በጋራ ለመሞት እንዲዘጋጁ ይኽን ማደረግ አለብን ብሎ ይመክራል ፦
“ያልኹት ፥ ከእዚኽ ቀደመም ከአኹን ቀደምም የአለውን ተከትሎ የእሚመጣው ሕግ ፤ የእሚከተለውን ዓይነት ነው ፤ ‘ሞግዚቶቻችን’ ሚስቶቻቸው እና ልጆቻቸው የጋራ ሊሆኑ ይገባል ፥ የትኛውም ቤተሰብ የእርሱ ልጅ የቱ እንደ ሆነ ማወቅ የለበትም ፥ የትኛውም ልጅ የእርሱ ቤተሰቡ የቱ እንደ ሆነ ማወቅ የለበትም ። “
“The law, I said, which is the sequel of this and of all that has preceded, is to the following effect,–’that the wives of our guardians are to be common, and their children are to be common, and no parent is to know his own child, nor any child his parent.” [22]
ፕሌቶ በእዚኽ ክፍል ላይ ፤ ሞግዚቶቻችን (Our Guardians) የእሚላቸው ፤ የፖለቲካ ስልጣን የእሚይዙትን ሰዎች ነው ።
በእኔ እምነት ፤ በእዚኽ ዘመን ይኽን መሰሉን የፖለቲካ ባለ ስልጣናት ማሰልጠኛ ተቋም ፤ ከሞራላዊ ልሽቀቱ በአሻገር ለአተገባበርም የእማይመች እና ሊሆን የእማይችል እንደ ሆነ ለአብዛኛው ሰው ግልጽ የእሚሆን ይመስለኛል ።
ከላይ እንደ አልነው በፕሌቶ እና አርስቶል ጽሁፎች ውስጥ ፤ መሰል ብዙ እንከኖች መንቀስ የእሚቻል ቢሆንም ፤ ከእሚኖሩበት ዘመን አንጻር በጣም የቀደሙ እና ዘመን ተሻጋሪ የእሚባሉ ፖለቲካዊ ግንዛቤዎችን አሳይተዋል ። ለምሳሌ ፦ ፕሌቶ በእዛኽ ዘመን ፤ የመረጃ ፍሰት እና ፕሮፖጋንዳ ፤ በአንድ ማሕበረሰብ ፖለቲካዊ ጤናማነት ውስጥ የአለውን አቅም በመረዳት ፤ የመረጃ እና የፕሮፖጋንዳ ስረዓት በእንዴት ያለ ስነ ምግባር መመራት እንደ አለበት መልካም የእሚባል ምክር ሲመክር እናገኛዋለን ።
አንዳንዶቻችን እንደ እምናውቀው ፤ የወቅቱ የግሪክ የልብ ወለድ ደራሲያን ፤ አማልክቶቻቸውን ገጸ ባሕሪዎቻቸው እንደ እሚያደርጉ እናም በድርሰታቸው አማልክቶቹ ፥ ለአኹኑ ዘመን ፈገግ የእሚያሰኙ ተግባራትን ሲፈጽሙ እንደ እሚገኙ ይታወቃል ። ለምሳሌ ፦ ዚየስ የእሚባለው ‘ዓምላክ’ እህቱ ከሆነችው እና ‘ሔራ’ ከእምትባለው ‘ ዓምላኪት ‘ ጋር በፍቅር በመውደቁ ፤ ፍቅሯ በምሽት ሲያሴር የነበረውን ተንኮል እንደ አስረሳው የእሚተርክ ድርሰት አለ ። ሪፐብሊክ በእሚለው መጽሐፉ ፤ ፕሌቶ እንደ እዚኽ የአለውን ባሕሪ እና ተግባር ለዓምላክ ገጸ ባሕሪ አላብሶ መተረክ ፤ እንደ እውነት ለእሚያያቸው የዘመኑ ግሪክ ማሕበረሰብ ፤ መጥፎ ምሳሌ እንደ እሚሆኑት እና መንግሥት ለፖለቲካዊ ኃላፊነት የእሚያሰለጥናቸውን ወጣቶች ከእንደ እዚኽ ዓይነት ስነ መግባርን ከእሚያበላሹ ፕሮፖጋንዳዎች መከላከል እንደ አለበት ወይንም ይኽን መሰል የስነ ምግባር ልሽቀት የእሚፈጥሩ ትምህርቶችን ማገድ (ሳንሱር) ማድረግ እንደ አለበት ይናገራል ፦
“... ስለ ዚየስ በእሚናገረው ተረት ፣ ሰዎች እና ሌሎች አማልክት ኹሉ ሲተኙ እና እርሱ ብቻ ቁጭ ብሎ በአለበት ፣ ሲያሴር የነበረውን ተንኮል ፣ ሔራን ሲያያት በእሚያድርበት ምኞት በቅጽበት እርግፍ አድርጎ ይረሳውና ፣ ወደ ማጀት እስኪ ኼዱ እንኳን መጠበቅ ተስኖት ፣ በአገኛት ቦታ ወለሉ ላይ አብሯት ልተኛ ይላል ፤ መጀመሪያ ቀን እንኳን ሲያያት እንደ ዛሬው በስሜት እንደ አልናወዘ እየ ነገራት።”
“... the tale of Zeus, who, while other gods and men were asleep and he the only person awake, lay devising plans, but forgot them all in a moment through his lust, and was so completely overcome at the sight of Here that he would not even go into the hut, but wanted to lie with her on the ground, declaring that he had never been in such a state of rapture before, even when they first met one another. “ [22]
በአመራር ማሰልጠኛ ውስጥ የእሚገቡት ወጣቶች ፤ ይኽንን ዓይነት ስሜታዊነትን እና ግብታዊነትይን የእሚያበረታቱ ታሪኮች ከእሚሰሙ ይልቅ ፤ እንደ ፕሌቶ ፤ ፅናትን ፣ ታማኝነትን ፣ ጀግንነትን ፣ አርበኝነትን ፣ ወዘተ ፤ የእሚያበረታቱ ወይንም መልካም በኃሪን በምሳሌኔት ቢሰሙ የእሚሻል ነው ብሎ በመሞገት ፤ የመረጃ ፍሰት በትምሕርት ስረዓት ቀረጻ እና በጠቅላላው የማሕበረሰብ ጤናማነት ውስጥ የአለውን ከፈትኛ አቅም በመረዳት ይኽንን ለመቆጣጠር ያሳየው ንቃት የእሚደነቅ ነው ።
እነ እዚኽን ኃሳቦች በፕሌቶ ላይ ያነሳኹበት ምክንያት ፤ ፕሌቶ እጅግ የእሚደነቅ ፈላስፋ የመሆኑን ያኽል ፤ ከአለንበት ዘመን አንጻር አንዳንድ የእሚያነሳቸው ኃሳቦች ወይንም የእሚለግሳቸው ምክሮች ፤ በጣም የተናቁ መሆናቸውን ለማሳየት ነው ።
ይኽንም ማሳየት ፤ የፈለኩበት ምክንያት ፤ እነ እዚኽ የፍልስፍና ኃያላን ስለ ዴሞክራሲ አመጣጥ እና ባሕሪ የነበራቸው ግንዛቤም ፤ በተመሳሳይ የራሱ ውስንነት የነበረበት መሆኑን ለማስረገጥ ነው ። ምክንያቱም ፕሌቶ ምንም እንኳን ከባድ ሚዛን ፈላስፋ ቢሆንም ፤ በሌሎች ጉዳዮች ላይ እንደ ተሳሳተው በዴሞክራሲም ላይ መሠረታዊ የእሚባል ስህተት ነበረበት።
በዴሞክራሲ ላይ ቀዳሚ የእሚባል ኃያሲ የሆነው ፕሌቶ ፤ በዴሞክራሲ ላይ ያቀረባቸው ትችቶች ትክክል እንደ አልሆኑ ፥ ሪፐብሊክ ተብሎ በተተሮገመው መጽሐፉ ፤ በዓለም ላይ ስለ እሚገኙ ዋና ዋና የመንግሥት ስረዓት ዓይነቶች አመጣጥ ፣ የስረዓቶቹ መሠረታዊ ችግር ፣ ስለ ስረዓቶቹ ባሕሪያት ፣ ወዘተ ፤ በማነጻጸር የእሚያብራራበትን መንገድ እንደ ማሳያ ወስደን እንይ ።
ለምሳሌ ፦ እንደ ፕሌቶ ገለፃ ፤ በዓለም ላይ በዋናነት አምስት ዓይነት የፖለቲካ ስረዓቶች አሉ ፦
እነ እዚኽ ስረዓቶችም ፤ ከላይ በተቀመጡበት ቅደም ተከተል በማሕበረሰብ ውስጥ ይፈጠራሉ ይላል ።
እንደ ፕሌቶ እምነት ፤ የፖለቲካ ስረዓት ሲጀምር ብዙ ግዜ አሪስቶክራሲ (Aristocracy) ወይንም የመኳንንት ስረዓት በመሆን ነው ።
ነገር ግን ፤ እያንዳንዳቸው ስረዓቶች በውስጣቸው ባለው መሠረታዊ ችግር ምክንያት እየፈረሱ በቀጣዩ ይተካሉ ። በእዚኽም መሠረት አሪስቶክራሲ ፣ በቲሞክራሲ ይተካል ፣ ቲሞክራሲ በኦሊጋሪኪ ይተካል ፣ ኦሊጋሪኪ በዴሞክራሲ ይተካል ፥ በስተ መጨረሻም ዴሞክራሲ በቲረኒ ይተካል ።
እንደ ፕሌቶ ትንታኔ ፤ በአራተኛ ደረጃ ላይ የእሚገኘው ዴሞክራሲ የድሆች መንግሥት ሲሆን ፤ ዴሞክራሲ የእሚፈጠረውም ፤ ኦሊጋርኪው (The Oligarchy) ወይንም ጥቂቶቹ እና ገዢ ወደ መሆን የተቀየሩት ኃብታሞች ፤ የአብዛኛውን ሕዝብ ኃብት በመግዛት በግዜ ኺደት አብዛኛውን ሕዝብ ነዳያን ማድረጋቸው የእማይቀር በመሆኑ ፤ አብዛኛው ሕዝብ ምንም የሌለው ነዳያን ሲሆን ፤ የሐገሬው ኃብት በሙሉ በጥቂት ሰዎች እጅ ይገባል ።
ከእዚያኽም በግዜ ኺደት ፤ ንብረቱን በሙሉ ለኃብታሙ የሸጠው ነዳያኑ እና ምንም የሌለው ፤ ንብረቱን የሸጠላቸውን ኃብታሞቹን በድሎት ምክንያት በጦርነት ጉዳይ ሰነፍ ሆነው ሲያየቸው ፤ አብዮት አስነስቶ ኃብታሞቹን እና ገዢዎቹን (The Oligarchy) ከስልጣን አውርዶ ፤ ኃብታቸውን ወስዶ ይከፋፈል እና ራሱ የመረጣቸውን ሰዎች በስልጣን ላይ በማስቀመጥ ፤ ያለ ማንም ከልካይ እንደ ፈለገ የእሚፋንንበት ነጻነት ያገኛል ይላል ። እንደ ፕሌቶ አረዳድም ፤ ዴሞክራሲ ማለት ይኼ ነው ፦
“... ብዙ ግዜ እንደ እሚሆነው ገዢዎች እና ገባሮች መንገድ ላይ መገናኘታቸው አይቀርም፣ ወደ አንድ ስፍራ ሲኼዱ በጉዞ ይሆናል ወይንም በሌላ የመገናኛ አጋጣሚ ፥ ... ምን አልባትም ጅማቱ የወጣው እና ፀሀይ ያከሰለው ነዳያኑ በጦርነት ወቅት ፀሀይ ፊቱን ነክቶት ከእማያውቀው እና የሰውነቱ ስብ ከተትረፈረፈው ባለ ፀጋው ጎን ሊሰለፍ ይችላል ፤ በእዚኽ ኹኔታ የተዝረጠረጠው ኃብታም ሲያቃስት እና የእሚያደርገው ሲጠፋው የእሚመለከት ነዳያን ፤ እንደ እዚኽ ዓይነቶቹ ሰዎች ኃብታም ሆነው የእሚኖሩት እንደ እርሱ ዓይነቶቹ ሰዎች እነ እዚኽን ዓይነቱን ኃብታም የመዝረፍ እና የመገልበጥ ድፍረት ስሌላቸው መሆኑን ማሰቡ ይቀራል ? ከእዚያኽም ከመሰል ወዳጆቹ ጋር በግል ሲገናኝ ፥ ‘የእኛ ጦረኞች ጀግንነታቸው ብዙም ዋጋ የለውም’ ማለቱስ ይቀራል ?... ከእዚያኽም ፤ በሽታ እንደ ያዘው የሰው አካል ... ሐገራቸውም ውስጥ ኦሊጋሪኪው (ኃብታሙ) የራሱን ቡድን እየመሠረተ በተቃራኒው ዴሞክራሲያዊ (ነዳያኑ) ኃይሉም የራሱን ቡድን እያጠናከረ ፤ ሐገራቸው ከውጭ ምንም ወራሪ ሳይመጣባት ፤ ዜጎቿ በቡድን ተከፋፍለው እርስ በእርሳቸው ውጊያ ውስጥ ትገባለች ። ከእዚኽም በኋላ ፤ ነዳያኑ ተፃራሪዎቻቸውን ገሚሱን በመጨፍጨፍ ፣ ገሚሱን ከሐገር በማባረር ከአሸነፉ በኋላ ፤ በሐገር ውስጥ የቀሩት ስልጣን እና ነጻነት በእኩልነት ይካፈላሉ ፤ ይኽም ገዢዎች በዕጣ የእሚመደቡት ስረዓት ነው ዴሞክራሲ የእሚባለው ። “
“…And often rulers and their subjects may come in one another’s way, whether on a journey or on some other occasion of meeting, ... and very likely the wiry sunburnt poor man may be placed in battle at the side of a wealthy one who has never spoilt his complexion and has plenty of superfluous flesh– when he sees such an one puffing and at his wits’-end, how can he avoid drawing the conclusion that men like him are only rich because no one has the courage to despoil them? And when they meet in private will not people be saying to one another ’Our warriors are not good for much’? ... And, as in a body which is diseased... the one party introducing from without their oligarchical, the other their democratical allies, and then the State falls sick, and is at war with herself; and may be at times distracted, even when there is no external cause....And then democracy comes into being after the poor have conquered their opponents, slaughtering some and banishing some, while to the remainder they give an equal share of freedom and power; and this is the form of government in which the magistrates are commonly elected by lot. [22]“
በእዚኽ የፕሌቶ የዴሞክራሲ ገለፃ መሠረት ፤ ዴሞክራሲ የእሚመጣው ፤ ንብረቱን የሸጠ ነዳያን ፤ ንብረቱን የሸጠለትን ኃብታም ተጋላጭነት ወይንም ኃብት እና ምቾት አስንፎት ሲያይ ፤ ከእሚፈጠርበት ፥ የቀማኛነት እና የዘራፊነት የቅናት ስሜት ነው ።
በእዚኽ መልኩ ፤ ሆ ብሎ ነዳያኑ ኃብታሙን ከዘረፈ እና ኃብቱን ከተከፋፈለ በኋላ ፤ አዲስ መንግሥት በእጣ (በምርጫ ሰአይሆን) መርጦ ፤ አለቃ እና ገዢ የሌለበት ፤ የስድ ኑሮውን የእሚኖርበት ኹኔታ ነው ፤ ዴሞክራሲ ለፕሌቶ ።
ከላይ የተቀመጠውን የፕሌቶን የዴሞክራሲ አመጣጥ ገለጻ የተመለከተ ሰው ፤ የዘመናዊ ከምኒዝም መሥራች በሆነው ካርል ማርክስ ፤ የፖለቲካዊ ጽንፈኝነት በእሚል በእዚኽ መጽሐፍ ውስጥ እንደ አየነው ፤ የመደብ ትግል በካፒታሊስቱ እና በሠራተኛው መካከል መካኼዱ የግድ ነው በእሚል ፤ እንደ ከምኒስት ማንፌስቶ [18] ባሉ የማርክሲዝም ሰነዶች ውስጥ የአንጸባረቀው ኃሳብ ፤ እና ታሪክ በመደብ ግጭት መዘውርነት እየተመራ ፤ ለምሳሌ ፦ ከፊውዳሊዝም ወደ ካፒታሊዝም ፣ ከካፒታሊዝም ወደ ሲሻሊዝም ፣ ወዘተ ፤ ይሸጋገራል የአለበት ኹኔታ ፤ ከተወሰኑ ለውጦች በስተቀር ከፕሌቶ ትንታኔ ጋር ተመሳሳይነታቸውን ማየት ይችላል ።
ፕሌቶ ፤ ዴሞክራሲ ይመጣበታል የአለው መንገድ እና የዴሞክራሲ ባሕሪ ነው የአለው ፤ ኃብቱን የሸጠ ነዳያን ፥ ኃብቱን በገዛው ኃብታም ላይ ነፍጥ በማንሳቱ ዴሞክራሲ ይጀመራል ፣ በዴሞክራሲ ውስጥ ስልጣን የእሚከፋፈለው መሪን በእጣ በመምረጥ ነው በእሚሉት ኃሳቦች ብቻ ሰአይሆን በዴሞክራሲ ጉዳይ የነበረው ግንዛቤ ግርድፍ እና የግንዛቤ ውስንነት እንደ ነበረበት የአሳየው ፤ በስረዓት አልበኝነት ወይንም በስነ ምግባር መላሸቅ እና በነፃነት መካከል የአለውን ልዩነት ባግባቡ የመረዳት ችግርም ይዞ በመገኘቱም ነው ።
እንደ ፕሌቶ አገላለጽ ፤ የዴሞክራሲያዊ ስረዓት ወድቆ በአምስተኛው ወይንም በአምባገነናዊው ስረዓት የእሚተካው ፤ በዴሞክራሲ ውስጥ የእሚኖረው ሰው የስረዓት አልበኛ እና የብኩን ስነልቦና የእሚያዳብር በመሆኑ ነው ፦
“... [ዴሞክራሲ ውስጥ የእሚኖረው ሰው] በእየ እለቱ የግዜያዊው ፍላጎቱን ማርካት ላይ ብቻ በማተኮር ይኖራል ፤ አንድ አንድ ግዜ በፌሽታ እና በሙዚቃ ግዜውን ያሳልፋል ፣ አንድ አንድ ግዜ ውኃ ብቻ እየጠጣ ፥ ውፍረት በመቀነስ ለመቅጠን ይሞክራል ፣ አንድ አንድ ግዜ ጂምናዚየም በመመላለስ ሌላውን ኃላፊነቱን በመዘንጋት ሥራ ይፈታል ፣ ሲለው ደግሞ እንደ ፈላስፋው ለመኖር ፤ በእየቦታው ጎራ እያለ ስለ ፖለቲካ ማንኛውንም በአዕምሮው ላይ የእሚመጣውን በማውራት ራሱን በፍልስፍና ይወጥራል ፣ ደግሞ በሌላ ወቅት በጦር ሜዳ ጀብድ የማረከው ሰው ከዓየ ደግሞ ፥ የጦር ሜዳ ጀብደኛም ለመሆን ይሞክራል ፣ ወይንም ጎበዝ ነጋዴ አይቶ ከተማረከም እንደ እዛው ። ህይወቱ ሕግም ሆነ መርህ የእሚባል ነገር የለውም ፣ ይኽን የባዛኝ ህይወት የነጻነት ደስታ እና በረከት ብሎ ይሰይመዋል ፤ ህይወቱም በእዚኽ መልኩ ይቀጥላል... ይኽም ለከት የሌለው (ነጻነትን)የመፈለግ ጉዞ ፤ ሌላውን የህይወት ጉዳይ እንዲ ዘነጋ ያደርገውና አምባገነኑ ብቅ እንዲል ግድ ይላል ።”
“... Yes, I said, he lives from day to day indulging the appetite of the hour; and sometimes he is lapped in drink and strains of the flute; then he becomes a water-drinker, and tries to get thin; then he takes a turn at gymnastics; sometimes idling and neglecting everything, then once more living the life of a philosopher; often he is busy with politics, and starts to his feet and says and does whatever comes into his head; and, if he is emulous of any one who is a warrior, off he is in that direction, or of men of business, once more in that. His life has neither law nor order; and this distracted existence he terms joy and bliss and freedom; and so he goes on... the insatiable desire of this and the neglect of other things introduces the change in democracy, which occasions a demand for tyranny. [22]“
ይኽም ማለት ወይንም እንደ ፕሌቶ በዴሞክራሲያዊ ስረዓት ውስጥ የእሚኖረው ሰው ፤ በነጻነት ስም ሥራ ፈት እና ባዛኝ በመሆኑ ህይወቱን በእማይረቡ ነገሮች ላይ በማባከን ሲንዘላዘል ፤ አምባገነናዊ ዝንባሌ የአለው ፖለቲከኛ እነ እዚኽን ዴሞክራሲ ያባከናቸውን እና ያሰነፋቸውን ዜጎች በቀላሉ አሸንፎ ስልጣን እንዲይዝ በር ይከፍትለታል ።
ይኽም ዴሞክራሲ የእሚፈጥረው የዜጎች ባካኝነት ነው የዴሞክራሲያዊ ስረዓት መውደቅ ምክንያት እና በፕሌቶ የማሕበረሰብ አወቃቀር ዝግመት ቅደም ተከተል መሠረት ከ4ኛው ወደ 5ኛው ማለትም ከዴሞክራሲ ወደ ቲረኒ (ፍጹማዊ አምባገነንነት) ማሕበረሰብ የእሚሸጋገረው ።
