
በእዚኽ ሐገር በእሚለው ምዕራፍ ፤ የተለያዩ ፖለቲካዊ ርዕዮቶችን በስፋት የቃኝንበት ምክንያት ፤ ፖለቲካዊ ርዕዮቶች ሐገር እና ሐገርን የእሚያስተዳድር መንግሥት የእሚዋቀርበትን አግባብ መተንተን ሥራቸው በመሆኑ ፤ ስለ ሐገር የእሚኖረን ግንዛቤ ፤ በእምንይዘው ፖለቲካዊ ርዕዮት የእሚወሰን መሆኑን ለማስረገጥ እና ይኽም መጽሐፍ ሐገርን የእሚረዳበት እና የእሚያቀርብበት አግባብ የነጻነት ዴሞክራሲው ወይንም በእኔ አሰያየም የሕገክራሲው የሐገር ትርጉም ነው ለማለት ነው።
ይኽም እውነታ ከእሚያስያን ኃቆች መካከል ፦
የእሚወሰን መሆኑን ነው።
በእርግጥ ሐገር ሰው ሰራሽ ውቅር ነች ስንል ፤ በዓለማችን ላይ በቅድመ እቅድ ሐገር እንፍጠር ተብለው የተፈጠሩ ሐገራት እጅግ በጣም ጥቂት መሆናቸውን ወይንም አብዛኛዎቹ ሐገራት ሰው በተፈጥሮዋዊ ባሕሪው ምክንያት በውዴታ ግዴታ በደመ ነፍሳዊ መነዳት ተነድቶ የፈጠራቸው መሆናቸው በመዘንጋት ሰአይሆን ፤ ሐገራት በድንገት ወይንም በእቅድ ይፈጠሩ ፤ በሐገራቱ ኽልውና እና ቀጣይነት ላይ ፤ በውስጥም በውጭም ያሉ ሰዎች ፤ የአላቸው ሚና የአንበሳውን ድርሻ የእሚወስድ መሆኑን ለማስረገጥ ነው። ሐገር የሰው ልጆች ተግባር ውጤት ነች ።
ለምሳሌ ፦ አርስታትል ሰው በአፈንጋጭነት ከማሕበረሰብ የተነጠለ ሕይወት ሊኖር ቢችልም በአብዛኛው ሰው ከብቸኝነት ይልቅ በማሕበር መኖርን መርጦ ማሕበረሰብን የእሚቀላል እና የማሕበረሰብ አባል መሆኑም በኹሉም መመዘኛ ለእዛ ሰው የተሻለ በመሆኑ ፤ ማሕበረሰብ ወይንም ሐገር ተፈጥሮ ነች ይላል ፦
“ስለ ሰው እያወራን ይኹን ፣ ስለ ፈረስ ወይንም ስለ ቤተሰብ ፤ አንድ ነገር የእድገት ኺደቱን ጨርሶ የእሚኾነውን ነገር ተፈጥሮው ነው እንላለን ። ከእዚያኽም በአሻገር ፤ የአንድ ነገር የመጨረሻ ምክንያቱ እና ግቡ የተሻለው ነው ፤ እናም ራስን መቻልም የመጨረሻው እና ተመራጩ ነው ።
ከእዚኽም የተነሳ ርጋታው (መንግሥቱ ፣ ሐገሩ ፣ ብሔራዊው ወይንም ብሔሩ) የተፈጥሮ ፍጥረት መኾኑ ግልፅ ነው ፣ …”
“For what each thing is when fully developed, we call its nature, whether we are speaking of a man, a horse, or a family. Besides, the final cause and end of a thing is the best, and to be self-sufficing is the end and the best.
Hence it is evident that the state is a creation of nature, ... [1]“
ማሕበረሰብን መመሥረት የሰው ተፈጥሮ ነው ከማለት ይልቅ ይኽን የአርስታትልን አባባል ወይንም ማሕበረሰብ ተፈጥሮ ነው የእሚለውን አባባል ትክክል ነው ብለን ከተቀበልን ፦ በስሕተት የተመሠረተው ጋብቻም ፣ የንግድ ማሕበሩም ፣ የሽፍታ ስብስቡም ፣ የሙዚቃ ባንዱም ፣ የስፖርት ክለቡም ፣ ወዘተ ፤ በአጠቃላይ የሰው ልጅ አንዳችን ግብ ታሳቢ አድርጎ የእሚያቋቁማቸውን ማሕበራት በሙሉ ተፈጥሮ ናቸው ልንል ነው። ይኽ ግን ትክክል አይደለም።
ማሕብረሰብ በጠቅላላው የሰው ልጅ የእሚመሰርታቸው ሌሎች ንዑስ ማሕበራት በተናጠል ፤ የሰው ተፈጥሮዋዊ ባሕሪ ላይ የተመሠረተ ፤ ሰው ሰራሽ ውቅራት እንጂ ተፈጥሮዋዊ ውቅር አይደሉም ፤ ለእዚኽም ማሕበረሰብ እና ሌሎች የሰው ልጆች የእሚያቋቁማቸውን ማሕበራት ፤ ሰው ሰራሽ ከአልሆኑ ተፈጥሮዋዊ ውቅሮች ጋር በማነጻጸር መረዳት እንችላለን።
ለምሳሌ ፦ የፈረስ ድንጉላው ወደ ሰጋር ፈረስነት የማደጉን ኺደት የመምረጥ ፣ ቅርፁን የመቀየር ፣ የማሻሻል አቅም ወይንም ምርጫ የለውም ፤ ከእዚኽ በተጨማሪም የፈረስ ድንጉላ አድጎ ፈረስ በእሚሆንበት ግዜ እድገቱ በኹሉም መመዘኛ ፤ ቢያንስ ለእሚጠቀምበት ሰው ፤ ከድንጉላነቱ ግዜ የተሻለ ነው ።
ስለ ሰው ማሕበረሰብ ግን በተመሳሳይ እንደ እዚኽ ማለት አይቻልም ። ምክንያቱም ፦ የሰው ማሕበረሰብ ከተፈጥሮዋዊ ውቅሮች በተለየ ፤ በውቅር አህዶቹ ወይንም በማሕበረሰቡ አባላት ግንዛቤ ልክ ጥራቱ የእሚወሰን እና በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ለረዥም ግዜ የተስተዋሉት የማሕበረሰብ አወቃቀሮችም ፤ ለማሕበርሰቡ አባላት ከእሚያበረክቱት ጥቅም ይልቅ ፤ የጉዳት ምንጭ በመሆን የሰው ልጅ የሰቆቃ ምንጭ የሆኑበት ግዜ ቀላል አይደለም።
ማሕበረሰብ እንደ ፍጥረታዊ አካል ፤ ተፈጥሮ በራሷ ፕሮግራም ገንብታ የእምታመጣው በአለመኾኑም ነው ፤ ማሕበረሰብ በትክክል ከተገነባበት ግዜ በላይ በትክክል የአልተገነባበት ግዜ የእሚበልጠው ።
የግንባታ ኺደቱን ተፈጥሮ ብቻ የእማይወስነው ውቅር ተፈጥሮ ሊኾን አይችልም ፤ እንደ እዛ ከአልኾነ ፦ ቤቱም ፣ ሕንፃውም ፣ መኪናውም ፣ ኼሊኮፕተሩም ፣ በግዳጅ የተመሠረተው ትዳር (ቤተሰብ) ፣ የንግድ አጋርነቱም ፣ ወዘተ ፤ ተፈጥሮ ሊኾን ነው ።
በእርግጥ የተፈጥሮ ሳይንስ ሳይንቲስቶች ፤ ሳይንስ ሊኖር የእሚችለውን ወይንም መሆን የአለበትን ወደ ብርኃን ወይንም ወደ መሆን ያመጣል እንጂ አዲስ ነገር አይፈጥርም እንደ እሚሉት ፤ ማሕበረሰብም መሆን የአለበት መሆኑን የደነገገው ተፈጥሮ ነው።
ሰው ራሱን ስላልፈጠረ ማሕበረሰባዊነቱንም አልፈጠረውም ወይንም ማሕበረሰባዊ ፍጥረት ልኹን አልኹን ብሎ መምረጥ አይችልም።
ለምሳሌ ፦ ኼሊኮፕተር እንዲፈጠር ወይንም መሆን እንዲችል ወይንም ወደ መሆን እንዲመጣ የተፈጥሮ ድንጋጌ ነው ፤ የሳይንስም ሥራ ይኽን እምቅ እና የተሰወረ የተፈጥሮ ድንጋጌ ከተሰወረበት የማውጣቱን ሥራ ይሰራል ፤ ሳይንስ ይኽን ሥራ ባይሰራ ግን ፤ ምንም እንኳን የተፈጥሮ ድንጋጌ ኺሊኮፕተርን ወደ መሆን እንዲመጣ የእሚያስችል ቢሆንም ፤ ኼሊኮፕተር ሳይመጣ ፥ ሳይሆን መቅረቱ አይቀርም ፤ ለእዛም ነው ፤ ኼሊኮፕተር ሳይፈጠር ብዙ ሺ ዓመታት ያለፉት።
ይኽም ማለት ፤ ምንም እንኳን ማሕበረሰብ አርስታትል እንደ አለው ፍጥረታዊ አካል በአይሆንም ፤ ከሰው ተፈጥሮዋዊ ፍላጎት የእሚመነጭ በመሆኑ ፤ ስለ እዚኽም ለመመስርቱ ተፈጥሮዋዊ መሠረት ወይንም አስገዳጅነት የአለው እና የአወቃቀሩም አግባብ ላይ የውቅሩ የግንባታ አህድ የሆኑት ሰዎች ግንዛቤ የአንበሳ ድርሻ የአለው መሆኑ ፤ ለኹሉም የፖለቲካ ርዕዮቶች ፤ አኹን ያሉትን ሉዓላዊ ሐገራትን የእሚቀባሉትም ሆኑ ሐገር የእሚባል ውቅር አያስፈልገንም ፥ ዓለም ዓቀፍ ወንድማማች መሆን አለብን የእሚሉት ፤ የህልውናቸው ምንጭ እና ሐገራትም የአላቸው የሰብዓዊ እና የቁሳዊ ልማት ደረጃቸው በከፍተኛ ደረጃ በተዋቀሩበት ርዕዮት አንጻር የእሚወሰን ነው።
ኺሊኮፕተር እንዲሆን የተፈጥሮ ድንጋጌ ቢሆንም ፤ ኹሉም ማሕበረሰብ ወይንም ሰብ ኺሊኮፕተርን ወደ መሆን የእሚያመጣበት እውቀት የለውም ፤ ይኽም ብቻ ሳይሆን ፤ ወደ መሆን የመጡት ኹሉም የኺሊኮፕተር ዓይነታት እኩል አቅም እና ጠቀሜታ አላቸው ማለትም አይደለም።
ከእላይ እንደ አልነው ማሕበረሰብ በተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ በኃሪ ነጂነት መዋቀሩ የእማይቀር መሆኑ እና የአወቃቀሩም አግባብ ላይ ሰዎች እንደ አላቸው ግንዛቤ መጠን በፈለጉት መንገድ ሊያዋቅሩት መቻላቸው ፤ ኹሉም ሰው ትክክለኛውን ወይንም የተሻለን ኃሳብ አሳቢ በአለመሆኑም ፤ ሐገራት የእሚመሩበት ርዕዮት የማሕበረ ኢከነሚ የእድገት ደረጃቸውን የእሚወስን ሆኗል።
ሐገር እና ተቋሞቿ በዴሞክራሲ (በነጻነቱ ዴሞክራሲ አግባብ) ሲዋቀሩ ፤ ከሌሎቹ ከቃኘናቸው ርዕዮቶች በተለየ እና በተሻለ ኹኔታ ፤ እዛያች ሐገር ውስጥ የእሚኖሩ ዜጎች የእሚከተሉትን ሦሥት ጥቅሞች ያገኛሉ ፦
የነጻነቱ ዴሞክራሲ በእሚተገበርበት ግዜ ሐገር ለዜጎቿ የእምትሰጣቸውን እነ እዚኽን ጥቅሞች በዝርዝር ከማየታቸን በፊት ፤ የነጻነቱ ዴሞክራሲ እነ እዚኽ መልካም ትሩፋቶች ለዜጎች ማቅረብ የቻለው ፤ የዜጎችን የማሕበረሰብ አህድነት በመቀበሉ በመሆኑ ፤ የነጻነቱ ዴሞክራሲ ዜጎች የማሕበርሰብ አህድ ናቸው ሲል ምን ማለት እንደሆነ በመመልከት እንጀምር።
አህድ ስንል ፤ የመጨረሻው ፣ የእማይከፋፈለው እና መሠረታዊው የግንባታ ፣ የአወቃቀር ወይንም የአደረጃጀት አካል ማለታችን ነው ።
በብሎኬት የእሚገነባ አንድ ቤትን እንደ ማሳያ ብንወስድው ፤ ብሎኬቱ የቤቱ የግንባታ አህድ ነው ። ምክንያቱም ፦ ቤቱ እንደ ቤት መቆም የቻለው እና የእሚላበሰውን ማንኛውም ገፅታ የተላበሰው ወይንም የእሚሰጠውን አገልግሎት መስጠት የቻለው ፤ ብሎኬቶች በመሰብሰባቸው እና ገፅታው እና ግልጋሎትም ከእያንዳንዱ ብሎኬት ገፅታ እና ግልጋሎት የእሚመነጭ በመሆኑ ነው ።