ስለ እዚኽ ፦ ከፕሌቶ የዴሞክራሲያው መንግሥት ግንዛቤ ብዥታ ተነስተን ፤ ፕሌቶ የዴሞክራሲያዊ መንግሥት ተቃዋሚ መሆኑን ለመረዳት ብዙም አስቸጋሪ አይደለም ። ምክንያቱም በፕሌቶ ገለፃ ዴሞክራሲ ማለት ፦ የአመፀኞች ፣ የስረዓት አልበኞች ፣ የሥራ ፈቶች እና የዓላማ ቢሶች መንግሥት ነው ።
ምንም እንኳን የፕሌቶ የዴሞክራሲ ገለፃ እና ትችት ፤ መሠረታዊ የግንዛቤ እጥረት የአለበት መሆኑ ከላይ በተቀመጡት ገለፃዎች በግልፅ የእሚታይ ቢሆንም ፤ ፕሌቶ በፍልስፍናው እና በፖለቲካዊ ሳይንስ መስክ የአለው ተከባሪነት እና ዝና ፤ የተሳሳተውን የዴሞክራሲ ግንዛቤውን ክብደት ይሰጣቸዋል ።
ይኽንም መሰሉ ተከባሪ ፖለቲከኞች በዴሞክራሲ ላይ የነበራቸው የተዛባ አመለካከት ነው ዴሞክራሲን በእዚኽ መልኩ ለረዥም ዘመን ያዳፈነው።
ፕሌቶ ፤ በእርሱ ፅንሰ ኃሳብ መሠረት የእሚዋቀረው መንግሥት የሕዝብ ወገንተኛ ስለ ሆነ ፤ ቢዋሽም ለሕዝብ ጥቅም ነው የእሚዋሸው ከአለ በኋላ ፤ በሽተኛ ለኃኪሙ መዋሸት እንደ እማይገባው ኹሉ ፤ ገባሩ (ሕዝቡ) ግን ለመንግሥት መዋሸቱ ወንጀል ነው ይላል ፦
“ለመዋሸት የእሚፈቀድለት ማንም ሰው ቢኖር ፤ ሐገረ ገዢዎች ብቻ ናቸው ፥ እነርሱም የውጭን ጠላት ወይንም የራሳቸውንም ሕዝብ ፤ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ሲባል ማታለል ይችላሉ ። ከእነርሱ ውጭ የሆነ ማንኛውም ሰው ፤ እንደ እዚኽ ዓይነት ተግባር ውስጥ በፍጹም መግባት አይፈቀድለትም ። ገዢዎች ይኽ መብት ቢኖራቸውም ተርታው ነዋሪ ግን ይኽን መብት ማግኘት ፤ አንድ ሰው ለስፖርት አሰልጣኙ ወይንም ለኃኪሙ ፤ በሰውነቱ ላይ የእሚሰማውን ህመም እንደ መደበቅ ያኽል እጅግ አሰከፊ ነገር ነው....። “
“Then if any one at all is to have the privilege of lying, the rulers of the State should be the persons; and they, in their dealings either with enemies or with their own citizens, may be allowed to lie for the public good. But nobody else should meddle with anything of the kind; and although the rulers have this privilege, for a private man to lie to them in return is to be deemed a more heinous fault than for the patient or the pupil of a gymnasium not to speak the truth about his own bodily illnesses to the physician or to the trainer... [22]“
ዋናው ቁም ነገር ፤ ከግንዛቤ እጥረት ይኹን ወይንም እርሱ የእሚለውን ፈላስፋውን ንጉሥ ለማድረግ ከአለው ፍላጎት የተነሳ ይኹን ፤ የፕሌቶ ፥ የዴሞክራሲ ገለፃ ወይንም ግንዛቤ የተሳሳተ ነው ።
በእርግጥ ይኽ የእኔ ብቻ አመለካከት ሰአይሆን ፤ የፕሌቶ የራሱ ተማሪ የነበረው አርስታትል ፤ ከላይ የተቀመጠውን የፕሌቶ የዴሞክራሲ ገለፃ ውስንነት በእሚከተለው መልኩ አስቀመጦቷል ። እዚኽ ጋር ፤ ለማሳሰብ ያኽል ፤ የአርስታትል የዴሞክራሲ ግንዛቤ ከፕሌቶ የተሻለ ቢሆንም ፤ የአርስታትልም የዴሞክራሲ ግንዛቤ ፤ አኹን የአለንበት ዘመን ላይ የአለውን የዴሞክራሲ አስተሳሰብ የእሚመጥን ነው ማለት አይደለም ።
እንደ አርስታትል ገለፃ ፤ አንድን ፖለቲካዊ ማሕበረሰብን የኢከነሚ መመዘኛን መሠረት በማድረግ ኃብታም እና ነዳያን ወይንም በእነ አርስታትል ዘመን የነበሩ ፖለቲከኞች እንደ እሚሉት ፤ ኦሊጋርኪ እና ዴሞክራሲ ፥ ኦሊጋርኪ ኃብታሙ ፥ ዴሞክራሲ ነዳያኑ ፤ ብሎ በተፃራሪ መደብ መከፋፈል ፤ የተለመደ ቢሆንም ስህተት ነው ይላል ።
ይኽንንም የአለበትን ምክንያት ሲያስረዳ ፦ ማሕበረሰብን ነዳያን እና ኃብታም በእሚሉ ኹለት ጎራዎች ብቻ መክፈል ትክክል አይደለም ፤ ምክንያቱም ፦ ኃብታም የእሚባሉትም መደባት ቢሆኑ በውስጣቸው ብዙ ዓይነት ኢከነሚያው እና የተለያየ ይዘት የአላቸው ልዩነቶች ያሏቸው ሲሆን ፥ ነዳያኑም (ዴሞው ወይንም ሰፊው ሕዝብ ወይንም ድኃው) በተመሳሳይ በውስጡ ብዙ የተለያየ የኑሮ ደረጃ የያዘ መሆኑን በማስረጃነት ያቀርባል ።
ስለ እዚኽ ፦ በግርድፉ ማሕበረሰብን ነዳያን እና ኃብታም ብሎ በኹለት ተፃራሪ መደብ መከፍል እና በተጨማሪም በኃብታሞቹ ወይንም በድሆቹ መካከል ውስጥ ያሉትን ብዙ ዓይነት ልዩነቶች እንደ ሌሉ መቁጠር ትክክል እንደ አልሆነ ያስቀምጣል ፦
“እንደገናም ፥ ኃብታሙ ጥቂት ስለ ሆነ እና ነዳያኑ ብዙ ስለ ሆነ ፤ በተቃርኖ ውስጥ የእሚኖሩ ይመስላል ፤ ከእዚኽም የተነሳ የበረታው መንግሥት ይመሰርታል ። ከእዚኽም በመነሳት ፤ አንድ ልማዳዊ አባባል አለ ፦ ኹለት ዓይነት መንግሥታት አሉ እነርሱም ፤ ዴሞክራሲ እና ኦሊጋርኪ … የተለያዩ ዓይነት ዴሞክራሲ እና ኦሊጋርኪ እንደ አሉ ላሳይ … ምክንያቱም መኳንንቱም ሆኑ መደበኛው ሕዝብ በውስጡ የተለያዩ ክፍፍል እንደ አለው ልአስቀምጥ ፤ ተርታውን ሕዝብ ብእንወሰድ አንድ አንዱ ገበሬ ነው ፣ አንድ አንዱ የእደ ጥበብ ባለ ሞያ ነው ፣ አንድ አንዱ ነጋዴ ነው … መኳንንቱ እንደገና በኃብት መጠን ፣ በውልደት ፣ በዝና ፣ በትምህርት እና መሰል ልዩነቶች ያሉባቸው ናቸው ።”
“Again, because the rich are generally few in number, while the poor are many, they appear to be antagonistic, and as the one or the other prevails they form the government. Hence arises the common opinion that there are two kinds of government—democracy and oligarchy… Let me now show that there are different forms both of democracy and oligarchy, ... For both in the common people and in the notables various classes are included; of the common people, one class are husbandmen, another artisans; another traders,… The notables again may be divided according to their wealth, birth, virtue, education and similar differences. [1]“
አርስታትል ፤ ልማዳዊ ነው በእሚለው የፕሌቶ እና መሰሎቹ የዴሞክራሲ ግንዛቤ ላይ የነበራቸውን ግንዛቤ ስኹትነት ለማስየት የእሚያደርገው ገለጻ በእዚኽም ብቻ አልአበቃም ። እንደ እሚታወቀው ፤ አርስታትል ፤ ‘ፖለቲካ’ የእሚባለውን መጽኃፉን ከመጻፉ በፊት ፤ የ158 ግዛቶችን (city states ወይንም ሐገራት ልእንላቸው እንችላለን) ፤ መንግሥታቸውን የእሚያዋቅሩበትን ልማድ በመረጃ ደረጃ ሰብስቦ አጥንቷል ይባላል ፤ ለምሳሌ ፦ ኢትዮጲያኖች ንጉሥ የእሚሾሙት መልክ እያዩ በመሆኑ መንግሥታቸው መልክን መሠረት የአደረገ መረጣ ስለ እሚያደርግ ኦሊጋርኪ ነው ብሏል :-
“… ኢትዮጲያ ውስጥ አለ እንደ እሚባለው ፤ የመንግሥት ስልጣን የእሚሰጠው በተክለሰውነት ወይንም በውበት መመዘኛ ስለሆነ ፤ የመንግሥታቸው ዓይነት ኦሊጋሪክ ነው ፤ ረዥም እና መለከ መላካም የሆኑ ሰዎች ቁጥራቸው ጥቂት በመሆኑ ።”
“… a government in which the offices were given according to stature, as is said to be the case in Ethiopia, or according to beauty, would be an oligarchy; for the number of tall or good-looking men is small. [1]“
ከእዚኽም ተነስቶ ፤ በእርሱ ዘመን የተለመደ በእሚለው ዕሳቤ የተያዘው ፤ ዴሞክራሲ የነዳያኑ ፥ ኦሊጋርኪ የኃብታሙ መንግሥት የእሚለው ክፍፍል ፤ ልክ እንደ አልሆነ እና ነዳያኑም ኃብታሙም በእኩልነት የእሚኖሩበት ዴሞክራሲያው ስረዓት እንደ አለም ያስቀምጣል ።
ከእዚኽም ቀጥሎ በእርሱ ዘመን በጠቅላላው ዴሞክራሲያዊ ሊባሉ የእሚገባቸው ነገር ግን በውስጣቸው ብዙ ዓይነት የአወቃቀር ልዩነት የአላቸው መንግሥታት መኖራቸውን አስቀምጦ ፤ በእዚኽም የፕሌቶ ዓይነቱ ዴሞክራሲን አንድ ዓይነት ብቻ አደርጎ ማቅረቡ እና ዴሞክራሲን የነዳያኑ መንግሥት ብሎ የእሚያስቀምጠው ግትር ፍረጃ ልክ እንደ አል ሆነ እና ዴሞክራሲ ራሱ በውስጡ ብዙ ፈርጅ እንደ አለው ፤ ከእነ እዚኽም መካከል ኃብታሙም ነዳያኑም በእኩልነት የእሚታዩበት ዴሞክራሲ እንደ አለ ያሳያል ፦
“ከኹሉም ዴሞክራሲ ዓይነቶች መጀመሪያ የእሚመጣው ፤ ጥብቅ በሆነ እኩልነት ላይ የተመሠረተው ነው ። ይኽ ዴሞክራሲ ፤ ነዳያኑ ከኃብታሙ የበለጠ ምንም ዓይነት መብት ሊኖረው አለ መገባቱ ፥ ፍትሕ ነው ፤ አንዱ የአንዱ አለቃ ሊሆን አይገባም ፤ ነገር ግን ኹለቱም እኩል ሊሆኑ ይገባል ይላል ። ስለ እዚኽ ፤ ማንም ነፃነት እና እኩልነት ፤ በዋናነት በዴሞክራሲ ውስጥ ይገኛሉ ብሎ ከአለ ፤ ይኽ እኩልነት በይበልጥ የእሚረጋገጠው ፤ ኹሉም ሰዎች ያለ ምንም ዓይነት ልዩነት በመንግሥት ጉዳይ እኩል የመሳተፍ መብት ሲኖራቸው ነው ይኽ የእሚረጋገጠው ። ሕዝቡም (ነዳያኑ ወይንም ድኃው) ብዛት ስለ አለው እና በስተመጨረሻም የአብዛኛው ሕዝብ ውሳኔ ሚዛን ስለ እሚደፋ ፤ ይኽ ዓይነቱ መንግሥት የግድ ዴሞክራሲ መባል አለበት ። በእዚኽም መሠረት ፤ ይኽም አንዱ የዴሞክራሲ ዓይነት ነው ።”
“Of forms of democracy first comes that which is said to be based strictly on equality. In such a democracy the law says that it is just for the poor to have no more advantage than the rich; and that neither should be masters, but both equal. For if liberty and equality, as is thought by some, are chiefly to be found in democracy, they will be best attained when all persons alike share in the government to the utmost. And since the people are the majority, and the opinion of the majority is decisive, such a government must necessarily be a democracy. [1] “
ከእዚኽ እንደ እምንረዳው ፤ በጣም ግርድፍ እና ፍርደ ገምድል ከሆነው የፕሌቶ የዴሞክራሲ አረዳድ ይልቅ በአርስታትል ፖለቲካ የታየው የዴሞክራሲ ግንዛቤ ፤ የበለጠ ሰፋ ያለ እና ከተግባራዊ ምሳሌ ተነስቶ ወደ አንድ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የተሞከረበት በመሆኑ ከፕሌቶ የዴሞክራሲ ግንዛቤ ይልቅ የአርስታትል ግንዛቤ ላቅ ያለ መሆኑ ግልፅ ነው ።
የክሌስተነሱ ዴሞክራሲ እንደ እነ ፕሌቶ እና አርስታትል መሰል የተከበሩ የፖለቲካ ሊህቃን ከመታገዝ ይልቅ ሲተች በመቆየቱ ዴሞክራሲ ከእላይ እንደ አልነው በአውሮፓ ሕዳሴ ትንሳኤ እስኪያገኝ ከሌሎች የመንግሥት አወቃቀሮች ይልቅ ተዳፍኖ ቆይቶ ነበር።
በርግጥ ዴሞክራሲ ከአውሮፓ ሕዳሴ አንስቶ አንሰራራ ስንል ፤ ዴሞክራሲ የእሚደርስበት መሠረት የለሽ ትችት አበቃ ማለት አይደለም ፤ ምክንያቱም ፦ ዴሞክራሲ በአውሮፓ ሕዳሴ ከአንሰራራበት አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ፤ ይዘታቸው እና ዓይነታቸው የተለያዩ ነገር ግን ውኃ የእማይቋጥሩ ትችቶች የእሚቀርቡበት መሆኑ ለአብዛኛዎቻችን ዜና አይደለም።
እ.አ.አ. በ1776 ዓ.ም. አከባቢ የአሜሪካ መሥራቾች ፤ ዴሞክራሲያዊ ወይንም ሕዝባዊ መንግሥት መመሥረት እንችላለን ብለው ሲንቀሳቀሱ ፤ ዴሞክራሲ የእሚለው አስተሳሰብ ፤ በየትኛውም መልኩ ቢተገበር ፤ ከዓለበት መሠረታዊ ስህተት የተነሳ ፤ ሊተገበር የእማይችል ፤ ቢተገበረርም በአጭር ግዜ መልሶ መፍረሱ እማይቀር ስረዓት ነው ብለው ከደመደሙ ሰዎች ተቃውሞ ሲገጥማቸው ነበር ።
እነ እዚኽ የዴሞክራሲ ኃያሲያን ፤ የተለያየ ዓይነት ዴሞክራሲያዊ መንግሥትን ለማቆም የሞከሩ ጥንታዊ የግሪክ እና የሮም ስልጣኔዎችን በማጣቀስ ፤ ዴሞክራሲ የእሚሰራ ቢሆን ኖሮ ፤ እነ እዚኽ መንግሥታት የገቡባቸው ችግሮች ውስጥ አይገቡም ይሉ ነበር ።
የሕዝባዊት አሜሪካ መሥራች አባት ከእሚባሉት መካከል አንዱ የሆነው አሌክሳንደር ሐሚልተን ፤ የዴሞክራሲያዊት ሐገር እቅዳችኹ አይሳካም በእሚል ይቀርብባቸው የነበረውን ትችት እንዲኽ ይገልጸዋል ፦
“የቀደሙትን የግሪክ እና ጣሊያን ትናንሽ ሪፐብሊኮች ታሪክ የእሚያነብ ሰው ፤ እነ እዚኽ ትናንሽ ሪፐብሊኮች በሐገራቸው ባለው መናጥ ፤ በፍፁም አምባገነን እና በስረዓት አልበኝነት መካከል በፍጥነት የእሚወድቁበትን አኳኋን እያየ ፤ በፍርኃት እና በመጸየፍ ስሜት መሞላቱ የእማይቀር ነው ። እንደው ትንሽ የእፎይታ ግዜ ያገኙ መስለው ሰላም ቢሰፍን ፤ ይኽ ሰላም የእሚቀጥለው ማዕበል እስኪ መጣ ብቻ የቆየ ነው የእሚሆነው ። አኹንም አኹንም የተድላ ግዜ ወደ እይታችን ቢመጣ ፡ ይኽን የተድላ ግዜ በቅርቡ መጥቶ የእሚያጠፋውን የመከፋፈል እና የቡድን ጠብ እያሰብን ውስጣችን በእሚፈጠር ስጋት እንድ እናየው እንሆናለን ። ከእሚያስገመግመው ጥቁር ደመና መሐል በድንገት የክብር ጮራ ብቅ ቢል ፤ ይኽም የክብር ጮራ በእሚያልፈው እና በግዜያዊው ነጸብራቁ ቢያስደስተን ፤ በጥቂት ግዜ ውስጥ የእነዛኽ ሐገር አፈር የአበቀሉት ፤ ይኽ አንፀባራቂ ክህሎት እና ተሰጦ ፤ በመንግሥት ክፋት አቅጣጫውን ስቶ ማንጸባረቁን እንደ እሚያጠለሸው እየ አስጠነቀቁን ነው ።
የእነ እዚኽን ትናንሽ ሪፐብሊኮች ታሪክ ከእሚያበላሸው ንግርት እየተነሱ ፤ የአምባገነን ስረዓት ደጋፊዎች ትችታቸውን በሪፐብሊክ (ሕዝባዊ) የመንግሥት አወቃቀር ብቻ ሰአይሆን በነጻነት በራሱ ላይ አድርገዋል ። ነጻ መንግሥት የእሚባለው ነገር ፤ ከማሕበረሰብ የአወቃቀር መርህ ጋር በፍጹም ሊጣጣም የእማይችል ነው በማለት ፤ የነጻ መንግሥት ደጋፊዎች እና ወዳጆች ላይ ራሳቸውን አጓደዋል ። ደስ የእሚለው ፤ ለሰው ዘር በሙሉ ፤ እጅግ አስደናቂ የእሚባሉ ተምሳሌት የአላቸው በነጻነት (Liberty) መደብ ላይ የበቀሉ ጥለቶች ፤ ለዘመናት ቦግ ብለው ታይተው የእነርሱን ጨለምተኛ ተረት ተረት ባዶ አድርገውታል ። አሜሪካም ሰፊ እና ፅኑ መሠረት ከአላቸው ሕንጸቶች አንዷ በመሆን ፤ እንደ ቀደሙት ኹሉ የስህተተኝነታቸው ማስተወሻ ኃውልት እንደ እምትሆን አምናለሁ ።”
“It is impossible to read the history of the petty republics of Greece and Italy, without feeling sensations of horror and disgust at the distractions with which they were continually agitated, and at the rapid succession of revolutions, by which they were kept perpetually vibrating between the extremes of tyranny and anarchy. If they exhibit occasional calms, these only serve as short-lived contrasts to the furious storms that are to succeed. If now and then intervals of felicity open themselves to view, we behold them with a mixture of regret arising from the reflection, that the pleasing scenes before us are soon to be overwhelmed by the tempestuous waves of sedition and party rage. If momentary rays of glory break forth from the gloom, while they dazzle us with a transient and fleeting brilliancy, they at the same time admonish us to lament, that the vices of government should pervert the direction, and tarnish the luster, of those bright talents and exalted endowments, for which the favored soils that produced them have been so justly celebrated.
From the disorders that disfigure the annals of those republics, the advocates of despotism have drawn arguments, not only against the forms of republican government, but against the very principles of civil liberty. They have decried all free government, as inconsistent with the order of society, and have indulged themselves in malicious exultation over its friends and partisans. Happily for mankind, stupendous fabrics reared on the basis of liberty, which have flourished for ages, have in a few glorious instances refuted their gloomy sophisms. And, I trust, America will be the broad and solid foundation of other edifices not less magnificent, which will be equally permanent monuments of their error. [70]“
ይኽ ከላይ የቀረበውን የአሌክሳንደር ሐሚልተን መከላከያ ፤ እርሱ በነበረበት ወቅት ፤ አሜሪካ ፥ እናት ሐገሯ ታላቋ ብሪታኒያ የቀኝ ግዛትነት እንጂ የእንግሊዝ እኩል አካልነት መብት አልሰጥሽም ከአለቻት በኋላ ፤ በዓመጽ ተነጥላ የራሷን ነጻ መንግሥት ማቋቋም በጀመረችበት ወቅት ፤ በወቅቱ የነበረው የአምባገነን ስረዓት አፍቃሪዎች ፤ ነጻ መንግሥት ወይንም ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ወይንም ሕዝባዊ መንግሥት፤ በጽንሰ ኃሳብ ደረጃ ስህተት የአለበት እና አጉል ምኞት እንጂ ፤ መሬት ላይ ወርዶ በተግባር ሊተረጎም የእሚችል ነገር አይደለም ብለው ለእሚሞግቱት ሰዎች ፤ ከተጻፉ ብዙ ታዋቂ እና ታሪካዊ ከእሚባሉት አምዶች መካከል ፤ ፌደራሊስት ቁጥር 9 በእሚባለው ላይ ያሰፈረው ነው ።
በእዚኽ ረገድ የአሜሪካ ዴሞክራሲ ፤ ይቀርብበት ከነበረው ትችት አንዱ ፤ ዴሞክራሲ የእሚሰራው በጣም ጥቂት ሕዝብ በእሚኖሩበት ማሕበረሰብ ውስጥ እንጂ እንደ አሜሪካው ሰፈራ ባሉ ትላልቅ ማሕበረሰባት ውስጥ አይደለም የእሚል እና ለእዚኽም በማስረጃነት ሞንተስኪው የተባለው የፈረንሳይ ሊህቅ በዴሞክራሲ እና በሕዝብ ብዛት መካከል ስለ አለው ግንኙነት የጻፈውን ጽሑፍ በማስረጃነት በማቅረብ ነበር ።
አርስታትል ራሱ ፤ ሕዝብ የቁጥር መብዛት ለመንግሥት አስተዳደር አይመችም የእሚል የአመለካከት ውስንነት ነበረበት ፦
“በተጨማሪም ፣ ልምድ እንደ እሚያሳየን ብዙ ሕዝብ የአለበት ከተማ ፤ መልካም አስተዳደር ኖሮት አያውቅም ፤ ምክንያቱም ፦ እስከ ዛሬ መልካም አስተዳደር የተገኘባቸው ቦታዎች የሕዝብ ቁጥራቸው የተወሰኑት ናቸው። ... ትልቅ ቁጥር[2] የአለው ሕዝብ በስረዓት ሊኖር አይችልም።”
ስለ እዚኽ በወቅቱ የእነ ሐሚልተን በዴሞክራሲ ላይ እየቀረበ ጥረታቸውን የእሚያጣጥለው አንዱ ጸረ ዴሞክራሲ ትችት ፤ ዴሞክራሲያቹሁ ፣ የነጻነት መንግሥታችሁ ፣ የሕዝብ መንግሥታችሁ ፤ እንደ አሜሪካ በአለች ትልቅ ሐገር አይሳካም የእሚል ትችት ነበር ።
ሐሚልተን ፤ ለእዚኽ ትችት ምላሽ በሰጠበት ፌደራሊስት ቁጥር 9 በተባለው አምዱ ፦ ሞንተስኪው ራሱ ብዥታ የአለበት በመሆኑን እና ሞንተስኪው የዳበረውን እና እነ ሐሚልተን እየተገበሩት የአለውን ዴሞክራሲ ስለ እማያውቀው እርሱ በዴሞክራሲ ላይ የሰጠው ትችት ግዜው ያለፈበት መሆኑን አስቀምጦ ትችቱን ተከላክሏል ።
ሐሚልተን ፤ በቀደመው ዘመን ያልነበሩ እና በእርሱ ዘመን የተካተቱ ፤ ስለ እዚኽም እነ ሞንተስኪው ዓይነት ሊህቃን በዴሞክራሲ ስረዓት ላይ የእሚያቀርቡትን ትችት ዘመን አለፍ የእሚያደርጉዋቸውን ፤ የዴሞክራሲ ማሻሻያዎች የአላቸውን እንዲኽ አስቀምጧቸዋል ፦
“ስልጣንን በቋሚነት በእየ ሥራ መምሪያው ማከፋፈል ፣ የሕግ አውጪውን ስልጣን ሚዛናዊነት ማረጋገጥ እና መቆጣጣሪያ ማበጀት ፣ ዳኞች የባሕሪ ዝቅጠት እስከ አላሳዩ ድረስ ኃላፊነታቸውን እንደ ያዙ እንዲ ቀጥሉ ማድረግ ፣ በሕግ መወሰኛው ቤት ውስጥ ሕዝቡ በመረጣቸው ሰዎች እንዲ ወከል መደረጉ ፤ አዲስ ማሻሻያዎች ናቸው ወይንም ትርጉም በእሚሰጥ መልኩ የተሻሻሉት በእኛ ዘመን ነው ። እነርሱም ደግሞ ፤ የሕዝባዊ መንግሥት ታላቅነት የእሚጠበቅበት መላዎች ፤ ኃይለኛ መላዎች እና ጉድለቶቹ የእሚታረሙበት ወይንም እስከ እነ አካቴው የእሚወገዱበት መንገድ ናቸው ።”
“The regular distribution of power into distinct departments; the introduction of legislative balances and checks; the institution of courts composed of judges, holding their offices during good behavior; the representation of the people in the legislature, by deputies of their own election; these are either wholly new discoveries, or have made their principal progress towards perfection in modern times. They are means, and powerful means, by which the Excellencies of republican government may be retained, and its imperfections lessened or avoided. [70]“
በታሪክ እንደ እምናውቀው ፤ የሐሚልተን ዴሞክራሲን የተከላከለበት መከራከሪያ ፤ በግዜ ኺደት ተፈትኖ ፤ ብዙም አትፈይዱም ፤ በዘውዳዊዋ እና መኳንንታዊቷ አውሮፓ ለእናንተ ቦታ የለም ተብለው ወደ ምድረ አሜሪካ የተሰደዱትን ‘ደካሞች’ አንድ መቶ ዓመት በአልፈጀ ግዜ ውስጥ ፤ እስከ ዛሬ ድረስ ተገዳዳሪዎቹን ኹሉ እያሸነፈ ያለ የዓለማችን ልዕለ ኃያል ሐገር ለመገንባት አስችሏቸዋል ።
እነ እዚኽ ፤ በዴሞክራሲ ላይ የቀረቡ የአልናቸው የጥንታዊው እና የመካከለኛው ዘመን ትችቶች ፤ ትችቶቹ የተቀናበሩበት ዘመን እንጂ ጥንታዊ እና የመካከለኛው ዘመን ትችቶች ብዬ እንድ አቀርባቸው የአደረገኝ ፤ ዛሬም ቢሆን ፤ ምንም እንኳን የትችታቸው ይዘት (የአንዳንዶቹ) የጥንታዊው የዴሞክራሲ ትችት ከእሚባሉት ጎራ የእሚመደብ ቢሆንም ፤ የጥንታዊዎቹን የዴሞክራሲ ኃያሲያን ኃሳብ ፤ በእዚኽ ዘመን በዴሞክራሲ ላይ የእሚያቀርቡ ሰዎች አሉ ። ለምሳሌ ፦ የነፃነት ታጋይ የእሚባሉት ፤ የቀድሞው የዚምቧቤው ርዕሰ ብሔር ሮበርት ሙጋቤ ፤ ዴሞክራሲ በአፍሪካ አይሰራም ሲሉ በአደባባይ ተደምጠዋል ። ሌሎችም በእዚኽ በእኛ ዘመን ዴሞክራሲ የድሆች ቀዳሚ አጀንዳ እንደ አልሆነም ለማስቀመጥ ሲሞክሩ ይታያል ።
እውነታውን ከአየነው ግን ፤ ዴሞክራሲ ከሌሎች የመንግሥት ዓይነቶች በተለየ ኹኔታ በሕዝብ ኢከነሚያዊ ኹኔታ ላይ እንዲ ደገፍ የእሚያደርገው ምንም ነገር የለም ። ብዙዎች በአፍሪካ ወይንም በነዳያን ሐገራት ዴሞክራሲ አይሰራም የእሚሉ ሰዎች ፤ መመለስ ያለባቸው ጥያቄ ፤ የአኹኑ የአፍሪካ ወይንም የአንዱ ነዳያን ሐገር ሕዝብ እ.አ.አ. በ1215 ዓ.ም. ከነበረው የብሪታኒያ ሕዝብ ወይንም በ1787 ዓ.ም. በአሜሪካ ከነበረው ሕዝብ የባሰ ድኃ ነበር? ወይ የእሚለውን ነው ።
ለእዚኽ ጥያቄ የአለው መልስ አሉታዊ ከሆነ ፤ በ13ኛው ምዕተ ዓመት በእንግሊዝ እና በ18ኛው ምዕተ ዓመት በአሜሪካ ሰፋሪዎች የሰራው ዴሞክራሲ ፤ ሌሎች ቅድመ ኹኔታዎች ከተሟሉለት ፤ በአፍሪካ ወይንም በአንዱ የዓለም ነዳያን ሐገር ፤ በእዚኽ ዘመን እንደ አይሰራ የሕዝብ ኢከነሚያዊ ድህነት ከልክሎታል ወይንም ይከለክለዋል የእሚለው ምክንያት ሊሆን አይችልም ማለት ነው ።
በአጭሩ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ፤ ከሌሎች መንግሥታዊ አወቃቀሮች በተለየ በአንድ ማሕበረሰብ ኢከነሚያዊ ደረጃ ላይ የእሚደገፍ አይደለም።
በአጠቃላይ እነ እዚኽን ዴሞክራሲን ለረዥም ዘመን አዳፍነው እና የማንሰራራቱንም ኺደት ፈታኝ አድርገው የቆዩ በዴሞክራሲ ላይ የእሚቀርቡ ትችቶች ስናያቸው ፤ ስህተታቸው ፤ የአልዳበረው የዴሞክራሲ ፅንሰ-ኃሳብ ላይ ማነጣጠራቸው እና በዴሞክራሲ ላይ ትችት የአቀረቡ ትልልቅ ሙህራንን ሊሳሳቱ እንደ እማይችሉ ፍፁም አዋቂያን አድርጎ ከመውሰድ የመጡ መኾናቸው ነው ።
የዴሞክራሲ ፅነሰ-ኃሳብ ፤ እንደ ማንኛውም ሳይንሳዊ ፅንሰ-ኃሳብ ፤ በአንድ ቦታ ማለትም በአቴንስ ይጀመር እንጂ ፤ በአግባቡ ዳብሮ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ እስኪ ደርስ የራሱን ዝግመት ኼዷል ።
በባሕር ላይ በመርከብ መንሳፈፍ ከዴሞክራሲ ቀድሞ የተገኘ የተፈጥሮ ሳይንስ ግኝት ነው ። የመጀመሪያ የመረከብ እሳቤ ፤ የዛሬው የመርከብ ቴክኖሎጂ ላይ እንዲ ደርስ ብዙ ፤ የማዳበሪያ ኺደቶችን አልፏል ።
ዴሞክራሲም እንደ እዚያው ነው ። ዴሞክራሲ በግሪክ ተጀመረ ማለት ፤ የግሪክ ዴሞክራሲ ብቸኛው እና እውነተኛው ዴሞክራሲ ነው ማለት አይደለም ።
ልክ የመጀመሪያውን መርከብ የሰራው ሰው ፤ በእርሱ የተጀመረው መርከብ ዛሬ የደረሰበትን ደረጃ ቢያይ እንደ እሚገረመው ፤ ክሌስተነስ ፣ ሶሎን ፣ ፕሌቶ ፣ አርስታትል ወይንም የመካከለኛው ዘመን ፈላስፎች የእሚባሉት እንደ ሞንተስኪው ያሉት ፈላስፎች ፤ እነርሱ ለመረዳት ሲታገሉት የነበረው ዴሞክራሲ ዛሬ የደረሰበትን ደረጃ ቢያዩ ፤ መገረማቸው አይቀርም ።
እነ እዚኽም ከላይ በዴሞክራሲ ላይ ሲቀርቡ የነበሩ ትችቶች ፤ በንፋስ የእሚገፋው ጥንታዊው መርከብን በማስረጃነት በማቅረብ ፤ መርከብ ለማዕበል እና ለእንግልት በማጋለጥ የተጓዦችን ሕይወትን እና ንብረትን ለጥፋት ይዳርጋል እና የሰው ልጅ ራሱንም ሆነ ቅፍለቱን በመርከብ ፤ በተለይ ውቂያኖስ አቋርጭ ጉዞ ማድረግ የለበትም ዓይነት ምክሮች ወይንም ትችቶች በመሆናቸው ፤ እናም ይኽ የመርከብ ጉዞ ክልከላ ዘመናዊዎቹን መርከቦች የእሚመለከት እንደ አልሆነ ፤ ከላይ የተዘረዘሩት በዴሞክራሲ ላይ የእሚቀርቡት ትችቶች ዘመናዊውን ወይንም የነፃነቱን ዴሞክራሲ የእሚመለከቱ አይደሉም ።
በአጠቃላይም ፦ ዘመናዊ ዴሞክራሲ በአሜሪካ በ18ኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻ አከባቢ ጀምሮ ፤ እንደ አሜሪካ በአለ ሰፊ ቦታ ላይ በሰፈረ ብዙ እና ብዝኃነት (Diversity) በአለው ሕዝብ መካከል ተተግብሮ ውጤታማነቱ በተግባር እስኪ ይታይ ድረስ ፤ በዴሞክራሲ ላይ በአብዛኛው የእሚሰነዘረው ትችት ፦ ዴሞክራሲ ማለት እንደ ባቢሎን ዓይነት ትርምስ የሰፈነበት እና ዓዕምሮቢስ መንጋ የእሚፈንጭበት የትርምስ ስረዓት ነው የእሚሉ ፤ እና በታሪክ ማስረጃነት ውኃ የእማይቋጥሩ ጸረ ዴሞክራሲ አስተሳሰቦች የነበሩ ናቸው ።
በሌላ አገላለፅ ፦ ዴሞክራሲ በነዳያን ሐገር አይሰራም ፣ ዴሞክራሲ የባህል እና የሞራል ልሽቀት ያስከትላል ፣ ዴሞክራሲ በነፃነት ስም ስረዓት አልበኝነትን ያስፋፋል ፣ ወዘተ ፤ የእሚሉ ትችት በእዚኽ ዘመን የእሚሰነዝር ሰው ፤ ይኽ ትችቱ ሊበራል ወይንም የነፃነት ዴሞክራሲን የእማይመለከት መሆኑን ሊያውቅ ይገባል ።
ያም ብቻ ሰአይሆን ፤ ፕሌቶን እና አርስታትልን ጨምሮ ፤ ማንኛውም ፈላስፋ ፤ የመጨረሻው የእውቀት እና የግንዛቤ ዳኛ ወይንም ጉልላት ተደርጎ መወሰድ የለበትም ። ምንም እንኳን ፤ ያልተሻረ ግንዛቤ ያስተዋወቁን አዋቂዎች በአይጠፉም ፤ አብዛኛው እውቀት ከግዜ እና ከኹኔታዎች ጋር እየተሻሻለ የእሚኼድ ነው ።
በእነ ክሌስተነስ ተጀምሮ ፤ ከፕሌቶ እስከ ሞንተስኪው በተለያዩ ሙህራን ተተችቶ ከእላይ በአየነው መልኩ ለርጅም ዘመናት ተዳፍኖ ከእዚያኽም ከአውሮፓ ሕዳሴ አንስቶ በእነ ሐሚልተን እና መሰሎቹ ዳብሮ ፤ በተግባር ውጤታማነቱን ያስመሰከረው የዛሬው ዴሞክራሲ ፤ የነፃነት ዴሞክራሲ ( Liberal Democracy ) ነው ማለት ነው ።
ዘመናዊውን ዴሞክራሲ ወይንም ሊበራል ዴሞክራሲን ፤ የመጀመሪያው ዴሞክራሲ የነበረበትን ውስንነት በመቅረፍ ፤ የዛሬውን መልክ እና አቋም እንዲይዝ የፅንሰ-ኃሳቡ አንኳር የሆኑት ፤ የእሚከተሉት ሦሥት ኃሳቦች ናቸው ፦
የተፈጥሮ መብት የእሚባለው ፤ የሰው ልጅ ተፈጥሮዋዊ ከሆነው ፤ በህይወት ከመቆየት ፍላጎቱ ተነስቶ ፤ ማንኛውንም ሰው በህይወት ለመኖር ያስፈልገኛል ብሎ የእሚያሰበውን ነገር ለማድረግ ፈቃድ ሳይጠይቅ ማድረግ የእሚችለውን ኹሉ ለማድረግ የአለው ተፈጥሮዋዊ ወይንም ሰዋዊ አቅም ወይንም ነፃነት ነው ። ይኽንን መብት ፤ ቶማስ ሆብስ እንደ እዚኽ ይገልፀዋል ፦
“የተፈጥሮ መብት ... እያንዳንዱ ሰው ተፈጥሮውን ፥ ማለትም ራሱን በህይወት ለማቆየት ፤ የራሱን ኃይል ለመጠቀም የአለው ነጻነት ነው ፤ በእዚኽም አግባብ ፥ በአዕምሮ ፍርዱ ይኽንን ዓላማ ለማሳካት የተሻለው መንገድ ነው ብሎ ያሰበውን ኹሉ መጠቀም ማለት ነው ።”
“The right of nature, ... is the liberty each man hath to use his own power as he will himself for the preservation of his own nature; that is to say, of his own life; and consequently, of doing anything which, in his own judgement and reason, he shall conceive to be the aptest means thereunto. [26]“
በሌላ አገላለጽ ፤ የተፈጥሮ መብት ማለት የሰው ልጅ የተፈጥሮ ነጻነት ነው ። ይኽም የተፈጥሮ ነጻነቱ ፤ የሰው ልጅ በተፈጥሮ በተጎናጸፈው ባሕሪው ፤ ህይወቱን ለማስቀጠል የትኛውንም የውጭ አካል ፈቃድ ሳይጠይቅ የእሚመስለውን የእሚያደርግበት ኹኔታ ወይንም ተፈጥሮዋዊ አቅም ማለት ነው ።
ይኽንኑ ተመሳሳይ ኃሳብ ፤ ሌላው የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪ ፤ ጆን ሎክ (John Locke) እንደ እዚኽ ይገልጸዋል ፦
“...በተፈጥሮ ሰው በሙሉ ፤ በተፈጥሮ ሕግ ብቻ እየተወሰነ ፤ ያም ማለት እርሱን ከእሚመስለው ሌላ ማንም ሰው ፈቃድ ሳይጠይቅ ወይንም በማንም ላይ ሳይደገፍ ፤ ያሻውን ተግባር ለመከወን ፍጽም ነጻነት አለው ፤ ንብረቱንም ይኹን ራሱን በአሻው እና ይገባል በእሚለው አግባብ ለማዋል ይችላል ።”
“...all men are naturally in, and that is, a state of perfect freedom to order their actions, and dispose of their possessions and persons as they think fit, within the bounds of the law of Nature, without asking leave or depending upon the will of any other man. [71]“
ይኽ በጆን ሎክ የተጠቀሰው እና የሰውን የተፈጥሮ ኹኔታ ወይንም መብት የእሚገድበው የተፈጥሮ ሕግ የተባለው ፤ ለሰው ልጅ የተፈጥሮዋዊ መብት ልክ ወይንም ገደብ የእሚያበጅለት ከተፈጥሮዋዊ ግንዛቤ የእሚመንጭ ስሌት ነው ።
ይኽ የተፈጥሮ ሕግ ፤ በግልፅ የተቀመጠ ሰአይሆን ፤ በአመክንዮ ወይንም በአዕምሮ የማመዛዘን ብቃት ወደ ብርኃን ወይንም ወደ መታወቅ የእሚመጣ ነው ።
ይኽ የተፈጥሮ ሕግ በዋናነት ኹለት ገጽታዎች አሉት ፤ እነርሱም ፦
ናቸው ።
ስለ እዚኽ ፦ የተፈጥሮ ሕግ ማለት ፤ በአዕምሮዋችን ፍርድ አመዛዝነን ፤ የእኛ ወይንም የሌሎች ሰዎች ፤ ተፈጥሮዋዊ መብት ወይንም ነፃነት ሕይወታችንን የእሚጠቅም እና ለአደጋ እንደ አይዳርገን የእምናደርግበት ፤ የተፈጥሮ መብት ወይንም የተፈጥሮ ነፃነት መግሪያ ነው ፦
“የተፈጥሮ ሕግ ... በዓዕምሮ ፍርድ የእሚገኝ ፥ የሰው ልጅ ህይወቴን ለጥፋት ይዳርጋል ወይንም ህይወቴን ለማቆየት የእሚያስፈልገውን ነገር ይነጥቃል የአለውን ነገር ከልክሎ ፤ ህይወቴን በተሻለ ኹኔታ ያቆይልኛል የእሚለውን መርጦ እንዲ ወስድ የእሚያዘው ፥ ብሒል ወይንም ትዕዛዝ ነው ።“
“A law of nature ... is a precept, or general rule, found out by reason, by which a man is forbidden to do that which is destructive of his life, or taketh away the means of preserving the same, and to omit that by which he thinketh it may be best preserved. [26]“
እነ እዚኽ ፤ ተፈጥሮዋዊ መብት እና ተፈጥሮዋዊ ሕግ የእሚባሉትን ፤ በአግባቡ ስንመለከት የእሚያጠነጥኑት ከሚዛናዊ የአዕምሮ ፍርድ ጋር ከእማይጋጨው ፤ የሰው ልጅ በህይወት የመቆየት ተፈጥሮዋዊ እና ቅጽበታዊ (Refelexive) ዝንባሌ ላይ መሆናቸውን እናያለን ።
ሰው የእሚያደርገውን ነገር በሙሉ ህይወቱን ለማስቀጠል ከእሚል ብኺል የእሚመንጭ መሆኑን እና ይኽም በህይወት የመኖር ተፈጥሮዋዊ ፍላጎት ፤ ሰው ይበጃል ብሎ ያሰበውን በማድረግ ወይንም በተፈጥሮዋዊ መብት የእሚረጋገጥ ሲሆን ፤ ይኽም ተፈጥሮዋዊ መብት ደግሞ ፤ በሰው አመዛዝኖ ወይንም የአዕምሮ ፍርድ እየተጋራ ወይንም በተፈጥሮ ሕግ እየተገዛ ተፈጥሮዋዊ መብታችን ራሳችንን ወይንም ሌላ ፍጥረት በእዚኽ የተፈጥሮ የመኖር ፍላጎታችን ላይ የህይወት አደጋ እንደ አያስከትል ይከላከላል ።
ስለ እዚኽ ፦ ሰው በህይወት የመኖር መሠረታዊ ፍላጎት አለው ፤ ይኽንንም ተፈጥሮዋዊ ፍላጎት ለማሳካት ተፈጥሮዋዊ መብቱ ወይንም አቅሙ በፈቀደው መልኩ ፤ ከማንም ፍቃድ ሳይጠይቅ ወይንም በማንም ላይ ሳይደገፍ እንዲንቀሳቀስ ተፈጥሮ ያጎናጸፈው መብት ወይንም አቅም አለ ፤ ይኽ መብት ግን ፤ እርሱም ራሱ በራሱ ላይ ጉዳት እንደ አያደርስ ወይንም ሌሎች በእርሱ ላይ ጉዳት እንደ አያደርሱ በዓዕምሮ ፍርድ ወይንም አመክንዮ እየተገራ ፤ የተፈጥሮ ሕግ ሆኖ ፤ የተፈጥሮ መብት እና የተፈጥሮ ሕግ የሰውን በህይወት የመቆየት ፍላጎት በጋራ እየሰሩ ያሳኩታል ።
ከላይ እንደ ተቀመጠው ፤ የዓዕምሮ ፍርድ ወይንም ሰዋዊ አመዛዝኖዋችን የእሚያስተምረን የተፈጥሮ ሕግ እንደ እሚያሳየን ፤ በህይወት የመኖር ፍላጎት ፣ የተፈጥሮዋዊ መብት ባለቤት የመሆን እና በተፈጥሮ ሕግ መገዛት የእኛ ብቻ ወይንም የአንድ ግለሰብ መብት ብቻ ሰአይሆን ፤ ኹሉም ሰዎች በጋራ የእሚጋሩት በመሆኑ ፤ ወይንም በተፈጥሮ የመኖር ፍላጎት፣ በተፈጥሮ መብት እና በተፈጥሮ ሕግ መገዛት የኹሉም ሰው ፤ እከሌ ከእከሌ ሳይባል ፤ ዘር ሳይቆጠር ፣ የቆዳ ቀለም ሳይታይ ፣ ወዘተ ፤ ሰው ኹሉ በእኩልነት የአለበት ደረጃ ነው ።
ይኽን ተፈጥሮዋዊ እኩልነት ቶማስ ሆብስም ጆን ሎክም በየእራሳቸው መንገድ እንደ እሚከተለው ያስቀምጡታል ፦
“ተፈጥሮ የሰውን ልጆች እኩል አዕምሮ እና አካል የእሚባል ነገር አድላቸዋለች ፤ ምንም እንኳን በግልጽ እንደ እሚታየው አንዳንዱ ሰው ከሌላው ሰው የላቀ የሰውነት ጥንካሬ ፥ አንዳንዱንም ከሌላው የላቀ የአዕምሮ ቅልጥፍና ያደለው ቢሆንም ፤ አካካሽ ነገሮችን ኹሉ ስናካትት ፤ በሰዎች መካከል የአለው ልዩነት ይኽ ነው የእሚባል አይደለም ፤ ከእዚኽም የተነሳ አንድ ሰው ለእኔ ይገባኛል የእሚለው ሌላው ሰው ለእኔ ይገባኛል የእማይለው ወይንም ሊል የእማይችለው ነገር የለም ። የአካል ጥንካሬን ብንወስድ ፤ በጥንካሬ ደካማ የእሚባለው ሰው ጠንካራ የእሚባለውን ሰው ለመግደል የእሚበቃ ጥንካሬ አለው ፤ በስውር አድብቶም ይኹን እንደ እርሱ ከተበደሉ ጋር ተባብሮ ይኽን ማድረግ ይችላል ።
የአዕምሮንም ጉዳይ በተመለከተ ፤ በንግግር ላይ የተመሠረቱትን ኪኖች ፡ በተለይ ደግሞ ከጠቅላላ እና ቋሚ ሕግጋት እውቀት የእሚመነጨውን ሳይንስን ፤ እንደ ህይወት ጥበብ ኑሮዋችንን ስንኖር የእምናዳብረው ነገር ሰአይሆን ሆን ብለን ግዜ አጥፍተን የእምናገኘው በመሆኑ ፤ የተወሰኑ ሰዎች በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ የአላቸውን እውቀት ወደ ጎን አድርገን ፤ የአዕምሮን ጉዳይ በተመለከተ ከአካላዊ ኹኔታ ይልቅ በሰዎች መካከል የበለጠ እኩልነት ያለ ይመስለኛል ። የህይወት ጥበብ የልምድ ጉዳይ ስለሆነ ፤ ሰዎች በተመሳሳይ ኹኔታ ውስጥ ለተመሳሳይ ግዜ ካሳላፉ የእሚያገኙት ነው ። ሰዎች በተፈጥሮዋዊ የአዕምሮ ጥበባቸው እኩል ናቸው ሲባል ፤ እውነት የእማይመስለው ብዙ ሰዎች ስለ ራሳቸው ጥበበኝነት ከአላቸው መኮፈስ የተነሳ ከተርታው ሰው የተሻለ ራሳቸውን ጥበበኛ አድርገው የማየት ዝንባሌ ስለ አላቸው ወይንም ከራሳቸው እይታ አንጻር በዝና የተለየ ጥበበኛ አድርገው የእሚያደንቋቸው ሰዎች በመኖራቸው ነው ።”
“Nature hath made men so equal in the faculties of body and mind as that, though there be found one man sometimes manifestly stronger in body or of quicker mind than another, yet when all is reckoned together the difference between man and man is not so considerable as that one man can thereupon claim to himself any benefit to which another may not pretend as well as he. For as to the strength of body, the weakest has strength enough to kill the strongest, either by secret machination or by confederacy with others that are in the same danger with himself.