ምንም እንኳን ቤቱ እንደ ቤት አንድ ግዜ ከቆመ በኋላ ፤ አንድ ብሎኬት ወይንም የተወሰኑ ብሎኬቶች በቤቱ ላይ የእሚኖራቸው ሚና ቢቀንስም ፤ ቤቱ ግን ቤት ሆኖ የቆመው ፤ በብሎኬት አህድነት ነው ።
ከእዚኽም የተነሳ ፤ ቤቱ ወይንም አንድ ሌላ ክስተት በአንድ አጋጣሚ ፥ የቤቱ የግንባታ አህድ የሆኑትን ብሎኬቶች የእሚጎዳ ወይንም ከመሠረታዊ በኃሪያቸው ጋር የእሚቃረን ነገር ማድረግ ቢጀምር ወይንም ለምሳሌ ፦ ብሎኬቶቹ በአንድ አጋጣሚ ወደ አሸዋነት እየ ተለወጡ ቢኼዱ ፤ ቤቱ ቤት መሆን እንደ እሚያቆም ጥያቄ የለውም ።
አንድ ማሕበረሰብም ፤ አንድ ግዜ ታንጬአለሁ እና የግንባታ አህዶቼ የሆኑትን ግለሰቦች ተፈጥሮዋዊ መብት አላከብርም ቢል ፤ ተፈጥሮዋዊ መብታቸው እንደ እሚጥስበት አግባብ ፤ ከተበላሸ ማሕበረሰብ እስከ ተበታተነ ማሕበረሰብ የእሚለያይ ችግር ውስጥ ራሱን ያስገባል ።
የሰው ልጅ የሐገር አህድ መሆኑን በእሚጠቁም መልኩ ማሕበረሰብን በቀዳሚነት በጥሩ ኹኔታ ከገለፁ የፖለቲካ ሊህቃን መካከል ቀዳሚ የሆነው አርስታትል ፤ ማንኛውም ማሕበረሰብ የሰው ልጅ መልካም የእሚለውን ነገር የማግኘት ፍላጎት ውጤት ከኾኑት ነገሮች አንዷ ነች በእሚል እንደ እዚኽ አስቀሞታል ፦
“የትኛውም መንግሥት (ርግ (እርግ) ፣ ሕዝብ ፣ ሐገር ፣ ብሔር) አንድ ዓይነት ማሕበር ነው ፤ የትኛውም ማሕበር ደግሞ አንድ የሆነ መልካም የእሚባል የጋራ ግብን ታሳቢ የአደረገ ነው ፤ ምክንያቱም ፦ የሰው ግብሩ ኹሉ መልካም ብሎ የእሚያስበውን ለማግኘት ከመፈለግ የእሚነሳ በመሆኑ ።”
«Every state is a community of some kind, and every community is established with a view to SOME GOOD; for mankind always act in order to obtain that which they think good. [1]»
የሰው ልጅ በተናጠል የማሕበረሰብ አህድ ያደረጉት ደግሞ በተፈጥሮ የተላበሳቸው ሰብዓዊ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ባሕሪያት ናቸው።
እነ እዚኽን ባሕሪያቱን ለማወቅ ፤ ከእዚኽ የአርስታትል ገለጻ ብንጀምር ፤ የሰው ልጅ መልካም ብሎ የእሚያስበውን ነገር ለመከወን መነሳት መቻሉ ፤ ለሰው ልጅ ማሕበረሰብ መመሥረት ምክንያት ከሆኑ ወይንም በሰው ልጅ ተፈጥሮው ውስጥ ከእሚገኙ እና የሰውን ልጅ የማሕበረሰብ አህድ ከአደረጉት ባሕሪያት ውስጥ አንዱ መሆኑን እንገነዘባለን።
የሰው ልጅ መልካም የእሚለውን ነገር በእማያቆም መልኩ ከመፈለጉ በአሻገር ፤ ማሕበራዊ ፍጥረት ወይንም የማሕበረሰብ አህድ ያደረጉት ሌሎች ተጫማሪ ባሕሪያትም አሉት።
ከእነ እዚኽም መካከል የእሚከተሉትን መጥቀስ እንችላለን ፦
የሰው ልጅ እነ እዚኽን ሰብዓዊ በኃሪያት በአይላበስ ኖሮ ፤ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ዓለም ዓቀፍ አጋርነት ያሉት ፤ ውስብስብ ፖለቲካዊም ሆነ ኢከነሚያዊ ሰባዓዊ ማሕበራት መፈጠር አይችሉም ነበር ።
ያም በመሆኑ ፤ ማሕበራዊ ተቋሞቻችን በሙሉ በሰው ሰብዓዊ በኃሪ ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው ፤ ሰብዓዊ ሰው የፖለቲካ እና ኢከነሚያዊ ማሕበረሰብ ብቸኛ አህድ (Unit or Building Block) መሆኑ በግልፅ ይታያል ።
ግለሰቦች የማንኛውም ሰብዓዊ ማሕበር የግንባታ አህድ ናቸው የእሚለውን አባባል ፤ ከእዚኽ በታች የተቀመጠው ስዕል በደንብ የእሚገልጸው ይመስለኛል። ይኽ ከእዚኽ በታች የአለው ስዕል ፤ በተለያየ መልኩ ስንጠቅሰው የነበረው ቶማስ ሆብስ ሌዋታን[1] በእሚል የጻፈው መጻፍ ሽፋን ላይ የእሚገኝ ስዕል ነው።ደጋግመን እንደ አልነው ፤ ምንም እንኳን ቶማስ ሆብስ ፤ ልዑሉ የጋርዮሹ ወይንም የማሕበረሰቡ ፈቃድ መገለጫ በመሆኑ ፤ ከዴሞክራሲ አንጻር ተቀባይነት በሌለው መልኩ ፤ የፍጹማዊ ስልጣን ባለቤት ሊሆን እና ለእሚሰራው ማንኛውም ጥፋት በሰው ችሎት ሊጠየቅ አይገባውም ቢልም ፤ የመጽሐፉ ሽፋን ስዕል መንግሥት ወይንም ማሕበረሰብ ፤ በግለሰቦች አሕድነት የተገነባ ፤ አንድ ማሕበራዊ ተክለሰወነት (body politic) ነው የእሚለውን ኃሳብ በጥሩ ኹኔታ ስለ እሚገልጸው ፤ ስዕሉን አስቀምጨዋለሁ።
ምስል 3 ፡ የቶማስ ሆብስ ሌዋታን!
ስዕሉ በግርድፉ እየ አሳየ የአለው ፤ ልዑሉ በሰይፉ እና በብትረ መንግሥቱ ፤ ከተማዋን ወይንም ማሕበረሰቡን እየጠበቀ ነው። ስዕሉን ጠጋ ብለን የተመለከትነው እንደ ሆነ ግን ፤ በሰይፉ እና በብትረ መንግሥቱ ከተማዋን ወይንም ማሕበረሰቡን የእሚጠብቀው ልዑል ተክለ ሰውነት የተግነባው ከእያንዳንዱ የከተማዋ ነዋሪ እንደ ሆነ ይታያል።
የማንኛውም ማሕበረሰብ የግንባታ አህድ የሆነው የሰው ልጅ የተላበሳቸው ልዩ ባሕሪያት ደግሞ ፤ የሰውን ልጅ ማሕበረሰብ ከሌሎች የማሕበር ዓይነታት በሙሉ የተለየ ባሕሪያት ያላብሱታል ።
ምንም እንኳን ሌሎች እንሰሳት በጋራ የመኖር እና የመሰራት ባሕሪ የአላቸው ቢሆንም ፤ የሰው ልጅ ማሕበር ግን በሰው ልጅ ልዩ ተፈጥሮዋዊ ባሕሪያት ምክንያት ፤ ከሌሎች ፍጥረት ኹሉ የላቀ ነው ። ይኽንን ኹኔታ ጥንታዊው አርስታትል እንደ እዚኽ አስቀምጦታል ፦
“ሰው ከንብ ወይንም ከማንኛውም በጋርዮሽ ከእሚኖር ፍጥረት በላይ ማሕበራዊ መሆኑ ግልፅ ነው ። ተፈጥሮ ምንንም ነገር በከንቱ አታመጣውም እያልን ብዙ ግዜ እንላለን ፤ ከእንስሳት ኹሉ ለይታ የመናገር ችሎታ የሰጠችው ደግሞ ለሰው ልጅ ነው ። ህመም እና ደስታን ለማመልከት የእሚጠቅም ድምፅ በሌሎች እንስሳት ቢኖርም (ተፈጥሮ ለእንሰሶቹ ያስቻለቻቸው ፤ ህመም እና ደስታን እንዲለዩ እና እነ እዚኹኑ ለሌሎች ማሰማት እንዲችሉ ከማድረግ ያልዘለለ ነው) ፤ ሰው ጋር የአለው የንግግር አቅም ግን ፤ ተገቢ እና ተገቢ የአልሆነውን ነገር ፣ እንደ እዛውም ፍትኃዊ እና ኢፍትኃዊ የሆነውን ነገር እንዲያስታውቅ ነው ። “
“Now, that man is more of a political animal than bees or any other gregarious animals is evident. Nature, as we often say, makes nothing in vain, and man is the only animal who she has endowed with gift of speech. And whereas mere voice is but an indication of pleasure or pain, and is therefore found in other animals (for their nature attains to the perception of pleasure and pain and the intimation of them to one another, and no further), the power of speech is intended to set forth the expedient and inexpedient, and therefore likewise the just and the unjust. [1]“
ከእዚኽ የአርስታትል ገለፃ እንደ እምንረዳው ፤ ሰው የላቀ ማሕበራዊ ወይንም ፖለቲካዊ ፍጥረት የሆነበት አንድ ምክንያት ፤ የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጥረታት በሙሉ በተለየ መልኩ የተላበሰው የቋንቋ ክህሎት እና ይኽንንም የቋንቋ ክህሎቱንም ሌላውን ከሌሎች ምድራዊ ፍጥረታት ላቅ ባለ ኹኔታ እርሱ ጋር ብቻ የእሚገኘውን የፍትሕ ግንዛቤ ለመግለፅ የእሚጠቅምበት መሆኑ አንደኛው ነው ።
ሌሎች እንሰሳት ህመምን ወይንም ደስታን ለማስተጋባት ቢጮሁም ፤ እንደ ሰው በተብራራ እና በተነተነ አግባብ ደስታን እና ኃዘንን ወይንም ፍትሕ እና በደልን ለይተው በዝርዝር አያስቀምጡም ። በእዚኽ ረገድ የሰው ልጆች ከየትኛውም ፍጥረት የተለዩ መሆናቸው እና ይኽም የሰውን ማሕበራዊ ህይወት ከሌሎች ምድራዊ ፍጥረታት ማሕበራዊ ህይወት በላይ የላቀ እንደ አደረገው ለተመልካች በግልፅ የእሚታይ ነው ።
አርስታትል የሰው ልጅ ፤ ህመም እና ደስታውን ከሌሎች እንሰሳት በላቀ መልኩ የእሚገልፅበት ቋንቋ አለው ሲል ፤ አንድ የሆነውን ቋንቋ እያለ ሰአይሆን ፤ የሰው ልጅ በአጠቃላይ ኃሳቡን በተብራራ መልኩ በቃል የመግለፅ ክህሎቱን እያለ መኾኑም ሊሰመርበት ይገባል ።
በጠቅላላውም የሰውን ልጅ ፤ የማሕበረሰብ አህድ ያደረጉትን ሰብዓዊ ባሕሪያት ፤ አንዳቸውም በግዜ አመጣሽ የሰው ልዩነቶች ፤ ለምሳሌ ፦ ኃይማኖት ፣ ባህል ፣ ቋንቋ ፣ ወዘተ ፤ ላይ ወይንም ተፈጥሮዋዊ በሆኑ ፤ ለምሳሌ ፦ የቆዳ ቀለም ፣ ፆታ ፣ ቁመት ፣ ወዘተ ፤ የተገደቡ አለ መሆናቸው ይታያል ።
በተጨማሪም የሰውን ልጅ ማሕበራዊ ወይንም ፖለቲካዊ ፍጥረት የአደረጉት ፤ የፍትሕ ግንዛቤው እና የቋንቋ ክህሎቶቹ ብቻ ሰአይሆኑ ፤ ከላይ ለመዘርዘር እንደ ሞከርነው ፤ መልካም የእሚለው ርዕይ የአለው መሆኑ እና ይኽንንም መፈለጉ ፣ ይኽንንም መፈለጉ ብቻ ሰአይሆን ፤ ይኽንን ፍላጎቱን ወይንም እነ እዚኽን ፍላጎቶቹን ማሳካት የእሚችልበት ፈርጀ ብዙ ክህሎቶች ፤ ከሌላው ከማንኛውም ምድራዊ ፍጥረት በላቀ መልኩ መላበሱም ነው ።
የሰው ልጅ በእዚኽ መልኩ ፤ ዘርፈ ብዙ ፍላጎት እና ፍላጎቶቹንም ማሟያ የተለያዩ ክህሎቶች መላበሱም ከሌላው ማንኛውም ምድራዊ ህያው ፍጡር በተለየ በባሕሪው የተወሳሰበ እና የላቀ ኢከነሚያዊ መዋቅር እንዲኖረው አድርጎታል። የሰው ልጅ ማሕበረሰብ የአለው ኢከነሚያዊ ደርዝ በሌላ በማንኛውም ማሕበራዊ ምድራዊ ህያው ፍጡር ማሕበር ውስጥ ከእሚገኝበት ዓይነት እጅግ የተለየ ነው።
የሰው ልጅ ማሕበረሰብ ኢከነሚያዊው ደርዝ በእዚኽ መልኩ እጅግ የተወሳሰበ እና የላቀ እንዲሆን የአደረገው ፤ አንደኛው ምክንያት እነ እዚኽ ዘርፈ ብዙ ክህሎቶች ፤ ከሰው ሰው በተለየ መልኩ ወይንም የሥራ ክፍፍልን ግድ በእሚል መልኩ የተላበሳቸው መሆኑ ነው።