And as to the faculties of the mind, setting aside the arts grounded upon words, and especially that skill of proceeding upon general and infallible rules, called science, which very few have and but in few things, as being not a native faculty born with us, nor attained, as prudence, while we look after somewhat else, I find yet a greater equality amongst men than that of strength. For prudence is but experience, which equal time equally bestows on all men in those things they equally apply themselves unto. That which may perhaps make such equality incredible is but a vain conceit of one’s own wisdom, which almost all men think they have in a greater degree than the vulgar; that is, than all men but themselves, and a few others, whom by fame, or for concurring with themselves, they approve. [26]“
የጆን ሎክ ኃሳብም ፤ የተቀመጠበት መንገድ ይለይ እንጂ ፤ ሰው በመሠረታዊነት እኩል ነው የእሚል ነው ። እንደ እሚታወቀው ፤ ሰው እኩል ነው ማለት ሰው ኹሉ አንድ ዓይነት ነው ማለት ሰአይሆን ፤ ሰውን ሰው ያስባለው ተክለ ሰውነት እና የአዕምሮ ብቃት ፤ ከእዚኽም የእሚመነጩት የተፈጥሮ መብቶች ፣ ሕግጋት እና ፍላጎቶች በሰው ዘር በሙሉ ተመሳሳይ ናቸው ማለት ነው ፦
“ይኽ ፤ የመሰለውን የማድረግ እና የመፍረድ ኹናቴ ፤ በሰዎች ዘንድ በእኩልነት ያለ ነው ። በእዚኽ ረገድ አንደኛው ሰው ከሌላው ሰው በተለየ ኹኔታ ያልታደለ መሆኑ ወይንም ተመሳሳይ ዝርያ እና ደረጃ የአላቸው ፍጥረታት ፤ ተመሳሳይ ተፈጥሯዋዊ መታደል እንደ አላቸው ግልጽ ነው ፤ ይኽም ፍጥረታቸው ተመሳሳይነት የአለው የአዕምሮ ብቃት በኹሉ ዘንድ አንዱ አንዱን እሚያስጎነብስ ወይንም የእሚያስገዛ በአልሆነበት ኹኔታ በእኩልነት ለኹሉም በተፈጥሮ መከፋፈሉ በግልጽ የእሚታይ ነው ።”
“A state also of equality, wherein all the power and jurisdiction is reciprocal, no one having more than another, there being nothing more evident than that creatures of the same species and rank, promiscuously born to all the same advantages of Nature, and the use of the same faculties, should also be equal one amongst another, without subordination or subjection. [71]“
እነ እዚኽ ተፈጥሮዋዊ ማንነቶች የእሚሰጡት መብት እና የተፈጥሮ ሕግ የእሚያስከትሉት ውስንነቶች ፤ የሰው ዘር በጋራ የእሚጋራቸው በመሆኑ ወይንም ተፈጥሮዋዊ ሰው ፤ በተፈጥሮ መብቱ ነጻ እና በእሚገዛበት የተፈጥሮ ሕግ እኩል መሆኑን ነው ፤ ከላይ የተቀመጡት ኃሳቦች የእሚያሳዩን ።
ይኽ በእኩልነት ሰዎች የእሚጋሩት ተፈጥሮዋዊ መብት እና የእሚገዙበት ተፈጥሮዋዊ ሕግ ፤ ሰዎችን ፥ ከላይ በሶስተኝነት በአስቀመጥነው የተፈጥሮ ኹኔታ የእሚባለው ውስጥ ይከትታቸዋል ።
ይኽም ተፈጥሮዋዊ ኹኔታ ፤ ሰው ህይወቱን ማቆየት በእሚለው ሰብዓዊ መርህ እየተነዳ ፤ የተፈጥሮ መብቱ የተፈጥሮን ሕግ በእማይጥስበት ኹኔታ ውስጥ እንዲኖር የማገናዘብ ኃይሉ ግድ የእሚለው ቢሆንም ፤ በአንድም በሌላ ምክንያት ፤ የተፈጥሮ ሕጉ በእማይከበርበት ግዜ ፤ የእሚፈጠረው አንዱ በአንዱ ላይ የመነሳት ወይንም የጦርነት ኹኔታ ነው ።
ይኽ ተፈጥሮዋዊ ኹኔታ የእሚያስከትለው ፤ የተፈጥሮ ሕግ የመጣስ አደጋ ፤ የሰዎችን ህይወት እና ንብረት ለአደጋ ስለ እሚያጋልጥ የውዴታ ግዴታ ፤ ሰው የተፈጥሮ ሕግ ነፀብራቅ የሆነውን ማሕበራዊ ውል (Social Contract) የእሚባለውን እንዲ ፈጥር ያደርገዋል ወይንም አድርጎታል ።
በግልጽ እና በቀላል ቋንቋ ፤ የተፈጥሮ መብት ፣ የተፈጥሮ ሕግ እና የተፈጥሮ ኹኔታ የእሚባሉትን ለማስቀመጥ ምሳሌ እንጠቀም።
ለምሳሌ ፦ አንድ ሰው ለመኖር መብላት አለበት ። የራበው ሰው ለመብላት ተፈጥሮዋዊ የሆነ መብት ወይንም ነፃነት አለው ፤ ይኽም ማለት ሰው ተፈጥሮ ያጎናፀፈችውን ለመኖር የመብላት ግዴታ እና ፍላጎት ለመተግበር የማንንም ፈቃድ ወይንም ይኹንታ ሳይጠይቅ የመፈፀም ተፈጥሮዋዊ መብት ፣ ነፃነት ወይንም አቅም አለው ። ተፈጥሮዋዊ መብቱ የሆነውን የመብላት መብቱን ለማስከበር ፦ ከእምናውቃቸው አማራጮች ሰርቶ ፣ ለምኖ ወይንም ሰርቆ መብላት ብለን ልናስቀምጥ እንችላለን ። ሰርቆ መብላት የእሚለውን አማራጭ እንደ አይከተል ፦ ምንም መንግሥት በሌለበት ኹኔታ ፤ እርሱ ለመብላት መስረቅ እችላለሁ ብሎ ከአሰበ ፤ ሌላውም ሰው እንደ እርሱው ለመብላት መስረቅ እችላለሁ ሊል እንደ እሚችል ብቻ ሰአይሆን ፤ ተሰራቂው ሰው ሊያጠቃው እንደ እሚችል ይገነዘባል ። ሰርቼ ነው መብላት የአለብኝ ብሎ ያሰበውም እንደ እዚኹ ፤ እርሱ ሰርቶ ያመጣውን ምግብ አንዱ ሰርቆ ሊወስድበት የእሚችል መሆኑን ስለ እሚገነዘብ ሰርቶ የአመጣውን ምግብ እንደ አይሰርቅበት እሚከላከልበት መንገድ ያስባል ።
ይኽ ኹኔታ ግን አንድ ሰው በተናጠል የእሚገኝበት ኹኔታ ሳይሆን ፤ ሰዎች ኹሉ ማሕበራዊ መስተጋብራቸውን የእሚዳኝ ስረዓት በሌለበት ወቅት ፤ እያንዳንዱ የማሕበረሰብ አባል የእሚገኝበት ኹኔታ በመሆኑ ፤ ኹሉም ሰው በስጋት እና በጥርጥር ውስጥ የእሚከት እና ሰዎች በቋሚነት ፤ ህይወታቸው እና ንብረታቸው ስጋት ውስጥ የአለበት ኹኔታ ነው ።
ሰው ያገናዝባል ማለት ፤ ግንዛቤውን አይተላለፍም ማለት አይደለም ።
ስለ እዚኽ አገናዛቢው ሰው ፦ የተፈጥሮ መብቱ ፤ በተፈጥሮ ሕግ ከአልተገራ ፤ የተፈጥሮ ኹኔታ ( State of nature or State of war) የእሚያስከትል መሆኑን ስለ እሚረዳ ፤ ይኽን የተፈጥሮ ኹኔታ ለማስወገድ ፤ የተፈጥሮ ሕጉን ወደ ተጻፈ ሕግ በመቀየር ፤ ማሕበራዊ ውል ( Social Contract) ውስጥ ይገባል ።
ሰውም ኹሉ በእኩልነት ይኽንን መብት እና የማሰብ ችሎታ የታደለ በመሆኑ እና የሰውም ሆነ የሰው የሆነው ነገር በሙሉ የእሚያጠነጥነው ሰውየውን በህይወት ማቆየት የእሚለውን ተፈጥሮዋዊ የሰው ፍላጎት በማሳካት ዙሪያ በመሆኑ ፤ የሰው ተፈጥሮዋዊ ኹኔታ ሰውን ወደ ማሕበራዊ ውል (Social Contract) እንዲ መጣ ያደርገዋል ።
ይኽ ፤ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ መብት እያከበረ ፤ ተፈጥሮዋዊ መብት ወይንም ነጻነት ደግሞ ወሰኑን ስቶ የሌሎችን ተፈጥሮዋዊ የመኖር መብት እንደ አይጋፋ እና የተፈጥሮ ኹኔታን እንደ አያስከትል የእሚያደርገው ፤ የተፈጥሮ ሕግ ነፀብራቅ የሆነው ፤ ማሕበራዊ ውል ነው።
ለምሳሌ ፦ የማሕበራዊ ዉሉ ፤ ምግብን በተመለከተ ፦ ምግብህን አምርተህ ወይንም ገዝተኽ ትበላለህ ፤ ይኽንን ገዝተኽ ወይንም አምርተህ የመብላት መብትህን ማንም ሊከለክልህ ወይንም አምርተህ ያስቀመጥኸውን ምግብ ወይንም በሕጋዊ መንገድ የአገኘውኸውን ምግብ መግዣ ገንዘብ ያለአንተ ፈቃድ ማንም ሊወስድብህ አይገባም ፤ አንተም የሌላውን ሰው አምርቶ ወይንም ገዝቶ የመብላት መብት ማደናቀፍ እና ያመረተውን ምግብ ወይንም በሕጋዊ መንገድ የአገኘውን የምግብ መግዣ ያለ ባለቤቱ ፈቃድ መንካት አትችልም ፤ የእሚል ዓይነት ይዘት ይኖረዋል ።
ስለ እዚኽ ሰው ፤ ተፈጥሮዋዊ የሆነውን ልቅ መብቱን በተፈጥሮ ሕግ ያስገዛዋል ወይንም ለራሱ ጥቅም ወይም ዋስትና ሲል ፤ እንደ ከራበህ ወይንም ከፈልግኽ ቀምተህም መብላት ትችላለህ ዓይነቶቹን ተፈጥሮዋዊ ኹኔታ የእሚያስከትሉትን የተፈጥሮዋዊ መብቶቹን ፤ “ሰርተህ በአገኘኸው ገንዘብ ገዝተኽ ወይንም አምርተኽ የመብላት መብትኽ በሕግ የተጠበቀ” በእሚሉ ዓይነት የአመዛዝኖ መብቶች ይተካቸዋል ።
ይኽንን ማሕበራዊ ውል እንደ ፖለቲካዊ ፍልስፍና አስተሳሰብ በማዳበር የእሚታወቁት ፤ ቶማስ ሆብስም ፣ ጆን ሎክ እና ዣን ዣክ ሩሶ ፤ ሰው ልቅ የሆነውን ተፈጥሮዋዊ መብቱን ለምን በተፈጥሮ ሕግ እንደ እሚገራ በእሚከተሉት መልኩ ያስቀምጡአቸዋል ፦
“ይኽ ሰው መብቱን (ተፈጥሮዋዊውን) የእሚተውበት እና የእሚያሸጋግርበት አግባብ መነሻ ሌላ ምንም ሰአይሆን ሰውየው ህይወቱ እና ህይወቱን ለማቆየት የእሚያስፈልጉት ነገሮች ከስጋት በፀዳ ኹኔታ ዋስትና እንዲ ያገኙ ከማሰብ ነው ። ... ይኽ የጋራ ተፈጥሮዋዊ መብትን አሳልፎ መስጠትን ሰዎች ማሕበራዊ ውል በማለት የእሚጠሩት ነገር ።”
“... The motive and end for which this renouncing and transferring of right is introduced is nothing else but the security of a man’s person, in his life, and in the means of so preserving life as not to be weary of it. ...The mutual transferring of right is that which men call contract [26].”
ጆን ሎክም ከእዚኽ ጋር ተመሳሳይነት የአለው ኃሳብ ፤ በተሻለ በተብራራ አኳኋን በእሚመለከተው መልኩ አስቀምጦታል ፦
“ የሰው ልጅ ፤ በተፈጥሮዋዊ ኹኔታው ውስጥ ፥ እንደ ተባለው ፤ ነፃ እና በራሱ ንብረት እና በህይወቱ ላይ ፍጹም ብቸኛ ጌታ ከሆነ ፤ ስለ ምን ሲባል ፥ ይኽንን ነጻነት ፥ ይኽንን ግዛት ፤ በመተው ራሱን ለሌላ አካል ቁጥጥር እና አገዛዝ ያጋልጣል ? ለእዚኽም ጥያቄ ቀላሉ እና ግልጽ የሆነው መልስ ፤ በእዚኽ የተፈጥሮ ኹኔታ ውስጥ ሰው ይኽን መሰል መብት ባለቤት ቢሆንም ፡ ይኽንን መብት የመጠቀም እድሉ ግን በቋሚነት ስጋት የአለበት መሆኑ እና ይኽም መብት በሌላ ሰው ሊገፈፍ የእሚችልበት አጋጣሚ ወይንም ተጋላጭነቱ ፤ ሌሎቹ ኹሉም ልከ እንደ እርሱ ባለ የንጉሥነት ደረጃ ላይ መገኘታቸው እና ኹሉም ሰው በእዚኽ ረገድ እኩል በመሆኑ ፤ ከእነ እዚኽም የእሚበዙቱ የእኩልነት እና የፍትሕ አክባሪ በአለ መሆናቸው ፤ በተፈጥሮዋዊ ኹኔታ ውስጥ የራሱ የሆነውን ነገር በደስታ ለመጠቀም አስተማማኝ ያለ መሆኑ እና የአለው የአደጋ ተጋላጭነት ከፍ ያለ በመሆኑ ነው ። ይኽም ሰዋዊ ተፈጥሮዋዊው ኹኔታ ምንም ነፃ ቢሆንም ፤ በፍርኃት የተሞላ እና ቋሚ አደጋ የተጋረጠበት በመሆኑ ፤ ይኽንን ኹኔታ በፈቃዱ ለመተው ፈቃደኛ ይሆናል ፤ ስለ እዚኽም ፦ ሰው እንዲያው በከንቱ አይደለም ፤ ከእዚኽ ቀደም የተቋቋመ ማሕበረሰብን ወይንም ከሰዎች ጋር ፤ ሰዎች ህይወታቸው ፥ ነጻነታቸው እና ንብረታቸው ፤ እኔ በጠቅላላው ንብረት (የእርሱ የሆነው ፤ ህይወት እና ንበረት) ብዬ የሰየምኩትን ፤ የእሚጠበቅበትን ማሕበር ለመቀላቀል ፈቃደኛ የእሚሆነው ።”
“If man in the state of Nature, be so free as has been said, if he be absolute lord of his own person and possessions, equal to the greatest and subject to nobody, why will he part with his freedom, this empire, and subject himself to the dominion and control of any other power? To which it is obvious to answer, that though in the state of Nature he hath such a right, yet the enjoyment of it is very uncertain and constantly exposed to the invasion of others; for all being kings as much as he, every man his equal, and the greater part no strict observers of equity and justice, the enjoyment of the property he has in this state is very unsafe, very insecure. This makes him willing to quit this condition which, however free, is full of fears and continual dangers; and it is not without reason that he seeks out and is willing to join in society with others who are already united, or have a mind to unite for the mutual preservation of their lives, liberties and estates, which I call by the general name—property. [71]“
ስለ እዚኽ ማሕበራዊ ውል ተመሳሳይ ሐሳብም በፈረንሳዩ ፤ ዣን ዣክ ሩሶ በእሚከተለው አግባብ ተቀምጦ እናያለን ፦
“አባላቱን እና ንብረታቸውን ከጉዳት የእሚጠብቅ አንድ ማሕበር መመሥረት ፤ ይኽንም በማድረግ ፤ እንደ ማሕበር አንድ ሆነው ሲተባበሩ ፤ ተፈጥሮዋዊ ነፃነታቸው ግን እንደ ተጠበቀ ሆኖ ራሳቸው የራሳቸው አለቃ ብቻ እንደ ሆኑ ይቀጥላሉ ።”
“Find a form of association that will bring the whole common force to bear on defending the protecting each associate's person and goods, doing this in such a way that each of them, while unitting himself with all, still obeys only himself and remains as free as before. [47]
“
እነ እዚኽ ከላይ ያስቀመጥናቸው ፤ በረጅሙ የሰው ልጅ የፖለቲካ ጉዞ እየዳበረ የመጣውን የዴሞክራሲያዊ መንግሥት አስተሳሰብ ፤ የመጨረሻውን ወይንም የማጠናቀቂያውን ሥራ የሰሩ ያልናቸው ኃሳቦች፤ ማለትም ፦
ስለ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በዋናነት የእሚመልሱት ፦
የእሚሉትን ጥያቄዎች ነው ።
ስለ እዚኽ ፦ በዴሞክራሲ ስነ መንግሥት ርዕዮት መንግሥት የእሚያስፈልገው ፤ የተፈጥሮ ወይንም የጦርነት ኹኔታ የእሚፈጥረውን ፤ የህይወት እና የንብረት ስጋት ለማስወገድ ነው ።
የመንግሥት የስልጣን ገደብም ፤ የዜጎች የተፈጥሮ መብት ወይንም ነፃነት ፤ የሌሎችን ዜጎች ህይወት እና ንብረት ለአደጋ በእማይዳርግ መልኩ ህይወታቸውን ለማስቀጠል እና ንብረት ለማፍራት በእሚመስላቸው መልክ መንቀሳቀስን መከልከል የእማይችልበት ድረስ ነው ።
መንግሥትም እነ እዚኽን ኹለት ረቂቅ የማመጣጠን ሥራ ፤ ማለትም ፦ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ መብት ወይንም ነፃነት አክብሮ ፤ የእነርሱ ነጻነት የሌሎችን ሰዎች ህይወት እና ንብረት አደጋ ላይ እንደ አይጥል እንደ እዚኹም የሌሎች ሰዎች ነጻነት የእነርሱን ህይወት እና ንብረት አደጋ ላይ እንደ አይጥል ፤ መከላከል የእሚችለው ወይንም አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት ማሳካት የእሚችለው ፤ ዜጎች በማሕበራዊ ውል አማካኝነት ህይወታቸውን እና ንብረታቸውን ከአደጋ የመከላከል ተፈጥሮዋዊ መብታቸውን በውክልና ለመንግሥት አሳልፈው ሲሰጡት እና መንግሥት የዜጎች በሙሉ ህይወት እና ንብረት ሕጋዊ ጠባቂ ሲሆን ነው ።
ይኽ ነው የዴሞክራሲያዊ መንግሥት አንኳር!
ሕገመንግሥት ወይንም ማሕበራዊ ውልም ፤ ዜጎች ተፈጥሮዋዊ ነፃነታቸውን ተጠቅመው ሲንቀሳቀሱ ፤ ተፈጥሮዋዊ ሕይወታቸውን እና ንብረታቸውን የመከላከል መብታቸው የሌሎችን ተፈጥሮዋዊ ሕይወትን እና ንብረትን የመከላከል መብት ጋር በማጋጨት ማሕበራዊ ቀውስ እንደ አያስከትል ፤ ዜጎች ህይወት እና ንብረታቸውን የመከላከላቸውን ተፈጥሮዋዊ መብት በጋራ ለመንግሥት አደራ የእሚሰጡበት አግባብ ነው ።
የዘመናዊ ፖለቲካዊ ፍልስፍና ፋና ወጊ የተባሉት ፤ እንደ ሆብስ ፣ ሎክ እና ሩሶ ያሉትን እውቅ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች ፤ የተፈጥሮ መብት ፣ የተፈጥሮ ኹኔታ እና የተፈጥሮ ሕግ የእሚባሉትን ኃሳቦች ፤ የማሕበራዊ ውል አዕማድ መሆናቸውን በጋራ ቢስማሙም ፤ ይኽ ማሕበራዊ ውል በማን እና በማን መካከል ሲደረግ ነው ፤ መንግሥት ይኽን የሕዝብ ሕይወት እና ንብረት ጠባቂነት ሚናውን በአግባቡ የእሚወጣው በእሚለው ላይ በኹለት ጎራ ተከፈለዋል ።
ቶማስ ሆብስ የአስተሳሰብ ጥራት በእሚጎድለው እና ከእራሱ ሌሎች አስተሳሰቦች ጋር በእሚጋጭ መልኩ ፤ በስልጣን ላይ ያለ ንጉሥ በአለበት ሐገራት ፤ የፖለቲካ ስልጣን የአለ አንዳች ዓይነት ስምምነት አይመጣም በእሚመስል አካኼድ ፤ ንጉሡ ፍጹማዊ ሆኖ የተፈጥሮ ሕግ ነጸብራቅ ከሆነው የማሕበራዊ ሕግ ውጭ አግባብ የዜጎችን ህይወት እና ንብረት ያለ አግባብ ቢነጥቅ እንኳን ፤ ሕዝብ ለምን ይኽን ታደርጋለኽ ብሎ ሊያምጽበት አይገባም ፤ ምክንያቱም ፦
የእሚሉ ምክንያቶች በማቅረብ ፤ ዜጎች እርስ በእርሳቸው ሳይሆን ከአንድ የሆነ መንግሥት ጋር የእሚያደርጉት ነው በእሚል የማሕበራዊ ውል መንግሥትን በመመሥረት ውስጥ የአለውን ፋይዳ በተዛባ መልኩ አስቀመጠው።
የቶማስ ሆብስ ኃሳብ ፤ ቀለል ባለ አገላለፅ ሲቀመጥ ፦ ማሕበራዊ ውሉ ዜጎች እርስ በእርሳቸው እንደ አይበዳደሉ እንጂ መንግሥት በሆነ አጋጣሚ ወይንም በስረዓታዊ ባሕሪ ዜጎችን እንደ አይበድል መከላከያ በአለ መሆኑ ፤ ዜጎች መንግሥት ቢበድላቸውም ፤ መንግሥትን በድለኸኛል ሊሉት አይችሉም የእሚል ሆነ ።
በሌላ በኩል ፤ ጆን ሎክ እና ዣን ዣክ ሩሶ ፤ አንድ ማሕበራዊ ውል የእሚከበረው ፤ ውሉ የተፈጥሮ ሕግ ነፀብራቅ በሆነ መልኩ የዜጎች ተፈጥሮዋዊ በህይወት የመኖር እና ሕይወታቸውን ከአደጋ የመጠበቅ ፍላጎታቸውን እስከ አሟላ ድረስ እንጂ ፤ ከእዚኽ ውጪ ሆኖ ህይወታቸውን እና ንብረታቸውን አደጋ ውስጥ የእሚያስገባ ከሆነ እና ሰዎች ሕይወታቸው እና ንብረታቸው አደጋ ውስጥ ከገባ ፤ ከተፈጥሮ ሕግ በፊት እንደ ነበሩበት ህይወት እና ንብረት ዋስትና የሌለበት የተፈጥሮ ወይንም የጦርነት ኹኔታ ውስጥ ስለ እሚመልሳቸው ፤ ተፈጥሮዋዊ የሆነ የመኖር ፍላጎት የአላቸው ሰዎች ፤ ይኽ ህይወታቸውን አደጋ ላይ የጣለው ግለሰብ ሆነ መንግሥት ላይ እንደ አያምፁ ሊያግዳቸው የእሚችል አዕምሮዋዊ ምክንያት አይኖርም በእሚል ከቶማስ ሆብስ ተለዩ ።
ስለ እዚኽ ፤ በቶማስ ሆብስ አካኼድ ፤ በተፈጥሮ ከአለንበት ኹኔታ ወይንም የተፈጥሮ ኹኔታ ከእሚጋርጥብን ተጋላጭነት እና ስጋት የእምንወጣው ፤ የተፈጥሮ ሕግ ነፀብራቅ የሆነ ውልን በማቆም እና ውልን አፍራሽ የእሚቀጣበትን አግባብ በመዘርጋት ነው ፤ ሆኖም ግን ይኽን የዜጎችን ህይወት እና ንብረት ከጉዳት እንዲከላከል የተሾመው ንጉሥ ከውሉ ግዴታ ነፃ ነው ወይንም መሆን አለበት የእሚል እና ፍፁማዊ የሆነ የመንግሥት ስልጣን የእሚያረጋግጥ መከራከሪያ አቅርቧል ።
በእዚኽም ምክንያት ፤ እንደ ቶማስ ሆብስ ኃሳብ ፦ በስልጣን ላይ ያለን መንግሥት ፤ የዜጎችን ህይወት እና ንብረት እንኳን አደጋ ላይ በእሚጥልበት ወቅት ፤ የተፈጥሮ ሕግን ተላልፈህ የዜጎችን ህይወት እና ንብረት አደጋ ላይ ጥለኃል ማለት ፤ በውል የተሰጠው ፍፁም ስልጣንን መጠየቅ ስለሆነ ህገወጥ ነው ፦
“ እናም በእዚኽ ምክንያት ፤ በዘውድ ስር ይኖሩ የነበሩ ሕዝብ ፤ ያለ ነጋሢው ፈቃድ ፦ ዘውዱን አውርደው ፤ ምንም ህብረት ወደ ሌለው መንጋ ግራ መጋባት መመለስ አይችሉም ፣ ወይንም ደግሞ ራሳቸውን በሌላ ንጉሥ ወይንም ማሕበር አስተዳደር ስር ለማድረግ ማስተላለፍ አይችሉም ፤ ምክንያቱም ፦ ከእዚኽ ቀደም በገቡት ውል ምክንያት ፥ ሉዓላዊ ንጉሳቸው ይገባል የእሚለውን ያድርግ የእሚለውን ሕግ ራሳቸው የተስማሙበት ስለ ሆነ ፤ በእዚኽም ፥ አንዳቸው እንኳን ይኽን ውል እምቢ ካሉ ፤ ኹሉም በጋራ ለዛ ሰው የገቡለትን ቃል እንደ አፈረሱ ያኽል በመሆኑ ኢፍትኃዊ ነው ፤ በተመሳሳይም እያንዳንዳቸው ነጋሢውን በእነርሱ ላይ ሉዓላዊ እንዲሆን ስለ አደረጉት ፤ ቢያወርዱት በውል የእርሱ የሆነውን ነገር እየወሰዱበት በመሆኑ ይኽም ኢፍትኃዊ ነው ። በተጨማሪም ፤ ነጋሢውን ለማውረድ የእሚሞክር ሰው ፤ በእዚኽ ሙከራው ምክንያት ቢገደል ወይንም ቢቀጣ ፤ በራሱ ላይ ይኽን ቅጣት የአመጣው ራሱ ነው ፤ ምክንያቱም ፦ ነጋሢው ልክ ነው ብሎ የእሚያስበውን ኹሉ እንዲ ያደርግ ለነጋሢው የሰጠው ራሱ በመሆኑ ፤ በተጨማሪም ራሱ ልክ አይደለም ብሎ ሰውን የእሚቀጣበትን ነገር የእሚያደርግ ሰው ኢፍትኃዊ በመሆኑ ፤ በእዚኽም ፍትሕ አልባ መሆኑ ይታያል ።”
“And therefore, they that are subjects to a monarch cannot without his leave cast off monarchy and return to the confusion of a disunited multitude; nor transfer their person from him that beareth it to another man, other assembly of men: for they are bound, every man to every man, to own and be reputed author of all that already is their sovereign shall do and judge fit to be done; so that any one man dissenting, all the rest should break their covenant made to that man, which is injustice: and they have also every man given the sovereignty to him that beareth their person; and therefore if they depose him, they take from him that which is his own, and so again it is injustice. Besides, if he that attempteth to depose his sovereign be killed or punished by him for such attempt, he is author of his own punishment, as being, by the institution, author of all his sovereign shall do; and because it is injustice for a man to do anything for which he may be punished by his own authority, he is also upon that title unjust [26].”
ጆን ሎክ ከእዚኽ ተጻጻሪ በመቆም ፤ የመሐበራዊ ውል ዋነኛ ዓላማው ፤ የተፈጥሮ ኹኔታ የእሚደቅነውን አደጋ መከላከል ከሆነ እና የተፈጥሮው ኹኔታ የእሚጋርጠውን አደጋ መከላከል ደግሞ ከሰው ሰብዓዊ በኃሪ የእሚመነጭ ከሆነ ፤ ማለትም ፦ ዜጎች በተናጠልም ሆነ በጋራ የተፈጥሮን ሕግን ሆን ብለውም ሆነ በስህተት ተላልፈው የሌሎችን ዜጎች ህይወት እና ንብረት አደጋ ላይ ሊጥሉ የእሚችሉበትን ኹኔታ መከላከል ከሆነ ፤ ዜጎች ብቻ ሰአይሆን መንግሥት ራሱ (መንግሥት የእሚሆኑት ወይንም የመንግሥት ስልጣን የእሚይዙት ራሳቸው ሰዎች ስለ ሆኑ) በተፈጥሮ ሕግ ወይንም በማሕበራዊ ውል ሳይገዛ ፤ በግብታዊነት ይኹን በሌላ ፤ የዜጎችን ህይወት እና ንብረት አደጋ ላይ የእሚጥል ከሆነ ፤ ማሕበረሰብ ተመልሶ ህይወት እና ንብረት ዋስትና የሌለበት ኹኔታ ውስጥ የእሚመለስ በመሆኑ ፤ መንግሥትም ለተፈጥሮ ሕጉ ወይንም ለማሕበራዊ ውሉ መገዛት አለበት ይላል ፦
“ብዙም ሳልጨነቅ ፤ በተፈጥሮ ኹኔታ ለእሚፈጠረው መስተጓገል መፍትኼው ሕዝባዊ መንግሥት መሆኑን አውቃለሁ ፤ ምክንያቱም ፦ ሰው ዜጋ ሆኖ በእሚኖርበት ግዜ ጎረቤቱን ለመበደል ይችላል ብለን ከአልን ፤ ስልጣን ሲይዝ ደግሞ የበለጠ ለራሱ ሊያደላ እንደ እሚችል መገመት ቀላል ነው ። ይኽንን መቃወም የእሚፈልጉ ሰዎች አንድ እንዲ ያስታውሱ የእምፈልገው ነገር ፤ ፍፅማዊ ነገሥታቶች ራሳቸው ሰዎች እንደ ሆኑ እና መንግሥትም የእሚያስፈልገው ሰዎች የራሳቸው አዛዥ በእሚሆኑበት ግዜ የእሚፈጠረውን ችግር ለማስቀረት ከሆነ ፤ ያም ማለት የተፈጥሮ ኹኔታ ልንገኝበት የእማይገባ መጥፎ ኹኔታ ከሆነ ፤ የፍፁማዊ ነገሥታቱ መንግሥት ምን ዓይነት መንግሥት እንደ ሆነ እና አንድ በሕዝብ ላይ የእሚያዝ ግለሰብ የራሱ ጉዳይ ላይ እንዲ ያዝ ልዩ መብት ሲሰጠው እና ያለ ምንም ተጠያቂነት በሕዝብ ላይ ያሻውን ብይን ማስተላለፍ የእሚችል ከሆነ ፤ ይኽ ከተፈጥሮ ኹኔታም በምን ሊሻል እንደ እሚችል እንዲ ያስረዱኝ እፈልጋለሁ ? እናም ይኽ ነጋሢ ተሳስቶም ይኹን ፣ ምክንያታዊም ሆኖ ወይንም በግዜያዊ ስሜት ተገፋፍቶ የእሚያድርገው ነገር በሙሉ ፤ ሕዝብ ምንም ሳይጠይቅ መታዘዝ አለበት ? ይኽንን ግን ሰዎች በተፈጥሮ ኹኔታ ውስጥ ሆነው አንድአቸው በአንድአቸው ላይ ሊያደርጉት አይችሉም እንላለን ? በፍርድ ወንበር ላይ የእሚቀመጥ ማንም ፤ በራሱም ጉዳይ ይኹን ወይንም በሌላ ሰው ላይ ፤ በፍርድ ቢስት ፤ መላው የሰው ልጅ ይጠይቀዋል … ምክንያቱም ፦ ኹሉም ዓይነት ስምምነት አይደለም ፤ በሰዎች መካከል የአለውን የተፈጥሮ ኹኔታ የእሚያስቆመው ፤ ነገር ግን ኹሉም በጋራ ከኹሉም ጋር አንድ ማሕበረሰብ በመሆን አንድ ሐገር የእሚፈጥሩበት እንጂ ፤ ከእዛኽ ውጭ ያሉት ሰዎች የእሚገቡባቸው ተስፋዎች እና ውሎች ፤ መልሰው የተፈጥሮ ኹኔታ ውስጥ ነው የእሚያመጡዋቸው ።”
“I easily grant that civil government is the proper remedy for the inconveniences of the state of Nature, which must certainly be great where men may be judges in their own case, since it is easy to be imagined that he who was so unjust as to do his brother an injury will scarce be so just as to condemn himself for it. But I shall desire those who make this objection to remember that absolute monarchs are but men; and if government is to be the remedy of those evils which necessarily follow from men being judges in their own cases, and the state of Nature is therefore not to be endured, I desire to know what kind of government that is, and how much better it is than the state of Nature, where one man commanding a multitude has the liberty to be judge in his own case, and may do to all his subjects whatever he pleases without the least question or control of those who execute his pleasure? And in whatsoever he doth, whether led by reason, mistake, or passion, must be submitted to? Which men in the state of Nature are not bound to do one to another? And if he that judges, judges amiss in his own or any other case, he is answerable for it to the rest of mankind...for it is not every compact that puts an end to the state of Nature between men, but only this one of agreeing together mutually to enter into one community, and make one body politic; other promises and compacts men may make one with another, and yet still be in the state of Nature. [71]“
በተቃራኒ ሆብስ መንግሥት ወይንም ልዕሉ (The Sovereign) ከሕግ ወይንም ከማሕበራዊ ውሉ በላይ በመሆኑ ፤ ያለ ሕግ አግባብ እንኳን የሰው ህይወት ቢቀማ በወንጀል እንደ እማይጠየቅ ለማሳየት የእሚከተለውን ብሏል ፦
“በእዚኽም ፤ ንጉሡ በህይወት እና በሞት ላይ የአለው ሉዓላዊ ስልጣን እንደ ተሻረ ወይንም እንደ ተገደበ መቁጠር የለብንም ። ምክንያቱም ፦ ሉዓላዊ ነጋሢው በሕዝቡ ላይ ፤ በምንም ምክንያት የእሚያደርገው ማንኛውም ነገር ኢፍትኃዊ ሊባል እንደ እማይችል አሳይተናል ፤ በእዚኽ ረገድ ብቸኛ የአለበት ገደብ ፤ ራሱም ከእግዚአብሔር ስልጣን በታች በመሆኑ ፤ ለተፈጥሮ ሕግ የመግዛት ግዴታ ብቻ ነው የአለበት ። እናም ፤ ስለ እዚኽ ፦ ማንም በጥፋት ሳይከሰስ ፤ በነገሥታት ሐገር በነገሥታቱ ትዕዛዝ ዜጎች በሉዓላዊው ነጋሢ በሞት ሊቀጡ ይችላሉ ወይንም ይቀጣሉ ፤ ልክ ዮፍታኼ[3] ልጁን እንደ ሰዋት ። በእዚኽ ታሪክ ፤ ሞት የተፈረደበት እምቢ ማለት ቢችልም ፤ ምንም ሳይቃወም የሞት ፅዋውን ተቀብሏል ። በተመሳሳይ ምሳሌ ፤ ወንጀል የሌለበትን ዜጋውን ልዑሉ መግደል ይችላል ። ምንም እንኳን ተግባሩ የተፈጥሮውን ሕግ የእሚጻረር ሕግ እንደ መሆኑ ኢፍትኃዊ ቢሆንም (ልክ ዳዊት ኦርዮንን እንደ ገደለው[4] ) ፤ የንጉሡ ጥፋት በእግዚአብሔር ላይ የተፈፀመ እንጂ በኦርዮን ላይ የተፈፀመ ጥፋት አልነበረም ።”
ጆን ሎክ ይኽንን የቶማስ ሆብስ የአምባገነን ጽንፈኝነት በመቃወም እና ለሰው ልጅ ነጻነት በመቆም ፤ ሕገመንግሥት የተፈጥሮን ሕግ ካለ አንፀባረቀ ወይንም ዴሞክራሲያዊ ከአልሆነ ፤ በዛ ስረዓት ውስጥ የእሚኖሩ ግለሰቦችም ሆኑ ሕዝብ ይኽንን ሕግ አንቀበለም የማለት ተፈጥሮዋዊ የመብት ግዴታ አለባቸው ፤ ብሎ ምክንያታዊ እና ትክክለኛ ኃሳብ አቅርቧል ፦
“ሕግ አውጭው ፤ ለአንድ ሰው ወይንም ለብዙ ሰዎች የተሰጠ ይኹን ፣ ስልጣኑ የህይወት ዘመን ይኹን በግዜ የተገደበ ፣ ወይንም በሐገሪቱ ውስጥ ያለ የመጨረሻው የስልጣን አካል ቢሆንም እንኳን ፤ በመጀመሪያ እና መጀመሪያ በሰዎች ህይወት እና ንብረት ላይ ፍፁማዊ ዘፈቀደ መሆን አይችልም ። ምክንያቱም ፦ ለአንድም ይኹን ለብዙ ሰዎች የእሚሰጠው ይኽ ስልጣን ፤ እያንዳንዱ ሰው ወደ ማሕበረሰብ ውስጥ ከመቀላቀሉ በፊት ፤ በተፈጥሮ ኹኔታ ውስጥ እያለ የነበረው ስልጣን ፤ በጋራ ተደማምሮ የተላለፈ በመሆኑ ፤ ከማሕበረሰቡ አባላት ተፈጥሮዋዊ ስልጣን ሊበልጥ አይችልም ። ምክንያቱም ፦ ማንም ሰው ከአለ፟ው ስልጣን በላይ ለሌላ ሰው ሊሰጥ አይችልም ፤ ማንም ሰው ደግሞ የራሱን ህይወት በፈለገው ሰዓት የማጥፋትም ሆነ የሌላውን ሰው ህይወት እና ንብረት የመቀማት የዘፈቀደ ስልጣን የለውም ፤ ሕጋዊ በአለ ስልጣኑም ከእዚኽ የአለፈ ስልጣን ሊኖረው አይችልም ። ስልጣናቸውም የማሕበራዊ እድገት ከማስመዝገብ የአለፈ ግብ ሊኖረው አይችልም ። የደህንነት ዋስትንና ከማረጋገጥ የአለፈ ስልጣንም አይደለም ፤ ስለ እዚኽ ነዋሪዎቹን የማጥፋት ፣ ባሪያ የማድረግ ወይንም የማደህየት እቅድ የአለው ሊሆን አይችልም ፤ ማሕበረሰብ ውስጥ የተፈጥሮ ሕግ መሥራት አያቆምም ፤ ነገር ግን የማሕበሩ ሕግጋት ከእርሱ ጋር በተቻለ መጠን እንዲ-መሳሰሉ ይደረጋሉ እንጂ ፤ ከእዚኽም የተነሳ በተጻፉ የሰዎች ሕግ ፤ የተፈጥሮ ሕጉ እንዲከበር ግልፅ ቅጣት ይደነገጋሉ ፤ እንዲ ከበሩ ። ስለ እዚኽ ፦ የሰው ልጆች የዘላለም ሕግ ሆነው ይኖራሉ ፤ ለሕጋዊ ባለ ስልጣኖች ይኹን ለነዋሪዎቹ ። ለሌላ ሰዎች የእሚወጣው ሕግ ፤ በአውጭውም ላይ ተፈፃሚ በእሚሆንበት ግዜ የእማይጎረብጣቸው መሆን አለበት ፤ ይኽም ከተፈጥሮ ሕግ ጋር የእሚስማማ መሆን አለበት ።”
“Though the legislative, whether placed in one or more, whether it be always in being or only by intervals, though it be the supreme power in every commonwealth, yet, first, it is not, nor can possibly be, absolutely arbitrary over the lives and fortunes of the people. For it being but the joint power of every member of the society given up to that person or assembly which is legislator, it can be no more than those persons had in a state of Nature before they entered into society, and gave it up to the community. For nobody can transfer to another more power than he has in himself, and nobody has an absolute arbitrary power over himself, or over any other, to destroy his own life, or take away the life or property of another. A man, as has been proved, cannot subject himself to the arbitrary power of another; and having, in the state of Nature, no arbitrary power over the life, liberty, or possession of another, but only so much as the law of Nature gave him for the preservation of himself and the rest of mankind, this is all he doth, or can give up to the commonwealth, and by it to the legislative power, so that the legislative can have no more than this. Their power in the utmost bounds of it is limited to the public good of the society. It is a power that hath no other end but preservation, and therefore can never have a right to destroy, enslave, or designedly to impoverish the subjects; the obligations of the law of Nature cease not in society, but only in many cases are drawn closer, and have, by human laws, known penalties annexed to them to enforce their observation. Thus the law of Nature stands as an eternal rule to all men, legislators as well as others. The rules that they make for, other men’s actions must, as well as their own and other men’s actions, be conformable to the law of Nature. [71]“
በእዚኽም መሠረት ፤ ጆን ሎክ እንደ እሚለው ፤ ይኽንን ከተፈጥሮ መብት የእሚመነጭ ስረዓት አልበኝነት የእሚከላከለውን ሕግ ወይንም ዴሞክራሲ ተጻሮ ፤ በስልጣን ላይ ያለ መንግሥት በዜጎች ህይወት እና ንብረት ላይ አደጋ ከጋረጠ ወይንም የተፈጥሮ ሕግን ከሻረ ፤ ራሱ አመፀኛ በመሆን ፤ በአመፅ እንዲ ወገድ ዴሞክራሲን አስወግዶ የተፈጥሮን ራስን የመከላከል ሕግ ወደ ስፍራው ስለ መለሰ ፤ በጉልበት ከስልጣን ቢወገድ ተገቢ ነው ወይንም ይኽን አመክኖያዊ ድምዳሜ ማስከተሉ አይቀርም ።
ይኽን ማለት ወይንም ሕዝብ የተፈጥሮን ሕግ የእሚጥስ መንግሥት ሲመጣ ግልጽ የሆነ አመጽ አድርጎ መንግሥትን ወይንም አማፂውን መንግሥት ማስወገድ አለበት ሲባል ፤ እንደ ሎክ እምነት ፤ አንዳንድ ሰዎች እንደ እሚመስላቸው ሕዝብን ለዓመፅ ማነሳሳት አይደለም ፤ እንዲያውም በባሕሪው ሕዝብ ፖለቲካዊ ለውጦችን እና ኺደቶች በነጻነቱ እና በኑሮው ላይ የእሚያመጡት አሉታዊ ተጽኖ ቶሎ ስለ እማይታየው ፤ እጅግ የመረረ ነገር ከአልገጠው ወደ አመጽ አይኼድም ።
ስለ እዚኽ ፦ ሕዝብ ህልውናው አደጋ ውስጥ ሲገባ ማመፅ መብቱ ነው ማለት ለዓመጽ አያነሳሳውም ፤ ይኽም በመሆኑ አንድ መንግሥት የዜጎችን ህይወት እና ንብረት ለአደጋ የመዳረግ አካኼድ በስረዓታዊ በኃሪ ደረጃ ከአንጸባረቀ ፤ በኃይል ቢወገድ ተገቢ ነው የእሚለውን አባባል ፤ አንድ የፖለቲካ መኃንዲስ እንደ እሚያስቀምጠው አመክንዮዋዊ መላምት እንጂ እንደ ተራ አመጽ ማነሳሻ ወይንም መቀስቀሻ ስልት ተደርጎ መታየት የለበትም።
በሌላ አገላለጽ ፤ መንግሥት በባሕሪ እና በፕሮግራም ደረጃ ፤ የተፈጥሮ ሕግ ነጸብራቅ የሆነውን ሕግ ፤ ተጻሮ ከቆመ ወይንም ከላይ ቶማስ ሆብስ እንደ እሚለው ዓይነት ፤ መንግሥት ነኝ እና እኔን የእሚጠይቀኝ እግዚአብሔር እንጂ ለተፈጥሮ ሕግ አልገዛም ከአለ ፤ ራሱ ጦርነትን ጋብዟል እና በእዚኽ የተበደለ ሕዝብ በጦርነት ወይንም በኃይል ቢያስወግደው መብቱ ነው ። ቢሆንም ግን መንግሥት በቋሚነት ወይንም መሠረታዊውን የተፈጥሮ ሕግ በመሻር የጭቆና እና የበደል ኃይል በቋሚነት ከአልሆነ ፤ እዚኽም እዚያኽም በእሚፈጠሩት የመንግሥት ክፍተቶች ፤ ማመጽ ብዙም ጥቅም የለውም ፤ በዘመናዊ ቋንቋ ፤ ከመረበሽ ሱስ የእሚመጣ ፤ ድንጋይ ወርውሮ መስታወት ከመስበር የእማይዘል አመጽ ፤ ማሕበራዊ ኪሳራው ይበልጣል ።
በአጠቃላይ ጆን ሎክ ፤ መንግሥት ግን የተፈጥሮን ሕግ ነጸብራቅ ፤ ዴሞክራሲን ከሻረ እና ከቀየረ ፤ በጉልበት መወገዱ ተፈጥሮዋዊ ራስን የመከላከል መብት አካል ነው ይላል ።
በአጭር አገላለጽ ፤ ሉዓላዊ መንግሥት የለም ፤ ሉዓላዊ ሕዝብ ነው የአለው ።
መንግሥት የእሚከበረው የሕዝብን ሉዓላዊነት አክብሮ እርሱን ለማስከበር እስከ ቆመ ነው ፤ ይኽንን የሕዝብን ሉዓላዊነት ማክበር ያቆመ ቀን እና ይኽንንም በባሕሪ ደረጃ ከአንጸባረቀ ፤ መከበሩ ይቀር እና ሕገ ወጥ ይሆናል ፦
“ ነገር ግን ፤ ረዥም የመብት ረገጣ ሰንሰለት እና ተለዋዋጭ ማታለያዎች ፤ ሕዝቡ ሊረዳ በእሚችልበት መልኩ እና ከእይታቸው ሊሰወር በእማይችልበት ኹኔታ ከቀጠሉ ፤ የመንግሥትን ስልጣን በመጀመሪያ በታቀደው መሠረት ማስኬድ ለእሚችለው ሰው ለመስጠት በአመፅ ቢነሱ ብዙም ሊያስገርመን አይገባም ፤ ያ በአይሆን ኖሮ በጥንታዊ ስምምነት እያብለጨለጩ የእሚኖሩት መንግሥታት ፤ ከተፈጥሮ ኹኔታ ወይንም ከስረዓት አልበኝነት በላይ ወይንም በተነፃፃሪነት የከፉ እና መፍትኼውም እጅግ የራቀ እና ፈታኝ ይሆን ነበር ።”
“But if a long train of abuses, prevarications, and artifices, all tending the same way, make the design visible to the people, and they cannot but feel what they lie under, and see whether they are going, it is not to be wondered that they should then rouse themselves, and endeavor to put the rule into such hands which may secure to them the ends for which government was at first erected, and without which, ancient names and specious forms are so far from being better, that they are much worse than the state of Nature or pure anarchy; the inconveniencies being all as great and as near, but the remedy farther off and more difficult. [71]“
በሌላ ስፍራ ላይም እንደ እዚኽ ብሏል ፦
“ሰዎች የአንድ መሐበረሰብ አባል የእሚሆኑበት ምክንያት የንብረት ጥበቃ ለማግኘት ነው ፤ ሲፈልጉ ሕጋዊ ስልጣን የእሚያቋቁምበትም ዓላማ ፤ የማሕበረሰብን ኹሉን ንብረት አጥር ሆነው የእሚጠብቁ ሕግ እና ደንቦች እንዲ ደነገጉ ነው ፤ በእዚኽም በማሕበረሰብ ውስጥ የአለው እያንዳንዳንዱ ሰው የአለውን ስልጣን ለመገደብ እና ለማለዘብ ነው ። ምክንያቱም ፦ ሰዎች ወደ ማሕበረስቡ የእሚገቡበት ምክንያት የሆነው ከለላ የማግኘት ፍላጎት ማሳጣት የአንድ ማሕበረሰብ ግቡ ሊሆን ስለ እማይችል እና ሰዎችም የእዚኽ ዓይነቱ ማሕበራዊ ከለላ ለእሚሰጣቸው ሕጋዊ ስልጣን ነው ራሳቸውን የእሚያስገዙት ፡ ስለ እዚኽ ፦ አንድ ሕግ አውጪ የሕዝቡን ንብረት ሊቀማ እና ሊያጠፋ ሲነሳ ፤ ወይንም በዘፈቀደ በባርነት ስር ሊያደርጋቸው ሲፈልግ ፤ ሕዝቡ እንደ እነርሱ ከተበደለው ጋር በማበር ራሳቸውን ከበዳዩ ነፃ በማውጣት የጦርነት ኹኔታ ውስጥ ያስገባሉ ፤ በእዚኽም እግዚአብሔር ሰዎች ራሳቸውን ከአመፅ ለመከላከል ወደ አዘጋጀላቸው ምሽግ ይገባሉ ። ስለ እዚኽ ፦ መቼም ቢሆን ፤ ሕጋዊ ስልጣን የአላቸው አካላት የማሕበረሰብን መሠረታዊ ሕግ ፤ በጀብደኝነት ፣ በፍርኃት ፣ በሞኝነት ወይንም በሙስና ሲተላለፉ እና ለእራሳቸው ወይንም በውክልና ለሌላ አካል ፤ በዜጎች ህይወት ፣ ነፃነት እና ንብረት ላይ የፈለጉትን ለማድረግ አምባገነን ሲሆኑ ፤ ይኽን በማድረጋቸው ሕዝብ በፈቃዱ የሰጣቸውን ስልጣን እንደ ተውት ይቆጠርና ፤ ሕዝቡ ወደ መጀመሪያው ተፈጥሮዋዊ ነፃነቱ ተመልሶ ፤ የደህንነት ዋስትና የእሚሰጥ አዲስ ሕጋዊ ስልጣን (ይገባል ብሎ በእሚለው መልኩ) ያቋቁማል ፤ መጀመሪያዉንም የማሕበረሰብ አካላት የሆኑት ለእዚኹ በመሆኑ ።”
“The reason why men enter into society is the preservation of their property; and the end while they choose and authorize a legislative is that there may be laws made, and rules set, as guards and fences to the properties of all the society, to limit the power and moderate the dominion of every part and member of the society. For since it can never be supposed to be the will of the society that the legislative should have a power to destroy that which everyone designs to secure by entering into society, and for which the people submitted themselves to legislators of their own making: whenever the legislators endeavor to take away and destroy the property of the people, or to reduce them to slavery under arbitrary power, they put themselves into a state of war with the people, who are thereupon absolved from any farther obedience, and are left to the common refuge which God hath provided for all men against force and violence. Whensoever, therefore, the legislative shall transgress this fundamental rule of society, and either by ambition, fear, folly, or corruption, endeavor to grasp themselves, or put into the hands of any other, an absolute power over the lives, liberties, and estates of the people, by this breach of trust they forfeit the power the people had put into their hands for quite contrary ends, and it devolves to the people, who have a right to resume their original liberty, and by the establishment of a new legislative (such as they shall think fit), provide for their own safety and security, which is the end for which they are in society. [71]“
ሉዓላዊው የእሚለው ወይንም የዘውድ ንጉሥ ፤ በሕዝቡ ላይ የፈለገውን ነገር ማድረግ ይችላል ፤ የተፈጥሮን ሕግንም የእሚጻረር ነገር ቢሆን ፤ ምክንያቱም ፦ የእርሱ ተጠያቂነት ለእግዚአብሔር ብቻ ነው ፤ ይኽንንም ሉዓላዊነቱን በውል አግኝቶቷል እንደ ገናም ዜጎች ከማሕበራዊ ውል መከበር የእሚያገኙትን ጥቅም የእሚያገኙት የማሕበራዊ ውሉን ተፈፃሚነት የእሚቆጣጠር ፍፁማዊ ባለ ስልጣን ሲኖር ነው ብሎ የእሚከራከረው ሆብስ ግን ፤ ይኽንን ፍጹም ስህተት እና ጭፍን የሆነ ድምዳሜ ላይ ከመድረሱ በፊት ፤ ሰው በቅድሚያ ሰላምን ይፈልጋል ፤ ይኽ ከአልተሳካለት ግን ህይወቱን እና ንብረቱን በሰላም ማስጠበቅ ከአልቻለ ፤ በጦርነት ለማስጠበቅ መኼዱ ፤ ተፈጥሮዋዊ ወይንም ከአዕምሮ የተመዛዘነ ፍርድ የእሚመነጭ ነው ሲል የነበረ ነው ፦
“ይኽንም ተከትሎ ፤ የተባለ ፥ ጠቅላላ ተቀባይነት የአለው ምክንያታዊነት ነው ፤ የማግኘቱ ተስፋ እስከ አለ ድረስ ፤ ሰው ኹሉ ሰላምን ለማግኘት መጣር አለበት ፤ በእዚኽ መልኩ ፈልጎ ሰላምን ሊያገኘው ከአልቻለ ግን ጦርነት የእሚሰጠውን እርዳታ እና ጥቅም መፈለግ አለበት ።”
“And consequently, it is a precept, or general rule of reason: that every man ought to endeavor peace, as far as he has hope of obtaining it; and when he cannot obtain it, that he may seek and use all helps and advantages of war [26].”