ይኽ በተለያዩ ግለሰቦች ዘንድ የእሚገኝ የተለያዩ ዓይነት ክህሎት ባለቤት የመሆን ኹኔታ ደግሞ ፤ በኢከነሚው መስክ ፤ የሰው ልጅን በጋራ የማምረት አቅም በብዙ እጥፍ እንዲጨምር የእሚያደርግ ነው።
በሰብዓዊ ሰዎች መካከል የአለው የሞያ እና የክህሎት ልዩነት የማሕበራዊ ምርት እድገት ምንጭ መሆኑን ፤ በተመዘገበ ታሪክ ፤ ለመጀመሪያ ግዜ የተገነዘበው ሰው ፤ የግሪኩ ፕሌቶ እንደ ሆነ ብዙዎች የእሚስማሙበት ሲሆን ከእዛኽ በመቀጠል በተብራራ ኹኔታ ያስቀመጠው ፤ የዘመናዊ ኢከነሚክስ ሳይንስ አባት የእሚባለው አዳም ስሚዝ ነው ።
ፕሌቶ ፤ ሪፐብሊክ በእሚለው መጽሀፉ ላይ ፤ ስለ ሞያዊ ክፍፍል እና እንደ ምታው እንደ እዚኽ ይላል ፦
“… ለተለያየ ሥራ የተመቸ የተለያየ ተፈጥሮ (ስጦታ) በውስጣችን አለ ፤ ኹላችንም አንድ ዓይነት ስለ አይደለን ። … ይኽም ከሆነ ደግሞ ፤ እያንዳንዱ ሰው ተፈጥሮ በአደለችው ሞያው ላይ አተኩሮ ሌላውን ለሌላ ሞያተኛ ሲተወው ፤ ጠቅላላ ማሕበራዊ ምርት በብዛት ፣ በቀላሉ እና በጥራት ይጨምራሉ ማለት እንችላለን።”
“…that we are not all alike; there are diversities of natures among us which are adapted to different occupations …And if so, we must infer that all things are produced more plentifully and easily and of a better quality when one man does one thing which is natural to him and does it at the right time, and leaves other things. [22]“
ይኽን ፕሌቶ ፤ ስለ ሐገረ ግንባታ በእሚወያይበት ወቅት ያስቀመጠው ኃሳብ እንደ እሚያሳየን ፤ ምንም እንኳን ተፈጥሮዋዊ እኩል ነፃነት ቢኖረንም ፤ በተፈጥሮ አንድ ዓይነት ሞያ እና ክህሎት ስለ ሌለን ፤ በተፈጥሮ የተካንበት ነገር ላይ እኛ አተኩረን ፤ ሌላውን ነገር የማምረት ጉዳይ እንደ እኛው ነገር ግን በተለየ መንገድ ለተካነው ሰው ስንተውለት ፤ ጠቅላላው ማሕበራዊ ምርታችን ፦ በመጠንም ፣ በዓይነትም ፣ በጥራትም እጅግ ይጨምራል ይላል ።
ይኽንኑ ፤ የፕሌቶን ኃሳብ ፤ በተግባራዊ ምሳሌ እና በበለጠ በተብራራ መልኩ ፤ የዘመናዊ ኢከነሚክስ ሳይንስ አባት የእሚባለው ፤ አዳም ስሚዝ ፤ በእርሱ ዘመን መርፌ ቁልፍ በእሚመረትበት የሥራ ኺደትን ማሳያ በማድረግ በእሚከተለው መልኩ አስቀምጦታል ፦
“በጣም ቀላል የእሚባለውን እና ነገር ግን የሥራ ክፍፍሉ በግልፅ የእሚስተዋልበትን ፤ በብዛት የማምረት ምሳሌ የሆነውን ፤ የመርፌ ቁልፍ አምራቾች የምርት ኺደት ምሳሌ አድርገን እንውሰድ። በእዚኽ ሞያ ያልሰለጠነ አንድ ሠራተኛ (ይኽንንም ሞያ ራሱን የቻለ አንድ የሞያ ዘርፍ እንዲሆን የአደረገው የሥራ ክፍፍሉ ነው) ፥ ወይንም መርፌ ቁልፉን ለማምረት የእሚውለውን ማሽን አጠቃቀም የእማያውቅ ሰው (በመጀመሪያ ደረጃ ማሽኑ እንዲ ፈጠር የሥራ ክፍፍሉ ምክንያት ሆኖ ሊሆን ይችላል[2]) ፤ በቀን ፥ ምናልባት በብዙ ትጋት አንድ መርፌ ቁልፍ ሊያመርት ይችላል ፤ ኃያ መርፌ ቁልፍ እንደ እማያመርት ግን ርግጠኞች ነን ። ነገር ግን በእዚኽ ዘመን ይኼ ንግድ/ሞያ በእሚካኼድበት አግባብ ፤ ጠቅላላ ሞያው ራሱን የቻለ ልዩ ሞያ መሆን ብቻ ሰአይሆን ፤ በውስጡ በተለያዩ ቅርንጫፎች ተከፋፍሎ ፤ ከእነዚኽ ቅርንጫፎች አብዛኛዎቹ ራሳቸውን የቻሉ ሞያዎች ሆነዋል ። አንዱ ሰው ሽቦውን ስቦ ያወጣል ፣ ሌላኛው ቀጥ ያደርገዋል ፣ ሦሥተኛው ይቆርጠዋል ፣ አራተኛው ያሾለዋል ፣ አምስተኛው መቆለፊያው ውስጥ ያስገባዋል ፤ መቆለፊያውን ለመሥራት ራሱ ኹለት እና ሦሥት ልዩ ሥራዎች ይፈልጋል ፤ ቁልፉን ከመርፌው ማያያዝ ራሱ አንድ ልዩ የሥራ መስክ ነው ፣ መርፌ ቁልፉን ማፅዳት ወይንም ነጭ ማድረግ አንድ ሌላ ሥራ ነው ፣ መርፌ ቁልፎቹን በካርቶናቸው ውስጥ ማስገባት ራሱ አንድ ራሱን የቻለ ሥራ ነው ፤ በእዚኽም መሠረት ፤ አስፈላጊው መርፌ ቁልፍን የማምረት ኺደት ፤ በእዚኽ መልኩ ወደ 18 የተለያዩ ተግባሮች ተከፋፍሏል ። አንድ አንድ ፋብሪካዎች እያንዳዳቸውን እነ እዚኽን የሥራ ክፍፍሎች በተለያየ ሰው ሲያሰሩ ፤ አንድ አንዶች ኹለቱን ወይንም ሦሥቱን ሥራዎች ለአንድ ሰው ይሰጣሉ ። እኔ ለማየት ያጋጠመኝ እንደ እዚኽ የአለው አነስተኛ ማምረቻ አስር ሰዎች ብቻ የተቀጠሩበት ነበር ፤ ከእዚኽም የተነሳ የተወሰኑት ሰራተኞች ኹለቱን ወይንም ሦሥቱን ሥራዎች ደርበው የእሚሰሩበት ነበር ። እነ እዚኽም ትናንሽ ማምረቻዎች ደካማዎች ቢሆኑም እና ማሽን በግብር ውጣ ዓይነት ቢቀርብላቸውም ፤ ከልባቸው ሲሰሩ በቀን ወደ አሥራ ኹለት ፓውንድ (12*0.45=5.40 ኪሎግራም) መርፌ ቁልፍ ያመርታሉ ። በእያንዳንዱ ፓውንድ (0.45 ኪሎግራም) ውስጥ ፤ መካከለኛ መጠን የአላቸው ከአራት ሺ በላይ መርፌ ቁልፎች አሉ ። ስለ እዚኽ ፦ እነዚኽ አስር ሰዎች በቀን ከአርባ ስምንት ሺ በላይ መርፌ ቁልፍ ያመርታሉ ። ይኽም ማለት ፤ ከአስር አንድ እጅ በመሆን እያንዳንዱ ሰው በቀን ከአራት ሺ ስምንት መቶ በላይ መርፌ ቁልፎች እንደ እሚያመርት መታሰብ አለበት ። ነገር ግን ፤ በሞያው ሳይሰለጥኑ ፤ ኹሉም ለእየብቻቸው በተናጠል ቢያመርቱ ኖሮ ፤ ትክክለኛው የሥራ ክፍፍል እና ቅንጅት ያስቻላቸውን አራት ሺ ስምንት መቶ ወይንም ኹለት መቶ አርባኛው የሆነውን ኃያ መርፌ ቁልፍ ምን አልባትም አንድ እንኳን በቀን ለአያመርቱ ይችሉ ነበር ። »
“To take an example, therefore, from a very trifling manufacture; but one in which the division of labour has been very often taken notice of, the trade of the pin-maker; a workman not educated to this business (which the division of labour has rendered a distinct trade), nor acquainted with the use of the machinery employed in it (to the invention of which the same division of labour has probably given occasion), could scarce, perhaps, with his utmost industry, make one pin in a day, and certainly could not make twenty. But in the way in which this business is now carried on, not only the whole work is a peculiar trade, but it is divided into a number of branches, of which the greater part are likewise peculiar trades. One man draws out the wire, another straights it, a third cuts it, a fourth points it, a fifth grinds it at the top for receiving the head; to make the head requires two or three distinct operations; to put it on, is a peculiar business, to whiten the pins is another; it is even a trade by itself to put them into the paper; and the important business of making a pin is, in this manner, divided into about eighteen distinct operations, which, in some manufactories, are all performed by distinct hands, though in others the same man will sometimes perform two or three of them. I have seen a small manufactory of this kind where ten men only were em-ployed, and where some of them consequently performed two or three distinct operations. But though they were very poor, and therefore but indifferently accommodated with the necessary machinery, they could, when they exerted themselves, make among them about twelve pounds of pins in a day. There are in a pound upwards of four thousand pins of a middling size. Those ten persons, therefore, could make among them upwards of forty-eight thousand pins in a day. Each person, there-fore, making a tenth part of forty-eight thousand pins, might be considered as making four thousand eight hundred pins in a day. But if they had all wrought separately and independently, and without any of them having been educated to this peculiar business, they certainly could not each of them have made twenty, perhaps not one pin in a day; that is, certainly, not the two hundred and fortieth, perhaps not the four thousand eight hundredth part of what they are at present capable of performing, in con-sequence of a proper division and combination of their different operations. [48]“
እነ እዚኽ እና መሰል ማብራሪያዎች እንደ እሚያስረዱን ፤ የሰው ሰብዓዊነት መገለጫ የሆነው ፤ በተለያዩ ግለሰቦች ዘንድ ያለ የሞያ ልዩነት እና ልዩ ልዩ የሞያ ደረጃዎች በሌሎች ልዩ የሰው ልጅ ሰብዓዊ እና ማሕበራዊ ባሕሪያቱ ታግዘው ፤ አንድ መልካም የእሚባልን ነገር ለማምረት በእሚቀናጁበት ግዜ ፤ መርፌ ቁልፍን የማምረትን ኺደት እንደ ምሳሌ ብንወሰድ ፤ ሰው በሞያ ክፍፍል አግባብ ሲደራጅ ፤ በነጠላ ከእሚያመርተው በላይ እስከ 240 እጥፍ የማምረት አቅሙ እንደ እሚጨምር ያሳያል ።
እነ እዚኽ ፦ ልዩ የሆኑ የሰው ልጆች ፤ ከግዜ አመጣሽ ልዩነቶች ( ኃይማኖት ፣ ኃብት ፣ የውልደት አከባቢ ፣ ጎጥ ፣ የሆነ ቋንቋ ተናጋሪነት ) ላይ ያልተመሠረቱት እና በተፈጥሮዋዊ ሰብዓዊ ልዩነቶች (ዘር ፣ የቆዳ ቀለም ፣ ቁመት ፣ ወዘተ) የእማይገደቡት እንደ የተለያዩ ክህሎቶች እና የመደረጀት ያሉት ሰብዓዊ ባሕሪያት ፤ ሰውን የማሕበረሰብ ወይንም የሐገር የግንባታ አህድ አድርገውታል ።