በሌላ አገለላጽ ፤ በስምምነት አንድ ግዜ መብትህን አሳልፈህ ሰጥተኃል ወይንም የእሚፈ፟ራ ንጉሥ በሌለበት ማሕበራዊ ውል በሕዝብ አይከበርም ፤ ስለ እዚኽ ብትረገጥም ዝም በል የእሚለው ሆብስ ፤ ከራሱ ጋር በእሚቃረን መልኩ ፤ ሰላምን ፈልጎ ያጣ ሰው ፤ በጦርነት መብቱን ማስከበሩ ተፈጥሮዋዊ መሆኑን ያስቀመጠ ነው ።
ስለ እዚኽ ፦ ሆብስ ከራሱ ጋር የእሚጋጭ የፖለቲካ አስተሳሰብ ነው የአለው ። ምክንያቱም ፦ ሰው ውልን የእሚገባው ፤ ለደህንነቱ ወይንም ለጥቅሙ ሲል ነው ፤ ውሉ ግን የእሚረግጠው እና የእሚበድለው ከሆነ ወይንም ውሉ የውሉን ዓላማ የእሚያከሽፍ ከሆነ ፤ አንድ ግዜ ውል ገብተኃል እና ቻለው ማለት ፤ ከተፈጥሮ በህይወት የመኖር እና ህይወትን እና ንብረትን ከአደጋ መከላከል መብት ወይንም ፍላጎት ጋር አብሮ አይኼድም ።
እዚኽ ጋር ፤ ለማስታወስ ያኽል ፤ ጆን ሎክ ፤ የመንግሥትን ስልጣን ወሰን እና መጠን በተመለከተ ፤ ለሕግ አውጭው የመንግሥት አካል ያልኹት በሙሉ ፤ ለአስፈፃሚውም እንደ እዚያው ነው ስለ እሚል ፤ እስከ አኹን መንግሥትን በተመለከተ ጆን ሎክ የአቀረበው ኃሳብ ለኹሉም የመንግሥት ፈርጆች ወይንም ቅርንጫፎች ተፈፃሚነት የአለው ነው ፦
“ስለ ሕግ አውጭው ያልኹት በሙሉ ፤ ለዋና አስፈፃሚውም የእሚሰራ እውነት ነው . . .”
“What I have said here concerning the legislative in general holds true also concerning the supreme executor, ... [71]“
በተመዘገበ ታሪክ ፤ ዴሞክራሲ በክሌስቲነስ ኃሳብ አመንጪነት ፤ በግሪኳ አቴንስ ከጀመረ በኋላ ፤ ለአለፉት ከ2000 ዓመታት በላይ በተለያየ የእድገት ኺደት ውስጥ አልፎ ፤ የተጀመረበትን ቅዱስ ዓላማ ፤ እርሱም ፦
ሰዎች ማሕበረሰብን የእሚያቋቁሙት ወይንም በማሕበረሰብ የእሚታቀፉት ፤ ለጥቅማቸው እንጂ ለጉዳታቸው አይደለም ወይንም በማሕበረሰብ ውስጥ መኖር ወይንም ማሕበራዊ ውል ማቆም (መንግሥት የእዚያኽ ውጤት ነው) ዋና ፋይዳው ፤ ኹሉም የራሱ አለቃ ሆኖ ከእሚኖርበት ኹኔታ በአሻገር ወይንም በላይ ለመጠቀም ነው ፤ የእሚለው ላይ ደርሷል ።
ይኽን ቅዱስ ዓላማ የእሚያሳካው ዴሞክራሲ ደግሞ በእሚከተለው ኹኔታ የእሚገለጸው ነው ፤ ወይንም ዴሞክራሲ ዓላማውን ሳይስት የእሚገለፀው በእሚከተለው አግባብ ነው ፦
ዴሞክራሲ ማለት በአመዛዝኖ የእሚደረስበት የተፈጥሮ ሕግ መገለጫ የሆነ ማሕበራዊ ውል በታሠረበት ማሕበረሰብ ውስጥ የእሚተገበር ሕዝባዊ ወይንም የብዙኃን መንግሥት ስረዓት ማለት ነው ። ይኽም ማሕበራዊ ውል ፤ የአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ አባላት ፤ አንዳቸው ከኹላቸው ጋር በተፈጥሮ ሕግ ፤ ማለትም ፦ ሰዎች ህይወታቸውን ለመጠበቅ እና በህይወት ለመኖር የእሚያስፈልጋቸውን ንብረት ለማግኘት እና ከአደጋ ለመከላከል ፥ የሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ ህይወትን የመጠበቅ እና ህይወትን ለማስጠበቅ የእሚያስፈልጉ ንብረት ለማግኘት እና ከአደጋ ለመከላከል የአላቸውን ተፈጥሮዋዊ መብት ሳይአደናቅፉ ፤ በአዕምሮ ፍርዳቸው የእሚመስላቸውን የማድረግ መብት የአላቸው መሆኑን በእሚያስረግጠው የአመዛዝኖ ሕግ ፤ ለመገዛት የተግባቡበት እና የተስማሙበት የፖለቲካ ስረዓት ሲሆን ፤ ይኽ ስምምነት ግን ፤ ኹሉም ዜጋ ከኹሉም ዜጋ ጋር የእሚገባው ስምምነት እንጂ ፤ ሕዝብ ከሆነ አመራር ጋር የእሚገቡት ውል በአለ መሆኑ ይኽንን የተፈጥሮ ሕግ ለማስከበር በድምፅ ብልጫ ተመርጦ ወደ ስልጣን የእሚመጣውም መንግሥትም በእዚኽ የተፈጥሮ ሕግ የእሚገዛበት ነው ።
ይኽ እስከ አኹን ከላይ የመጣንበት ኺደት ፤ ዴሞክራሲ ምንድነው ወይንም የዴሞክራሲ ትርጓሜ ፤ ከላይ የተሰመረበት አንቀጽ ላይ የተቀመጠውን ኃሳብ የያዘ መሆኑን ለማሳየት እነ እዚኽን የዴሞክራሲ መሠረት የሆኑ ዝርዝሮች ለማስረዳት የኼድንበት ነው ።
ከላይ እንደ ጀመርነው ፤ ዴሞክራሲ ምንድ ነው ወይንም የዴሞክራሲን ትርጓሜ ከታሪካዊ ዝግመቱ አኳያ ከአስቀመጥን ወዲያ ፤ የእሚቀጥለው ዴሞክራሲ ለምን ? የእሚለውን ጥያቄ መመለስ ነው ።
አስቀድመን ፤ ከላይ ስናስቀምጥ ፤ ዴሞክራሲን ዘመናዊ የማጠናቀቂያ ሥራውን የሰሩለት ፤ የተፈጥሮ መብት ፣ የተፈጥሮ ኹኔታ እና የተፈጥር ሕግ ያልናቸው ፅንሰ ኃሳቦች እንደ ሆኑ አስቀምጠናል ። ከእላይ ፤ ለማስረዳት እንዲመች ፤ የተፈጥሮ ኹኔታ ወይንም ሰዎች በተፈጥሮ የእሚገኙበት ኹናቴ ፤ የተፈጥሮ ሕግ የተፈጥሯቸውን ፈቃድ ወይንም ነጻነት ያረገበበት ነው ብለናል ።
በአመጣጥ ቅደም ተከተል እናስቀምጣቸው ብንል ፤ የተፈጥሮ መብት ብዙም ማሰብ ፣ ማመዛዘን እና ማስላት የእማይጠይቅ ፤ በአብዛኛው ደመ ነፍሳዊ የሆነ ነገር ነው ። በተነጻጻሪነት የተፈጥሮ ሕግ ግን ፤ በማመዛዘን እና በአመክንዮ የእሚደረስበት ነው ። ስለ እዚኽ ፦ ምንም እንኳን አኹን ከአለንበት የታሪክ ደረጃ አንጻር ፤ የተፈጥሮ ኹኔታ የተፈጥሮ መብት በተፈጥሮ ሕግ የተገራበት ቢሆንም ፤ ማመዛዘን የእሚያመጣው የተፈጥሮ ሕግ በሥራ ላይ በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ በእማይሆንበት ወቅት ፤ ተፈጥሮዋዊው ኹኔታ የተፈጥሮ መብት ብቻ የአለበት መሆኑ አይቀርም ወይንም የማሕበረሰብ አካላት በተፈጥሮ ሕግ ሳይዳኙ ፤ ኹሉም ሰው በዐይኑ ፊት መልካም መስሎ የእሚታየውን የእሚያደርግበትን መሆኑ ማለት ነው ።
ይኽ ፤ ከተፈጥሮ ሕግ በፊት የአለው የተፈጥሮ ኹኔታ ( State of Nature ) አንዳንድ ግዜ ወይንም በአንዳንድ ሰዎች የጦርነት ኹኔታ (State of War ) እየተባለ ይቀርባል ።
ምክንያቱም ፦ በእዚኽ ኹኔታ ውስጥ የእሚገኝ ግለሰብም ሆነ ማሕበረሰብ ፤ ወይንም የአዕምሮ ማመዛዘን በሌለበት ኹኔታ ፤ አንዱ በኹሉ ላይ የፈለገውን የእሚያደርግበት በመሆኑ ፤ ህይወት እና ንብረት አደጋ ላይ የእሚወድቁበት አጋጣሚ ወይንም እድል እጅግ ከፍ የአለበት በመሆኑ ነው ። ስለ እዚኽ ፦ ከተፈጥሮ ሕግ በፊት የአለው የተፈጥሮ ኹኔታ በሌላ ስያሜ የጦርነት ኹኔታ ተብሎ ይጠራል ።
ዴሞክራሲ ፤ እንደ ተፈጥሮ ሕግ ነፀብራቅ ሆኖ የእሚያስፈልግበት ምክንያትም ፤ ወይንም ዴሞክራሲ ለምን ለእሚለው ጥያቄ የመጀመሪያው ወይንም ቀዳሚው መልስ ፤ ከጦርነት ኹኔታ (State of War) ለመውጣት በማስፈለጉ ነው ።
ምክንያቱም ፦ በጦርነት ኹኔታ ውስጥ ህይወት አስቸጋሪ ስለ ሆነ ወይንም ዴሞክራሲ ህይወትን ለመጠበቅ እና ለህይወት የእሚያስፈልጉትን ለማግኘት ፥ ለማስጠበቅ እና ከአደጋ ለመከላከል ፤ ተፈጥሮዋዊ የመድህን ዋስትና በመሆኑ ነው ። ይኽ የተፈጥሮ የመድህን ዋስትና ግን ፥ ከላይ ጆን ሎክን ጠቅሰን እንደ አልነው ወይንም ይኽንን የደህንነት ዋስትና የእሚያስጠብቀው ፤ እንደው ማንኛውም ውል ወይንም መንግሥት ሰአይሆን ፤ የተፈጥሮው ሕግ ነፀብራቅ የሆነው ወይንም ዴሞክራሲያዊው መንግሥት ነው ።
ይኽም ማለት ፤ የተፈጥሮዋዊ ሕጉን የእማያንጸባርቅ ማንኛውም ውል ፤ መልሶ የተፈጥሮ ኹኔታ ዓይነት የሆነውን የጦርነት ኹኔታ መልሶ ስለ እሚያመጣው ወይንም የሰዎች በህይወት የመኖር እና ለህይወት ለመኖር የእሚያስፈልጋቸውን ንብረት የመፈለግ ፣ የማግኘት እና የማቆየት ፤ የሌላውን ሰው ተመሳሳይ ተፈጥሮዋዊ መብት ሳይጋፉ የእሚያስከብሩበትን ኹኔታ ስለ እሚያፈርሰው ፤ ሰዎች ተፈጥሮዋዊ የሆነውን እና በህይወት የመኖር እና ለህይወት የእሚያስፈልጋቸውን ንብረት በእሚመስላቸው መልክ የእሚያገኙበት መልክ እንዲመቻች ያምጻሉ ወይንም የተፈጥሮ ኹኔታው ተመልሶ ይመጣል ።
ስለ እዚኽ ፦ ከነፃነት ዴሞክራሲ ውጭ ያለ ማንኛውም የዴሞክራሲ ወይንም ሌላ ዓይነት መንግሥት ዓይነት ፦ ሶሻል ዴሞክራሲ ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ፣ የሠራተኛ አምባገነንነት ፣ እምባጠባቂ መንግሥት ( Vanguard ) ፣ የሞግዚት አስተዳደር ( Proctorate ) ፣ ወዘተ ፤ ከተፈጥሮ ሕግ በፊት የአለውን የተፈጥሮ ኹኔታ ተመልሶ እንዲ መጣ ስለ እሚያደርጉት ፤ የጦርነት ኹኔታን በማስከተል ማሕበረሰብን ፤ በአመጽ ፣ በጦርነት ፣ በሴራ ፣ ወዘተ ፤ ከመናጥ ሊታደጉት አይችሉም ።
እነ እዚኽ በማሕበራዊ ፍትሕ ስም ፤ የተፈጥሮን ሕግ ተፃርረው በመቆም ፤ የፖለቲካ ስረዓትን የሰው ልጅ የሰቆቃ መፍለቂያ የአደረጉ ከላይ የዘረዘርናቸው ከነፃነት ዴሞክራሲ ውጭ የአሉ ዘመናዊ የፖለቲካ ሰረዓቶች ፤ ከላይ በተቀመጠው መልኩ ዴሞክራሲ ወይንም የነፃነት ዴሞክራሲ የጦርነትን ኹኔታ የእሚመልሱ ብሎ ሲተቻቸው ፤ እነርሱም በተራቸው ዴሞክራሲ በድሆች እና በኃብታሞች መካከል ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ልዩነት በመፍቀድ ወይንም በማስቻል የማሕበራዊ ኢፍትኃዊነት ምንጭ ሆኗል በማለት ይተቻሉ ።
እነ እዚኽ በሶሻል ዴሞክራሲ ፣ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፣ በሠራተኛ አምባገነናዊ መንግሥት ፣ በእምባ ጠባቂ መንግሥት (Vanguard) ፣ በሞግዚት አስተዳደር (Proctorate) ፣ ወዘተ ፤ በእሚባሉት የመንግሥት ፍልስፍናዎች የእሚያምኑ ሰዎች በዴሞክራሲ ላይ የእሚያቀርቡት ትችት ፤ ዴሞክራሲ በነዳያን ሐገር አይሰራም ፣ ዴሞክራሲ የመንጋ ስረዓት ነው ፣ ዴሞክራሲ ብዛት የአለው ሕዝብ ውስጥ አይሰራም ፣ ወዘተ ፤ ዓይነት በዴሞክራሲ ላይ ይሰነዘሩ ከነበሩ የጥንታዊው እና የመካከለኛው ዘመን ትችቶች በኋላ የመጡ ፥ ሦሥተኛው ወይንም ዘመናዊ በዴሞክራሲ ላይ የእሚቀርቡ ትችቶች ናቸው ።
በዘመናዊዎቹ የዴሞክራሲ ኃያሲያን እምነት ፤ የተፈጥሮ ሕግ የሐገር መዋቅር መሠረት በእሚሆንበት ወቅት ፤ በሐገር ውስጥ በኃብታም እና ነዳያን ማካከል ከፍተኛ የኃብት መጠን ልዩነት ይፈጠራል ፤ ስለ እዚኽ መንግሥት ጣልቃ እየገባ የተፈጥሮን ሕግን በመጣስ ፤ ማሕበራዊ ፍትሕን ለማረጋገጥ ወይንም በነዳያን እና በኃብታሞች መካከል የአለውን የኑሮ ልዩነት ለማጥበብ ፤ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ በሕይወት የመጠበቅ እና ለህይወት የእሚያስፈልጋቸውን ንብረት ባለቤት የመሆን ነፃነት እና ተመሳሳይ የሌሎችን መብት እስከ አልተጋፉ ድረስ በእሚመስላቸው መንገድ ጥቅማቸውን መፈለግ ፣ ማግኘት ፣ እና ከአደጋ መከላከል መብት አላቸው የእሚለውን ፤ እንደ አስፈላጊነቱ የመሻር መብት ሊኖረው ይገባል ይላሉ ።
ይኽ ደግሞ ፤ የጦርነትን ኹኔታ እየጋበዙ በሰላም መኖር እንችላለን ብለው እንደ ማሰብ ያኽል እርስ በእርሱ የእሚጋጭ ፤ ፖለቲካዊ ብቻ ሰአይሆን አመክንዮዋዊም ስህተት ነው ። የተከተሉት ይኽ አስተሳሰብ ስኹትነት ፤ በተደጋጋሚ የታሪክ ውድቀት እና ክስረት የታየ ቢሆንም ፤ ከሳይንሳዊ ማስረጃ ይልቅ ፤ ግዜያዊ የርዕዮት ታማኝነት እና የግል ፍላጎት ፤ እውነታውን እየጋረዳቸው ፤ ሳይንሳዊ በአልሆነ መንገድ እነ እዚኽን አስተሳሰቦች ለማስቀጠል ይሰራሉ ።
ለምሳሌ ፦ እንደ አሜሪካ በአሉ ሐገራት ፤ በመቶ ወይንም በሺ የእሚቆጠሩ ሰዎች የአላቸው ኃብት ድምር በሚልየን የእሚቆጠሩ የአሜሪካ ዜጎች ከአላቸው ኃብት ድምር ይበልጣል ፤ ስለ እዚኽ ይኽ የሆነው ማሕበረሰቡ ከላይ በአልነው መልኩ በዴሞክራሲያዊ መርህ መሠረት በመዋቀሩ ነው ይላሉ ።
ወይንም ምሳሌውን የበለጠ ተግባራዊ ለማድረግ ፦ በአሜሪካ በአንድ ወቅት የኃብት ደረጃ አንደኛ የእሚባለው ኃብታም ፤ ጠቅላላ የኃብት መጠኑ 150 ቢሊዮን የአሜሪካን ዳላር ቢሆን ፤ የእዚኽን ሰው ኃብት 300 ሺ ሰዎች 500 ሺ ዳላር የእሚመጥን የግል ንብረት ቢኖራቸው ነው ከእዚኽ ሰው እኩል ኃብታም የእሚሆኑት በድምር ፤ ይኽም በመሆኑ በሐገሪቱ ውስጥ የእሚገኘው ኃብት በጥቂት ሰዎች ባለቤትነት የተያዘ ነው ፤ ይኽ ደግሞ ማሕበራዊ ኢፍኃዊነት ስለ ሆነ መንግሥት እንደ እዚኽ ዓይነቱን ኢከነሚያዊ ልዩነት ጣልቃ በመግባት ማጥበብ አለበት ፤ በእነርሱ እምነት ።
ከእዚኽም በመነሳት ፤ እነ እዚኽ ሰዎች ፤ እንደ ፅንፈኝነታቸው መጠን ፤ ተፈጥሮዋዊ መብት የሆነው የግል ኃብት የማፍራት መጠን እስከ እነ አካቴው ይከልከል ከእሚሉት አንስተው ፤ የኃብት መጠን ገደብ ይበጅለት ፣ ባለ ኃብቶች እጅግ የተጋነነ ግብር እንዲ ከፍሉ ይደረግ ፣ ወዘተ ፤ እስከ እሚል ይለያያል ።
በእነርሱ እምነት ፤ ይኽ የተፈጥሮን ሕግ የእሚፃረር ሕጋቸው ፤ በማመዛዘን የእሚገኘውን የተፈጥሮ ሕግ በመሻር ማሕበረሰብን ወደ ጦርነት ኹኔታ እንደ እሚመልሰው ችላ በማለት ፤ መንግሥት ወይንም የመንጋ ጉልበት ፤ በተዛባ ኹኔታ ተሰራጭቶ የእሚገኘውን ኃብት ፤ በተቻለ መጠን ፍትኃዊ በሆነ ወይንም የኃብት እኩልነትን በእሚያረጋግጥ መልኩ ፤ በተለያየ ዘዴ ለዜጎች ማከፋፈል እንደ አለበት ያምናሉ ።
ዴሞክራሲያዊው ርዕዮት ፤ ለእነዚኽ ዘመናዊ የዴሞክራሲ ኃያሲያን የእሚሰጠው መልስ ፦ ፖለቲካዊ እኩልነት እንጂ ኢክኖሚያዊ እኩልነትን ለማረጋገጥ መሥራት ፤ ኢከነሚያዊ እኩልነቱን ማረጋገጥ አይችልም ብቻ ሰአይሆን ፤ ኢከነሚያዊ እኩልነትን ለማረጋገጥ በእሚል የዜጎችን ፖለቲካዊ እኩልነት በቋሚነት በመሻር ፤ የተለያዩ የማሕበርሰብ ክፍሎችን በማስቆጣት ማሕበራዊ አለ መረጋጋትን ወይንም የተፈጥሮ ኹኔታን ይመልሰዋል ፤ የእሚል ነው ።