እንደ ሰው ፤ የማሕበረሰብ አህድ የአደረገንን ባሕሪ በአንላበስ ወይንም ሰዎች ከሌላ ሰው የእሚፈልጉት እና ሌላው ሰውም ከእነርሱ የእሚፈልገው ነገር በአይኖር ፤ ኹላችንም ከማንም ምንም ሳንፈልግ እና ለማንም ምንም ሳንሰጥ ፤ ከተወለድንበት አንስተን እስከ እምንሞት ድረስ አየሩን ብቻ እየማግን ወይንም ፍላጎታችንን ኹሉ በግል ጥረታችን ብቻ በሟሟላት መኖር ብንችል ኖሮ ሐገር አይኖርም ነበር ።
አስተሳስሮ ሐገር የእሚያደርገን ገመድ ሰብዓዊነታችን በመሆኑ ፤ የማሕበረሰባችን ወይንም የማንኛውም ሰዋዊ ተቋም መሠረት ሰብዓዊነታችን መሆኑ ወይንም ሰዎች ፣ ግለሰቦች ፣ ዜጎች ፤ ሐገርን ጨምሮ የማንኛውም ሰብዓዊ ተቋም አህድ መሆናቸው ምንም የእማያጠያይቅ ነው።
እንደ ግለሰቦች ፤ የፍላጎታችን መብዛት እና ያንንም ፍላጎት ማርካት የእሚችሉ ብዙ ክህሎቶች ባለቤት ፍጥረት መሆናችን የሐገር ፣ የብሔር ፣ Nation or Polity መገንቢያ አህድ አድርጎናል ፤ ይኽ ብቸኛ የሐገር ማስተሳሰሪያ ገመድ ደግሞ የግለሰቦች እንጂ ፤ የቤተሰብ ፣ የጎሳ ወይንም የነገድ ባሕሪ ባለ መሆኑ ፤ ሐገርን የእሚፈጥረው የዜጎች ትስስር እንጂ የማንኛውም ቡድን ትስስር አይደለም ።
የዓለም ማሕበረ ኢከነሚ (The Global Political Economy) በሰዎች ወይንም በግለሰቦች ፍላጎት እና ክህሎት ዙሪያ ይሽከረከራል።
ከእዚኽም የተነሳ ፤ በዘልማድ ፤ ሐገር ማለት የቤተሰብ ወይንም የጎሳ ወይንም የነገድ ፣ ወዘተ ፤ ስብስብ ነች ማለት ብንችልም ፤ ዞሮ ዞሮ እነ እዚኽ አደረጃጀቶች ራሳቸው በግለሰቦች ሰብዓዊ ባሕሪያት ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው እና ፋይዳቸውም ሆነ መነሻቸው ግለሰባዊ የሰዎችን ፍላጎት በግለሰባዊ ሰብዓዊ ባሕሪ የእሚነዱ በመሆኑ ፤ እርግጥኛ የሆነው የማሕበረሰብ ወይንም የሐገር አወቃቀር መግለጫ ፤ ማሕበረሰብ ወይንም ሐገር የሰዎች ስብስብ ነች ወይንም ግለሰብ የማሕበርሰብ/የሐገር አህድ ነው የእሚለው ነው ።
አርስታትል እንደ እዚኽ ይላል ፦
“የብዙ ነገሮች ውህድ እንደ ሆነ እንደ ማንኛውም ነገር ፤ ሐገር (መንግሥት ፥ ብሔራዊው) አንድ ውህድ ነው ፤ ተዋህደው የመሠረቱትም ዜጎቹ ናቸው።”
“But a state is a composite, like any other whole made of many parts; these are citizens who compose it. [1]”
ሰው በባሕሪው ፤ አየር ላይ ወይንም ውኃ ውስጥ ሰአይሆን ፤ እንደ መሬት ያለ ጠጣር ነገር ላይ ብቻ ስለ ሆነ መኖር የእሚችለው ፤ ሐገር ብለን ስንል የእሚኖርበትን መሬት ፤ ኹል ግዜ በውስጥ ታዋቂነት እንዳለ እና የእማይለወጥ እውነት (Given) ፤ ወስደነው ፦ ግለሰብ የሐገር ወይንም የማሕበረሰብ አህድ ከሆነ ፤ ሐገር ደግሞ አደረጃጀት ነች ማለት እንችላለን ።
ስለ እዚኽ ስለ ሐገር ስናወራ ስለ አደረጃጀት እያወራን ነው። ሐገር እና የተለያዩት ማሕበራዊ ተቋሞች እንዴት ቢዋቀሩ ዜጎቿ የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለን እየተወያየን ነው ማለት ነው።
መግቢያችን ላይ እንደ አልነው ፤ የተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮቶች ግን ፤ የግለስብን ወይንም የዜጋን ፤ የሐገር ወይንም የማሕበረሰብ አህድነት በአንድም በሌላም ምክንያት አይቀበሉም ።
ፅንፈኛ ሐይማኖተኛውን ብንወስደው ፤ ከኃይማኖቱ ውጭ የአለውን ሰው በሰውነቱ ወስዶ ፤ በሰብዓዊነቱ የታደላቸውን ተፈጥሮዋዊ ባሕሪያት በነፃነት ለግል ጥቅሙ እንደ አያውል የተለያዩ ክልከላ ያበጅበታል ብቻ ሰአይሆን ፤ የሐይማኖቱንም ተከታይ ቢሆን ፤ ምንም እንኳን ከኃይማኖት ኃይማኖት ቢለያይም ፤ ሰብዓዊ ባሕሪውን ወይንም መብቱን የእሚያከብርለት ፤ የሐይማኖቱ ቀኖና እስከ ፈቀደለት ድረስ ነው ።
ለምሳሌ ፦ ወንድ እና ሴትን በሰብዓዊነት የአላቸውን እኩልነት የእማይቀበል ኃይማኖት ወይንም ሴት ልጅ ከወንድ ልጅ በመሠረታዊ ሰብዓዊ ባሕሪዋ ታንሳለች ብሎ የእሚል ኃይማኖት ከአለ ፤ ሴት ልጅ ፦ ሞያ እንድ አይኖራት ፣ ወደ ፈለገችበት በፈለገችበት ሰዓት እንድ አትንቀሳቀስ ፣ እንደ ፈለገች እንድ አትለብስ ፣ ወዘተ ፤ በመከልከል ፤ ሰው ማሕበራዊ ፍጥረት ወይንም የማሕበረሰብ አህድ ነው የእሚለውን ተፈጥሮዋዊ መርህ ይጥሳል ።
በተመሳሳይ ፅንፈኛ የብሔር ፖለቲከኛውን ብንወሰድ ፤ ይኽ እና ይኽ አከባቢ ፤ የእዚኽ እና የእዚያኽ የሕዝብ ንዑሳን ተወላጅ መኖሪያ ነው ብሎ የእሚደነግግ ስለ እሚሆን ፤ በታሪክ አጋጣሚ ፤ ከእዚያኽ የሕዝብ ንዑሳን ያልተወለደ እና ያ የሕዝብ ንዑሳን የእኔ ነገድ ሰው ብቻ መኖሪያ ነው ወደ እሚለው ስፍራ ኼዶ መኖር የጀመረ ሰው ፤ ብዙ ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች መሸራረፍ እንደ እሚያጋጥመው ግልፅ ነው ።
ልክ እንደ እዛው ፋሺስታዊ መልክ የአላቸው ፦ ማርክሲዝም ፣ ሌኒንዝም ፣ ማዖይዝም ወይንም በሌላ መጠሪያቸው ሶሻል ዴሞክራሲ ፣ ማሕበራዊ ፍትሕ ፣ ወዘተ ፤ አስፈላጊ ሆነው ሲያገኙት በግለሰቡ ሰብዓዊነት ላይ ምንም የእማያወላዳ ፍፁም ስልጣን አለን ብለው የእሚሉ በመሆናቸው እና በእዚኽም የሰውን ተፈጥሮዋዊ ነፃነት የእሚክዱ ፣ ግለሰብ ማሕበረሰብን የእሚቀላቀልበትን ዓላማ ፦ እርሱም ከተፈጥሮ ኹኔታ ለመዳን እና ኢከነሚያዊ ተጠቃሚነቱን ማሳደግ የእሚባሉትን በመፃረር ፤ አንድ ትልቅ ለእሚሉት ጉዳይ ግለሰቦች ያለ ምንም ማቅማማት ግላዊ ፍላጎታቸውን ማስገዛት አለባቸው ስለ እሚሉ ፤ የግለሰቡን የማሕበረሰብ አህድነት የእማይቀበሉ ናቸው ።
በፖለቲካዊ ፅንፈኝነት ስር እንዳየነው ፤ የፋሺስቱ መሥራች ዱቼ ሞሶሎኒ ፤ ፋሺዝምን እንደ እዚኽ ይገልፀዋል ፦