የተፈጥሮን ሕግ በመሻር ጭቆናን እና ብዝበዛን በማምጣት ፖለቲካዊ እኩልነትን ይሽራል ፤ በእዚኽም ወደ ቀደመው የጦርነት ኹኔታ (State of War) ማሕበረሰብን ይመልሳል ብቻ ሰአይሆን ፤ በኢከነሚያዊ መመዘኛ ራሱ ፤ ኢከነሚያዊ እኩልነትን ለማረጋገጥ ፖለቲካዊ እኩልነትን የእሚሽር ማሕበረሰብ ፤ ጠቅላላ የማሕበረሰብን የማምረት አቅም (GDP)በመቀነስ የግለሰቦችን የነጠረ ገቢ ወይንም ተጠቃሚነት (Net Income) ይቀንሳል ።
ምክንያቱም ፦ ኢከነሚያዊ ወዋቅር እና ፖለቲካዊ መዋቅር አንድ ዓይነት አንቀሳቃሽ እና ገዢ መርህ (Dynamics) የሌላቸው በመሆኑ ።
ፖለቲካዊ እኩልነት ፤ ለማሕበራዊ ደህንነት እና እድገት መተኪያ የሌለው ተፈጥሮዋዊ ኹናቴ ነው ፤ ኢከነሚያዊ እኩልነት ግን ፤ ከተፈጥሮ የእሚመነጭ ሰአይሆን ከውጭ በእሚመጣ አስገዳጅ ወይንም የይኹንታ (Normative) ሕግ የእሚጫን በመሆኑ ፤ ወይንም ተፈጥሮዋዊ የኢከነሚክስ መርህን የተከተለ በአለ መሆኑ እና ይሉቁንም ተፈጥሮዋዊ የኢከነሚክስ ሕግን የእሚፃረር በመኾኑ ፤ ለመፈክርነት ቢያምርም ፤ በውጤት ማሕበራዊ ድህነት ፣ ኢከነሚያዊ ውድቀት እና ማሕበራዊ አለ መረጋጋት ነው የእሚያስከትለው ።
ለምሳሌ ፦ የሒሳብ ትምህርት ክፍል በሆነው ጂኦሜትሪ በእሚባለው ዘርፍ ከኹለት ሺ ዓመት በላይ መልስ የአልተገኘለት የሒሳብ ጥያቄ አለ ፦ “እኩል ጎን የአለው አራት ማዕዘን (A Square) ከአንድ ክብ (Circle) ጋር እኩል ስፋት (Area) እንዲ ኖረው ማድረግ ይችላል?” የእሚል። ለእዚኽም ጥያቄ የእሚታወቀው መልስ ፤ አሉታዊ በመሆኑ ወይንም እኩል ጎን የአለው አራት ማዕዘን ከአንድ ክብ ጋር እኩል ስፋት ሊኖረው አይችልም የእሚል በመሆኑ ፤ በእንግሊዘኛ “እኩል ጎን የአለውን አራት ማዕዘን ክብ ልታደርገው አትችልም” (You cannot circle a square) የእሚባል አባባል እስከ ማስተዋወቅ የደረሰ ሆኗል።
እ.አ.አ. በ1897 ዓ.ም. እንድ ኤድዋርድ ጄ. ጉድዊን (Edward J. Goodwin) የእሚባል የኢንዲያና (Indiana) የእሚባለው የአሜሪካ ግዛት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ግን ፤ በሒሳብ ትምህርት ውስጥ የክብን ስፋት ለመለካት በእሚውለው ስሌት (ፎርሙላ) ውስጥ የአለው እና ፓይ (π) ተብሎ የእሚታወቀውን እና በተቀራራቢነት በግምት በቋሚነት 3.14 ዋጋ ወይንም መጠን የእሚሰጠውን ምልክት ፤ መጠኑን ከ3.14 ወደ 3.2 በመቀየር እኩል ጎን የአለውን አራት ማዕዘን ክብ ማድረግ ይቻላል እና ይኽንን ግኝቴን ወይንም የፓዩን ቋሚ መጠን ከ3.14 ወደ 3.2 የእሚቀይረው ስሌቴ በሕግ መወሰኛው ቤት ይጽደቅልኝ ብሎ ፤ ሕግ አድርጎ ሊያጸድቀው ከግማሽ በላይ ተጉዞ ነበር ፤ የእዚኽ ረቂቅ ሕግ በእሚጸድቅበት ቀን የሒሳብ ፕሮፌሰር የሆነው ክለረንስ አብያታር ወልዶው (Clarence Abiathar Waldo) በአጋጣሚ በፓርላምው አከባቢ ተገኝቶ ይኽንን ታሪካዊ ስሕተት ጣልቃ በመግባት በአያስቆመው ኖሮ።
ኤድዋርድ ጄ. ጉድዊን አንድ ማወቅ የነበረበት ነገር ፤ የሳይንስ ሕግ በፓርላማ እንደ እማይወጣ ነበር።
ማሕበረ_ኢከነሚም የራሱ ‘ፍጥረት’ እና ከእዚኽም ‘ፍጥረቱ’ የእሚመነጭ የራሱ ሳይንስ የአለው ነው ፤ ስለ እዚኽም ፦ መሠረቱ የሰዎች በጎ ፈቃድ መሆን አይችልም። አንድ ፖለቲከኛ ወይንም ቀንዓዊ ተነስቶ ፤ አጭር እጅ የአላቸው ሰዎች ረዥም እጅ ከአላቸው ሰዎች ይልቅ የተለያየ ችግር እየ አጋጠማቸው ስለሆነ ፤ ይኽንን ማሕበራዊ ኢፍትኃዊነት መፍታት የእሚቻለው ፤ ኹሉም ሰው እኩል እጅ ሲኖረው ነው ብሎ ፤ የመጨረሻ አጭር እጅ ባለው ሰው ልክ የሰውን ኹሉ እጅ መቁረጥ አለብኝ ቢል ፤ ሰውየው በእዚኽ ዕቅዱ የማሕበረሰብን ችግር ከመፍታት ይልቅ ይበልጥ እንደ እሚያወሳስበው ፤ ኢከነሚያዊ እኩልነትን ግብ አድርጎ መሥራት ፤ በማሕበረሰብ ውስጥ ኢከነሚያዊ እኩልነትን ከማምጣት ይልቅ ማለቂያ የሌላቸው ሌሎች ብዙ ተዛማጅ ችግሮችን ይዞ የእሚመጣ ነው።
ምክንያቱም ፦ እንደ ሒሳቡ ወይንም እንደ ሌላው ሳይንስ ኢከነሚው በሰዎች አስተሳሰብ እና ፍላጎት ብቻ የእሚመራ ሳአይሆን ፤ በዋናነት በእራሱ ሳይንሳዊ መርህ የእሚመራ ነውና።
ኢከነሚያዊ እኩልነትን ፤ በመንግሥታዊ ጣልቃ ገብነት ማረጋገጥ ከእማይቻልበት ምክንያት አንዱ ፤ በኢከነሚክስ ሳይንስ ውስጥ ጤናማ እና ማሕበራዊ ኢከነሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ ፤ Pareto Effieciency ወይንም Pareto Superior የእሚባለው የኢከነሚክስ መርህ አስፈላጊነት ነው ።
የእዚኽ የኢከነሚክስ ሳይንስ መርህ ዋና ኃሳብ እንዲህ ሊቀመጥ ይችላል ፦ የኃብት ክፍፍል የሰዎችን የማምረት አቅም ያል አገናዘበ ከሆነ ድምር ውጤቱ ማሕበራዊ ብክነት ነው ። ስለ እዚኽ ፦ አንድ ማሕበራዊ የኃብት ክፍፍል ቀመር ውጤታማ የእሚባለው ክፍፍሉ የማሕበረሰብ የማምረት አቅመን ከጨመረ ነው ። ይኽም ማለት የክፍፍል ቀመሩ ፤ በሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ፤ ማሕበራዊ የማምረት አቅምን ወይንም ማሕበራዊ ምርትን ቢያንስ በአለበት ማስቀጠል አቅቶት እንዲያሽቆለቁል ሊያደርግ የእሚችል ከሆነ የመሐበራዊ የኃብት ክፍፍል ቀመር ፤ Pareto Inefficient or Pareto Inferior ነው ።
ስለ እዚኽ ፦ ማንኛውም የማሕበራዊ ኃብት ማከፋፈያ ቀመር ወይንም እቅድ ፤ ከተተገበረ በኋላ ፤ ጠቅላላ ማሕበራዊ ኃብትን በቀጣይነት እንዲ ያሽቆለቁል አድርጎ ፤ የኃብት እኩልነትን ቢያረጋግጥ ፤ እየጨመረ የእሚኼድ ድህነትን በእኩልነት ከማከፋፈል ያለፈ የእሚፈይደው ነገር በአለ መኖሩ ፤ ተመራጭ አይደለም ወይንም አባካኝ (Inefficient) ነው ፤ የእሚል ነው ።
ለምሳሌ ፦ 10 ሰዎች በአሉበት ማሕበረሰብ ውስጥ ፤ ለእያንዳንዱ ሰው 100 ሺ ብር በእኩልነት ማከፋፈል ፤ እኩልነትን በግዚያዊነት ያመጣ ቢመስልም በግዜ ኺደት ግን ፤ በእዚኽ ስሌት መሠረት ፤ ሲጀምር 1, 000, 000 (አንድ ሚልየን) የነበረው ማሕበራዊ ኃብት ፤ ወደ ፊት ሊፈጥር የእሚችለውን ኃብት በሙሉ አይፈጥርም ማለት ነው ወይንም የኃብት ስርጭቱ ፤ የሰዎቹን የማምረት አቅም ያገናዘበ በአለ መሆኑ ፤ አንዱ ግለሰብ ይኽን ኃብት ሊቀብረው ይችላል ፤ ሌላኛው ሊያባክነው ይችላል ፣ ሌላኛው ሊያከስረው ይችላል ፤ ሌላኛው ደግሞ ብዙ ሊያተርፍበት ይችላል ።
ከእዚኽ የተነሳ ፦ ነገር ተብሎ እና ተመትሮ ሲያልቅ ፤ በ 1, 000, 000 የጀመረው ማሕበረሰብ ኃብት ፤ ‘በማሕበራዊ ፍትሕ’ አቀንቃኝ ካድሬዎች ቀመር አግባብ የዜጎችን የማምረት አቅም በአላገናዘበ መንገድ ከተሰራጨ ፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ትርፍ እና ኪሳራው ፥ ወጪ እና ቀሪው ተቀናንሶ የተጣራው ኃብት ሲሰላ ፤ የቀረው 900,000 ሺ ሊሆን ይችላል ።
ስለ እዚኽ ፦ ቢቻል እና ኃብት በእዚኽ መልኩ በእኩልነት ወይንም ‘በፍታሐዊነት’ ቢከፋፈል እንኳን ፤ የኃብት ክፍፍሉ የኢከነሚክስን መርህ መሠረት የአደረገ ሰአይሆን ፤ የምድረ-ገነት (Utopia) ሰባኪያንን ቅዠት መርህ መሠረት የአደረገ በመሆኑ ፤ ምርታማነትን በመቀነስ ፤ ማሕበራዊ ኃብትን እያወደመ የእሚኼድ ነው የእሚሆነው ወይንም Pareto Inefficient ነው ወይንም Pareto Superior አይደለም ።
እንግዲኽ ፦ የማሕበራዊ ፍትሕ ቅዠትን ተከትለን ፤ በማሕበረሰብ ውስጥ 100 ሺ ተሰጥቶት 70 ሺ የመለሰውንም ፥ 100 ሺ ተሰጥቶት 110 ሺ የመለሰውንም እና በድምሩ ከ1, 000, 000 ወደ 900, 000 የወረደውን ማሕበራዊ ኃብት ፤ ኢከነሚያዊ እኩልነት በእሚል ቂልነት ፤ 900, 000 ውን እንደገና 90 ሺ እየአደረገን ለ10 የማሕበረሰብ አባላት ‘በማሕበራዊ ፍትሕ’ ስም በእኩልነት ብእናከፋፍል ፤ የተለመደው ዑደት ራሱን በመድገም ፤ በእሚቀጥለው የበጀት ዓመት ጠቅላላ የማሕበረሰብ ኃብት ከ800, 000 ማነሱ አይቀርም ብቻ ሰአይሆን ፤ አምራቹ እየተቀጣ አክሳሪው እየተሸለመ የአለበት በመሆኑ ፤ በእዚኽም የሰዎች ተፈጥሮዋዊ መብት የተገፈፈበት እና የሰዎች ቁጣ የናረበት ነው የእሚሆነው ።
በእኔ እምነት ፤ የተፈጥሮ ኹኔታ ወይንም የጦርነት ኹኔታ ፤ በተለይ በእዚኽ ዘመን የግድ ደም አፋሳሽ በሆነ ጦርነት ብቻ መገለፅ የለበትም ፤ ዜጎች ወይንም ኢንቨስተሮች በአንድ ሐገር የፖለቲካ ስረዓት ውስጥ ፤ ሕይወታቸው ፣ እውቀታቸው እና ንብረታቸው (ካፒታላቸው) የደህንነት ዋስትና የሌለው በመሆኑ ፤ በአገኙት ቀዳዳ ኹሉ ፦ የተማረው የሰው አዕምሮ እና አንጡራ ኃብቶች የሐገርን ድንበር ለቀው የእሚወጡ ወይንም የእሚሰደዱ ከሆነ ቴክኒካሊ የተፈጥሮ ወይንም የጦርነት ኹኔታ ውስጥ ነው ያ ሐገር ።
ይኽም ፤ ዴሞክራሲያዊው ርዕዮት ፤ የማሕበራዊ ፍትሕ አቀንቃኞች በዴሞክራሲ ላይ የእሚያቀርቡት ያልተማረ ነቀፋን አስተሳሰብ ስህተት ወደ እሚያሳየው ኹለተኛው ኢከነሚያዊ መርኽ ይመራናል ። ይኽም ፤ ኢከነሚስቶች የግዜ መስኮት (Time Frame) የእሚሉት ነው ።
ይኽ ፤ የግዜ መስኮት የእሚለው የኢከነሚክስ መርኽ የእሚለው ፤ በኢከነሚው ረገድ ሰዎችን በእኩልነት ማስጀመር ይቻላል ፤ በእኩልነት ግን ማስቀጠል አይቻልም ። ቁጭ ብሎ ማንበብ የእሚወደው እና የንግድ እቅድ እና ትግበራ አፍቃሪ የሆነ ሰው እኩል 100 ሺ ብር ቢሰጣቸው ፤ አንባቢው ለነጋዴው ብሩን ቢያበድረው እና ወለድ ከገንዘቡ ቢያገኝ ነው የእሚመርጠው ። ነጋዴው ደግሞ የራሱ 100 ሺ ላይ የአንባቢውን 100 ሺ ጨምሮ ፤ በአጠቃላይ 200 ሺ ካፒታል ይዞ ፤ በራሱ ገንዘብ ብቻ ቢነግድ የእሚያገኘውን 10 ሺ ትርፍ ፤ የሌላም ሰው ገንዘብ ጨምሮ ከእሚያገኘው ትርፍ ለአንባቢው 5 ሺ ከፍሎ የራሱን 15 ሺ (ተጨማሪ 5 ሺ) ማግኘት ነው የእሚፈልገው ።
ስለ እዚኽ ፦ በግዜ ፤ ኺደት አንባቢው በእውቀት ነጋዴው በገንዘብ እየተለያዩ መኼዳቸው ፤ የእማይቀር ነው ፦ እናም መንግሥት ሰዎች በእኩልነት ጀምረው በፈቃዳቸው የኼዱበትን የተለያየ መንገድ ከግምት ውስጥ ሰአያስገባ ፤ በእየ ግዜው ቁሳዊ ኃብቱን እንደ ገና በእየ ዘመኑ በእኩል ማካፈል አለበት ማለት መሠረታዊ የሆነ የማሕበረሰብ ስብጥርን ያለመረዳት ችግር ነፀብራቅ ነው ።
ለእዚኽም ነው ከነፃ ገበያ የተሻለ የፍትሐዊ የኃብት ማከፋፈያ መዋቅር የለም የእሚባለው ።
የአንባቢውን እውቀት ከአንባቢው ጭንቅላት አውጥቶ ፤ ነጋዴው ጭንቅላት ውስጥ ማስገባት የእማይቻል ከሆነ ፤ በምን መርህ ነው የነጋዴውን ገንዘብ ወስዶ ለአንባቢው መስጠት የእሚቻለው ?ሰዎችስ ለምርጫቸው ኃላፊነት መውሰድ የለባቸውም ? ይኽ እንግዲኽ በጣም አዎንታዊ የሆነው የሰዎች ባሕሪ ወስደን ነው ።
በጣም ውስብስብ እና እንደ ማጭበርበር ፣ ቅሚያ ፣ ስንፍና ፣ ስግብግብነት ፥ ወዘተ ፤ በአሉ በተለያየ ተጽኖ ስር ያለ ማሕበረሰብ ውስጥ ፤ ዘመን እየጠበቁ በቋሚነት የኃብት ክፍፍል ፍትሐዊነት በሕግ በማስፈር ፤ ማሕበራዊ ፍትሕ አሰፍናለሁ ባዮች ፤ ሲያንስ የኢከነሚክስ መኃይማን ሲከፋ ደግሞ ምድረ-ገነት(Utopia) በመስበክ ፤ ፀሎታቸውን እያስረዘሙ የድሆችን ፖለቲካዊ ድጋፍ ለማግኘት ሲሉ ሕዝብን እና ሐገርን የእሚጎዱ ማታለያዎችን የእሚጎነጉኑ ፤ ሐገር አፍራሽ ፖለቲከኞች ናቸው ብለን ከመሰየም ውጭ አማራጭ የአለ አይመስልም ።
ማንኛውም ፖለቲካዊ ርዕዮት መተቸት አለበት ። ከእዚኽም የተነሳ በዴሞክራሲ ላይ ከእነ ፕሌቶ ዘመን አንስቶ እስከ አኹን ዘመን ድረስ የቀረቡት ትችቶች እንደ አዲስ እና አስገራሚ ክስተት መታየት የለባቸውም ፤ ሆኖም ግን ፤ በዴሞክራሲ ላይ የቀረቡት ትችቶች ከግንዛቤ እጥረት ፣ ከርዕዮታዊ ወገንተኝነት ወይንም ከሌሎች እኩይ መነሻ የቀረቡ እንጂ መሠረታዊ የዴሞክራሲን ችግር መሠረት የአደረጉ በአለ መሆናቸው ፤ አኹን በእምንኖርበት ዘመን ላይ የመናገር ነፃነት ሙሉ በሙሉ በታፈነበት ሐገር ከአልሆነ በስተቀር ፤ በዴሞክራሲ ላይ የእሚቀርቡ ትችቶች ተዳክመው ፤ በአደባባይ የዴሞክራሲን አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የእሚያስገባ ሰው አፈንጋጭ እና መኃይም የእሚመስልበት ደረጃ ላይ ደርስናል ።
ምን አልባት ለኋላቀር ሐገራት የእዚኽ ዘመን ትልቁ ፈተና ፤ አምባገነናዊ እና የዜጎችን ሕይወት እና ንብረት ስጋት ውስጥ የእሚጨምሩ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ስረዓቶች በኃሳብ ገበያው ከተሸነፉ በኋላ ፤ ዴሞክራሲ ትክክል ነው ነገር ግን ሶሻል ዴሞክራሲ መሆን አለበት ወይንም አብዮታዊ ዴሞክራሲ መሆን አለበት ዓይነት ማወናበጃዎችን ማቅረብ ነው ።
ከእዚኽም የተነሳ ፤ የአሊስ ጀብዱ በምድረዛብር (Alice’s Adventures in the Wonderland) በእሚለው ድርሰት ሥራ ላይ ፤ በገኃዱ ዓለም ኑሮ ተሰላችታ የቅዠት ዓለም ውስጥ ለመኖር የፈለገችው ህጻኗ አሊስ ወዴት እንደ እምትኼድ ሳታውቅ ፤ የትኛውን መንገድ ልወሰድ? ብላ ለጠየቀችው ጥያቄ ፤ ድመቱ የት እንደ እምትኼጂ ከአለ አወቅሽ ኹሉም ያደርስሻል ዓይነት እንደምታ የአለው ምፀታዊ መልስ እንደሰጣት ፤ ዴሞክራሲ ምን ማለት እንደሆነ ለአልገባው ሰው ፤ ዴሞክራሲ የሞልቃቆች ነው ሲባል ዴሞክራሲን ፤ ምን እንደሆነ ሳያውቀው ሲጠላ ወይንም ደግሞ ዴሞክራሲ ማለት የደኃው አምባገነንነት የነገሠበት ነው ተብሎ ፤ አምባገነን ስረዓት በላዩ ላይ ሲጫንበት ያወቀ መስሎት ፤ ማሕበራዊ ፍትሕ ፣ ሶሻል ዴሞክራሲ ፣ ዴሞክራሲያዊ አብዮት ፣ ወዘተ ፣ ብሎ ፤ እንደ በሬ ካራጁ ሲውል በተደጋጋሚ እየታየ የአለው ፦
“ … ፥ ቀጠል አድርጋ ‘ከእዚኽ የትኛውን መንገድ መውሰድ እንዳለብኝ ፤ ትነግረኝ እባክህ?’
‘ያ በጣም ፤ አንቺ መኼድ በእምትፈልጊበት ቦታ ይወሰናል’ አላት ድመቱ ።
‘ወዴት እንደ እምኼድ ብዙም አይገደኝም - ‘አለች አሊስ ።
‘እንዲያኽ ከሆነ የቱንም መንገድ ብትወስጂ ችግር የለውም ፥’ አላት ድመቱ ።”
“…, and she went on. ‘would you tell me, please, which way I ought to go from here?’
‘That depends a god deal on where you want to get to,’ said the Cat.
‘I don’t much care where- ‘said Alice.
‘Then it doesn’t matter which way you go,’ said the Cat. [72]“
ዴሞክራሲ ለምን ለእሚለው ጥያቄ ኹለተኛው መልስ ፤ በፖለቲካው መስክ ዴሞክራሲ በሰፈንበት ምህዳር ውስጥ ለኢከነሚያዊ እድገት ትክክለኛው እና አመቺውን ኹኔታ ስለ እሚፈጠር ነው።
ማንኛውም ውጤታማ ኢከነሚያዊ ስረዓት ማሕበራዊ ሰላምን በቅድመ ኹኔታነት የእሚፈልግ ነው። ዴሞክራሲም የጦርነትን ኹኔታ በማስወገድ ይኽን ለኢከነሚያዊ እድገት የእሚያስፈልገውን ቀዳሚ ኹኔታ ያሟላል። ኹላችንም እንደ እምናውቀው ግን ማሕበራዊ ደህንነት ወይንም ሰላም ስለ አለ ብቻ ኢከነሚያው እድገት አይመዘገብም ወይንም ማሕበራዊ መረጋጋት ወይንም ሰላም ለኢከነሚያዊ እድገት ቅድመ ኹኔታ ነው ማለት ፤ ማሕበራዊ መረጋጋት ፣ ሰላም ወይንም ደሕንነት በተናጠል ኢከነሚያዊ እድገትን ያስከትላል ማለት አይደለም።
እጅግ ሰላማዊ እና የነጡ ድሆች ሊኖሩ ይችላሉ።
ለኢከነሚዊ እድገት ፤ ከማሕበራዊ ሰላም ወይንም መረጋጋት በአሻገር ፤ አኹን በእሚታወቀው የኢከነሚክስ ሳይንስ መሠረት ፤ ሰዎች ወይንም ግለሰቦች ኢከነሚያዊ ሚናቸውን በአግባቡ የእሚጫወቱበት ሕጋዊ ማዕቀፍ መኖር አለበት ።
ይኽም ማለት ፦ የዜጎች የግል ንብረት በአለቤትነት ስለ እዚኽም በነጻ ገበያ ተወዳድረው በንብረትነት የያዙትን ሸቀጥ የእሚሸጡበት እና በነጻ ገበያ ከሕጋዊ በአለቤት የገዙትን ሸቀጥ ሕጋዊ በአለቤት ሊሆኑበት የእሚችሉበት ኹኔታ መኖር አለበት ፤ የእሚታወቀው ዘመናዊ የኢከነሚክስ ሳይንስ የእሚያስተምራቸው መርሆዎች ሰረተው ግለሰባዊ እና ማሕበራዊ ኢከነሚያዊ እድገት እንዲ መጣ።
ዴሞክራሲም የዜጎችን ንብረት የማፍራት እና የአፈሩትን ንብረት ፤ በሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ በእሚመስላቸው መንገድ እንዲያስተዳድሩ ወይንም በነጻ ገበያ ተወዳድረው መግዛት እና መሸጥ እንዲችሉ የእሚፈቅድ በመሆኑ ፤ ይኽንን ኹለተኛው ለኢከነሚያዊ እድገት የእሚያስፈልገውን ኹኔታ ያሟላል።
ስለ እዚኽ ፦ ዴሞክራሲ ፤ ለኢከነሚያዊ እድገት ፤ የጦርነትን ኹኔታ በማስቀረት እና የማሕበረሰብ ኢከነሚያዊ መዋቅር በኢከነሚያዊ ሳይንስ መርህ መሠረት እንዲሰራ በማመቻቸት ፤ ግለሰባዊ እና ማሕበራዊ እኮኖሚያዊ እድገትን ከሌሎች ፖለቲካዊ ርዕዮተች በተሻለ መልኩ ማረጋግጥ ይችላል። የእዚኽንም ዝርዝር ፤ ከእዚኽ በእሚቀጥለው ፤ በሐገር ጉዳይ ፡ ዴሞክራሲያዊ እሴቶች እና ፋይዳቸው በእሚለው ንዑስ ስር በዝርዝር እናየዋለን።
ይኽም ፤ ዴሞክራሲ ለምን ? ለእሚለው ጥያቄ ኹለተኛ መልስ ነው።
እንግዲህ ፤ ዴሞክራሲ ምንድ ነው? እና ዴሞክራሲ ለምን ? የእሚሉትን ጥያቄዎች ከመለስን ፤ ሦሥተኛው እና የመጨረሻው ጥያቄ የእሚሆነው ዴሞክራሲ እንዴት ? የእሚለው ነው ። ዴሞክራሲ እንዴት የእሚለውን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ሦሥት መሠረታዊ ኃሳቦችን ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል ፦
የሰው አቅም ስንል ፤ ሰዎች በአንድ ሥራ ላይ ውጤታማ የእሚሆኑት በአንድ የተመረጠ የሥራ መስክ ላይ ማተኮር ወይንም አንድን ተግባር በተናጠል ሞያ አድርገው መያዝ (Specialize) ሲችሉ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ፤ ሰዎች ላይ ኃላፊነት አለመደራረብ የእሚለውን እያልን ነው ።
ስለ እዚኽ ፦ የዴሞክራሲን እንዴታ ስናስብ የመጀመሪያው ጉዳይ ፤ ለዴሞክራሲያዊ ኃሳብ እና መንግሥት የተሰጠ ሰው ወይንም የፖለቲካ ማሕበረሰብ መኖሩ የግድ አስፈላጊ መኾኑን እና ሰዎች የተሻለ ውጤት በእሚያመጡበት መስክ መመደብ እንደ አለባቸው ማሰብ የግድ ነው የእሚለው የመጀመሪያ ጉዳይ ነው ።
የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰብ ተቃዋሚዎች እንደ እሚሉት ፤ የመንግሥትን ኃላፊነት ለመወጣት የእሚያስፈልገው ክህሎት ሕበረተሰብ ውስጥ በገፍ ወይንም በብዛት የእሚገኝ ስለ አልሆነ (Governance is a scarce social commodity) ፤ የእዚኽ “ብርቅዬ” ክህሎት የአላቸው ሰዎች ፤ በዋናነት ብቻ ሰአይሆን በብቸኝነት ፤ ዴሞክራሲያዊ መንግሥትን በማቆም ፣ በማጠናከር እና በማጠናቀር ላይ ማተኮር አለባቸው ።
ለምሳሌ ፦ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ የእሚመጡ ሰዎች ይኽንን ፤ በበቂ ኹኔታ የሌለ ክህሎት ይዘው ፤ የልማት ሥራ ውስጥ ራሳቸውን እያስገቡ ኃሳባቸውን በመከፋፈል መዳከም የለባቸውም ። መንግሥትነት (Governance) በራሱ ሰፊ እና የሙሉ ግዜ ሥራ ነው ።
ይኽ ቁጥብ የሰው አቅም ፤ አትኩሮቱን በሙሉ ፤ በዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሳይንስ ላይ ብቻ አትኩሮቱን በማድረግ ፤ የዴሞክራሲያዊ መንግሥት አስተሳሰብን ፤ በበቂ ኹኔታ የመንግሥት መዋቅር ዝርጋታ ፣ ማስፋፊያ ፣ ማሻሻያ እና ማስቀጠያ ወይንም አስተዳደር ላይ ማተኮር አለበት ።
አንዳንድ ሰዎች እንደ እሚመስላቸው ፤ መንግሥት በአገዛዝ (Governance) ጉዳይ ላይ ብቻ ማተኮሩ ፤ መንግሥትን ዘበኛ የእሚያደርገው ወይንም እጁን አስሮ የእሚያስቀምጠው ሰአይሆን ፤ አገዛዝ የብዙ ሳይንሶች ጭማቂ የሆነ እና ራሱን የቻለ የከበረ ሞያ በመሆኑ ፤ የመንግሥት ሰዎች በመንግሥትነት ኃላፊነት ብቻ እና ብቻ ላይ ማተኮራቸው ፤ በሞያ ክፍፍል መርህ ሕግ መሠረት ውጤታማ መንግሥት እንዲኖር እና ይኽም በተራው ጠቅላላው ማሕበራዊ ውጤታማነትን እንዲጨምር ያደርጋል ።
መንግሥት በመንግሥት ሥራ ላይ ብቻ መወሰኑ ፤ ትልቁን የመንግሥት አቅም ማባከን ሰአይሆን ፤ የመንግሥትን ትልቁን አቅም በተገቢው ቦታ ለተገቢው ዓላማ ሳይከፋፈል እንዲውል በማድረግ መንግሥትን የሐገር ደህንነት እና እድገት መሠረት እንዲሆን ማድረግ ነው ።
ከእዚኽ በመቀጠል ፤ ዴሞክራሲን የእሚያስችለው ፤ ከላይ በተጠቀሰው አግባብ ራሳቸውን ለመንግሥትነት ከሰጡ እና የእሚያስፈልገውን ክህሎት በአዳበሩ ሰዎች ፤ ዴሞክራሲን የእሚያስችል በዴሞክራሲያዊ ፅንሰ-ኃሳብ የተመሮከዘ መዋቅርን መዘርጋት ይጠይቃል ።
የመዋቅር ስኬት በሞያተኞች ላይ ብቻ የተመረኮዘ አይደለም ፤ በጣም አቅም የአላቸውንም ሰዎች መዋቅር አል አሰራ ብቻ እያለ ሰአይሆን እየደበደበ ወደ ጥግ ሊያስወጣ ይችላል ።
ለእዚኽም ነው ፤ ፖለቲካዊ መዋቅር በማሕበረሰብ ውስጥ የእሚገኙ የኹሉም መዋቅሮች እናት መዋቅር በመሆኑ ፤ የፖለቲካ መዋቅር የአበላሸውን ነገር ፤ ሌላ ምንም ዓይነት ማሕበራዊ መዋቅር ሊፈታው የእማይችለው ። (The political structure is the supra structure of all other social structures) ።
የፖለቲካ መዋቅር ያሰረውን ፦ ኃይማኖታዊ ፣ ባህላዊ ፣ ኢከነሚያዊ ወይንም ሌላ መዋቅር ሊፈታው አይችልም ወይንም የፖለቲካዊ መዋቅር ችግር ሳይፈታ ሌሎች የማሕበራዊ ቀውስ ምንጭ የሆኑ መዋቅራዊ ችግሮች ትርጉም በአለው መልኩ ሊፈቱ አይችሉም ።
ከዴሞክራሲ አንፃር ስለ መዋቅር ስናወራ ፤ እያወራን ያለነው ፦ የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት ማክበር የስረዓቱ ማዕከል ስለ ማድረግ ፣ ወደ መንግሥት ስልጣን የእሚመመጡ ሰዎች በምርጫ እና ለተወሰነ ግዜ እንዲመጡ ስለ ማድረግ ፣ የመንግሥትን ስልጣን በኃላፊነት እና በቦታ ስለ ማከፋፈል ፣ ወዘተ ፤ እየተነጋገርን ነው ።
ከአሜሪካ ዴሞክራሲ በፊት የነበሩ ብዙ ፤ ታሪካዊ ዴሞክራሲዎች እነ እዚኽን ኃሳቦች በአለ ማዳበራቸው እና በአግባቡ በአለ መትግበራቸው ነው ፤ ታላቁ የዴሞክራሲ ህልማቸው የከሰመው ።
ከላይ እንደ አስቀመጥነው ፤ አሌክሳንደር ሐሚልተን እንደ እሚለው ፤ በዘመነ አሜሪካ የዳበሩ አዲስ መዋቅራዊ አስተሳሰቦች ፤ ለአሜሪካ ዴሞክራሲ ስኬት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል ፦
“ስልጣንን በቋሚነት በእየሥራ መምሪያው ማከፋፈል ፣ የሕግ አውጪውን ስልጣን ሚዛናዊነት ማረጋገጥ እና መቆጣጣሪያ ማበጀት ፣ ዳኞች የባሕሪ ዝቅጠት እስከ አልአሳዩ ድረስ ኃላፊነታቸውን እንደ ያዙ እንዲ ቀጥሉ ማድረግ ፣ በሕግ መወሰኛው ቤት ውስጥ ሕዝቡ በመረጣቸው ሰዎች እንዲወከል መደረጉ ፤ አዲስ ማሻሻያዎች ናቸው ወይንም ትርጉም በእሚሰጥ መልኩ የተሻሻሉት በእኛ ዘመን ነው ። እነርሱም ደግሞ ፤ የሕዝባዊ መንግሥት ታላቅነት የእሚጠበቅበት መላዎች ፤ ኃይለኛ መላዎች እና ጉድለቶቹ የእሚታረሙበት ወይንም እስከ እነ አካቴው የእሚወገዱበት መንገድ ናቸው ።”
“The regular distribution of power into distinct departments; the introduction of legislative balances and checks; the institution of courts composed of judges, holding their offices during good behavior; the representation of the people in the legislature, by deputies of their own election; these are either wholly new discoveries, or have made their principal progress towards perfection in modern times. They are means, and powerful means, by which the Excellencies of republican government may be retained, and its imperfections lessened or avoided. [70]“
ስለ እዚኽ ፦ በእዚኽ መሠረት ፤ ዴሞክራሲን ለማስቻል ወይንም የዴሞክራሲ እንዴታ ጥያቄን ለመመለስ ፤ የእሚከተሉት ዓይነት የዴሞክራሲያዊ ስረዓት መዋቅር መሰረቶች ያስፈልጋሉ ፦
ወደ አቅም ግንባታው ስንመጣ ፤ መዋቅር ወይንም ስረዓት ፤ መዋቅሩን እና ስረዓቱን በአግባቡ የተረዳው የሰው ኃብት እስከ አለ ድረስ ብቻ ነው ውጤታማ መኾን የእሚችለው ።
አንዳንድ ግዜ እንዲያውም ጥሩ የማስፈፀም አቅም የአላቸው ስረዓቶች ፤ የስረዓታቸውን መዋቅራዊ ክፍተት በጥሩ አፈፃፀም ሊሸፍኑት ባይችሉም እንኳን ፤ የተሻለ ሥራ መሥራት ይችላሉ ።
ይኽም በመኾኑ በአንዲት ሐገር ፤ እስከ ዛሬ ከእሚታወቁት ፖለቲካዊ አወቃቀሮች ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ፤ የነፃነት ዴሞክራሲ ውጤታማ እንዲኾን ፤ ያችኽ ሐገር ዜጎቿን በቀለም ትምሕርት በማስተማር ፣ ትምህርት እና የኃሳብ ልውውጥን የእሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን በማምጣት ፣ ወዘተ ፤ የዜጎቿን አቅም መገንባት አለባት ።
እነ እዚኽ ከላይ የተቀመጡ ፤ ዴሞክራሲ እንዴት ለእሚለው ኃሳብ የተቀመጡ ኃሳቦች በጣም የተለመዱ እና ብዙ ሰው የእሚያውቃቸው ናቸው ። እነ እዚኽ የዴሞክራሲ እንዴታ መንገዶች የእሚታወቁ ብቻ ሰአይሆን ፤ በተለያዩ ሐገራት ተተግብረው ኖረው ፤ እንደ እሚጠበቀው የዜጎችን ህይወት እና ንበረት በአግባቡ መከላከል ሲሳናቸው እና አሳጪ የዴሞክራሲ ምሳሌ ሲሆኑ የእሚታይበት አጋጣሚ ቀላል ስለ አልሆነ ፤ እንዴታዎቹ እና አንዳንዴ ዴሞክራሲም የአለውን ፋይዳ አንዳንዶች ይጠራጠራሉ ።
ሆኖም ግን ፤ የብዙ ሐገሮች አወቃቀር ላይ ላዩን ይኽንን ቢመስልም ፤ ሕገ መንግሥታቸው እና ስርዓታቸውን ጠጋ ብለን ስን አየው ፤ እነ እዚኽ በተነጻጻሪነት ግልጽ እና ቀላል የዴሞክራሲ እንዴታ ኃሳቦች ፤ ሆን ተብለው እሚደናቀፉበት አግባብ ብዙ ነው ።
ይኽ በኢትዮጵያም ፤ ዘመናዊ ሕገ መንግሥት መርቀቅ ከጀመረበት ከ1923 ዓ.ም. አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ እውነት እንደ ሆነ ፤ የኢትዮጲያን ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ኺደት በእሚዳስሰው በመጽሐፉ ሦሥተኛው ምዕራፍ ላይ እና ሕዝባዊ ሕገመንግሥት በእሚለው 4ኛው የመጽሐፉ ምዕራፍ ስር በዝርዝር እናየዋለን ።
ይኽን ክፍል ስናጠቃልል ፦ ለዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ፤ የሐገር እንደምታ ፦ ሐገር ማለት ሰዎች ፤ ተፈጥሮዋዊ የሆነውን መብታቸውን በተፈጥሮ ሕግ ገርተው ፤ በህይወት ለመጠ፟በቅ እና ለህይወት የእሚያስፈልጋቸውን ንብረት በእሚመስላቸው መንገድ ለማግኘት ፤ የሌሎችን ተመሳሳይ በህይወት የመጠበቅ እና ለህይወት የእሚያስፈልጋቸውን ንብረት በመስላቸው መንገድ የመፈለግ መብት ሳይ አደናቅፉ ፤ የእሚንቀሳቀሱባት እና ይኽንንም የተፈጥሮ መብታቸውን ፤ የተፈጥሮ ሕግ ነፀብራቅ በሆነ ሕግ ፤ አክብሮ የእሚያስከብር መንግሥት ያለባት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የእምትታወቅ እና መኖሪያ ክልል ድንበር ነች ።
[1] አንዳንድ ሰዎች ፤ በሪፐብሊክ ውስጥ በሶቅራጠስ ስም የተነፀባረቀው ኃሳብ የፕሌቶ የእራሱ እንጂ የሶቅራጠስ አይደለም የእሚሉትን ታሳቢ በማድረግ ነው ፤ የፕሌቶ ኃሳብ እያልኩ ማቀርበው እንጂ ፤ በሪፐብሊክ መጽሐፍ ውስጥ ፕሌቶ ሶቅራጠስ አለ ብሎ ነው ኃሳቦቹን የእሚያስቀምጠው ፤ አርስቶትልም የፕሌቶን መጽሐፍ በእሚኃይስበት ግዜ ሶቅራጠስ እንደ ተናገራቸው ነው የእሚለው ።
[2] አርስቶትል በዋናነት የከተማ መንግሥታት ወይንም በእንግሊዘኛው city states በእሚባሉት አውድ እያወራ ነው ፤ ይኽም ማለት ለአርስቶትል ትልቅ የሕዝብ ቁጥር ማለት ቢበዛ 10 እና 20 ሺ ነው። ስለ እዚኽ ፦ በአርስቶትል እምነት በጣም ሰፋ አድርገነው ፤ ከ20 ሺ በላይ ነዋሪ የአለው ከተማ ወይንም መንግሥት በስረዓት ሊመራ አይችልም ማለት ነው።
[3] ሆብስ ዮፍታኼ ልጁን እንደ ሰዋት የእሚለው ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ፤ በመጽሐፈ መሣፍንት ምዕራፍ 11 ላይ በአለው ታሪክ መሠረት ፤ እስራኤልን እንዲያንድን በእስራኤል ሕዝብ የተጠራው እና በእስራኤል ላይ የነገሠው ዮፍታኼ ፤ ወደ ጦርነት ከመወጣቱ በፊት ፤ በመጽሐፈ መሣፍንት 11፡31 ላይ “ከአሞን ልጆች ዘንድ በደኅና የተመለስኹ ግዜ ፥ ሊገናነኝ ከቤት ደጅ የእሚመጣው ማንኛውም ለእግዚአብሔር ይሆናል ፤ ለእሚቃጠል መስዕዋት አቀርበዋለኹ ብሎ ለእግዚአብሔር ስዕለት ተሳለ።” በእሚለው መሠረት ፤ ከጦርነቱ በድል ሲመለስ ፤ ሴት ልጁ ልትቀበለው ከቤት በመውጣቷ ፤ ለአምላኬ ስለት ተስያለሁና ብሎ መስዕዋት አድርጎ የአቀረበበት እና ልጁም ለእግዚአብሔር ከተሳልክ እኔም በፈቃዴ እሰዋለኹ ብላ የተሰዋችበት ታሪክ ነው። መጽሐፍ ቅዱሱ በሕግ መጽሐፍ ላይ ልጅህን መስዕዋት አድርገህ እንደ አታቀርብልኝ ግን ይላል ፤ ዘጸዓት 34፡20 “የልጅህንም በኩር ኹሉ ትዋጀዋለህ።” እንደገናም በዘዳግም 18፡9 እስከ 11 በአለው ክፍል ላይ በግልጽ “አምላክህ እግዚአብሔር ወደ እሚሰጥህ ምድር በገባህ ግዜ ... ወንድ ልጁን ሴት ልጁን በእሳት የእሚያሳልፍ ፥ ... በአንተ ዘንድ አይገኝ።” ይላል።
[4] ይኽ የዳዊት እና የኦርዮን ታሪክም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ፤ በመጽሐፈ ሳሙኤል ካልዕ ምዕራፍ 11 ላይ የእሚገኝ እና ንጉሥ ዳዊት ፤ የኦርዮን ሚስት ቤርሳቤህ ከዳዊት እንደ ጸነሰች እንደ አያውቅ ሲል ኦርዮንን የአስገደለበት ታሪክ ነው።