“የፋሺስቱ የህይወት ውጥን ግንዛቤ ኃይማኖታዊ ነው ፤ በእዚኽም ሰውየውን ከፍ ከአለው ሕግ ጋር በአለው ግንኙነት ነው የእሚያየው ፤ ይኽም ሕግ የሰውየውን ግላዊነት ተሻግሮ የአንድ መንፈሳዊ ማሕበር ሆንታዊ አባል እንዲሆን ለማድረግ የእሚያስችለውን ግብ የያዘ ነው ። … ፀረ ግላዊነት የሆነው የፋሺዝም የህይወት ውጥን ግንዛቤ ፤ የመንግሥትን አስፈላጊነት በማስረገጥ ፤ ግለሰቡን የእሚቀበለው የግለሰቡ ጥቅም ፤ እንደ ታሪካዊ አካል የሰውን ልጅ ሆንታዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ ፈቃድ ለማስፈፀም ከቆመው መንግሥት ጋር እስከ ተስማማ ድረስ ብቻ ነው ።”
“The fascist conception of life is a religious one, in which man is viewed in his immanent relation to a higher law, endowed with an objective will transcending the individual and raising him to conscious membership of a spiritual society...Anti-individualistic, the Fascist conception of life stresses the importance of the state and accepts the individual only in so far as his interests coincide with those of the State, which stands for the conscious and the universal, will of man as a historic entity. [31]“
የሞሶሊኒ የፋሺዝም ‘ማንፌስቶም’ ወረድ ብሎም ፤ ፋሺዝም ወይንም ሕጉ ለስልጣኑ ገደብ የለውም ይላል ፦
“… ወደ ነፍስ ውስጥ ገብቶ ያለተቀናቃኝ ይገዛል ።”
“... entering into the soul and ruling with undisputed sway. [31]“
እነ እዚኽ ፅንፈኛ ርዕዮቶች ፤ የሰውን ወይንም የዜጋን የሐገር አደረጃጀትት አህድነት ወይንም የሰውን ማሕበራዊ ወይንም ፖለቲካዊ ፍጡርነት በእዚኽ አግባብ መጻረራቸው ፤ ከነፃነት ዴሞክራሲ ውጭ ያሉ የፖለቲካ ስረዓቶች በሙሉ አንድ የእሚያደርጋቸው ወይንም ከነፃነት ዴሞክራሲ የእሚለያቸው ነገር ፤ ሰብዓዊ ክብርን ኹለተኛ እና ሦሥተኛ የፖለቲካ ግባቸው ማድረጋቸው ሲሆን ፤ የነፃነቱ ዴሞክራሲ ደግሞ ከሌሎች የፖለቲካ ርዕዮቶች በሙሉ የእሚለይበት ምክንያት ፤ የሰዎችን ሰብዓዊነት ማክበር እና ማስከበር የስረዓቱ ቀዳሚ ግብ እና አንኳር ክፍል በማድረጉ ነው ።
የነፃነቱ ዴሞክራሲ ዜጎችን የማሕበረሰብ አህድ አድርጎ ፤ ማሕበረሰብ በሰዎች ለሰዎች ጥቅም የእሚቋቋም በመሆኑ ፤ አንድ ማሕበረሰብ እና የተለያዩት የማሕበረሰቡ ተቋማት ፤ የማሕበረሰብ አህድ የሆኑት ሰዎች እኩል ተፈጥሮዋዊ ነጻነታቸውን ፤ በተፈጥሮዋዊ ሕግ ብቻ ሲገታ በእሚመስላቸው መንገድ ሕይወታቸውን እና ንብረታቸው ለማቆየት እና ለማሻሻል ሊጠቀሙበት ይገባል የእሚለውን መርሕ ፤ ማክበር እና እንዲ ከበር ማድረግ በእሚለው መርሕ ላይ እንዲመሠረቱ ማድረጉ ፤ ከእላይ የዘረዘርናቸውን የእሚከተሉትን ሦሥት ትላልቅ ማሕበራዊ ጥቅሞች ለዜጎች እንዲሰጥ ያስችሉታል ፦
ስለ ማሕበራዊ መረጋጋት ስንነጋገር ፤ በአንድ መሐበረሰብ ውስጥ የዘላቂ ግጭት እና አለመረጋጋት መነሻ የእሚሆኑ ጉዳዮችን ስለ መለየት እና እነ እዚኽ በማሕበረሰብ ውስጥ የዘላቂ ግጭት መነሻ የእሚሆኑ ጉዳዮች በምን አግባብ ቢያዙ የማሕበረሰብ ቀውስ ኹሉ ምንጭ የሆነው ማሕበራዊ አለመረጋጋት (Lack of peace and security) ትርጉም በአለው መልኩ ሊታቀብ ወይንም አደጋ ከመሆን መቅረት ይችላል? የእሚሉት ኹለት ጉዳዮች ላይ እየተነጋገርን ነው።
ምንም እንኳን ከአምባገነናዊ ማሕበራዊ ውልተኞቹ ፣ ከነጻነቱ ዴሞክራሲ እና ከማርክሲዝም በስተቀር ከእላይ የአየናቸው ሌሎቹ ርዕዮቶች በአንድ መሐበረሰብ ውስጥ የማሕበራዊ አለመረጋጋት ወይንም የግጭት መነሻ ምክንያቶች ምንድን ናቸው እና እነ እዚኽ የግጭት ምክንያቶች እንዴት ብእንይዛቸው ማሕበራዊ መረጋጋትን በተነጻጻሪነት ማስፈን እንችላለን በእሚለው ጉዳይ ላይ ፤ ይኽ ነው የእሚባል ትንታኔ በአይኖራቸውም ፤ ዘላቂነት የአለው ማሕበራዊ መረጋጋት ለአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ የህልውና እና የልማት ቅድመ ኹኔታ በመሆኑ ፤ እያንዳንዱ ፖለቲካዊ ርዕዮት ማሕበራዊ መረጋጋት ከማስፈን አንጻር መመዘኑ የግድ አስፈላጊ ነው።
በአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ውስጥ ማሕበራዊ መረጋጋት በዘላቂነት የአለመኖሩ ችግር ፤ በአንድ ማሕበረሰብ ላይ የእሚያሳድረውን አስከፊ ተጽኖ ፤ በጥሩ እና ተጠቃሽ ቋንቋ ከገለጹት ሰዎች አንዱ ቶማስ ሆብስ እንደ እዚኽ አስቀምጦታል ፦
“... በእዚኽ ኹኔታ ውስጥ ፤ ሰው ትርፍ በእሚያስገኝ ማንኛውም ሥራ ላይ አይሰማራም ምክንያቱም ትርፉን ለመጠቀም ዋስትና ስለ እማይኖረው ። በእዚኽም ምክንያት ፣ በምድር ላይ ምንም የባህል መዳበር አይኖርም ፣ በንግድ ከውጭ ተገዝቶ የእሚገባ ዕቃ አይኖርም ፣ ጥሩ ህንጻ አይገነባም ፣ ትላልቅ ነገሮችን ከስፍራ ስፍራ የእሚያንቀሳቅሱ ማሽኖች አይኖሩም ፣ በምድር ኹሉ ላይ እወቀት አይበዛም ፣ ግዜ ትሩጉም የለሽ ይሆናል ፣ ኪነጥበብ አያድግም ፣ ትምህርት አይበዛም ፣ ማሕበረሰብ አይሰነብትም ፤ ከእዚኽ ኹሉ የከፋው ደግሞ ፤ ማብቂያ የሌለው ስጋት ፣ በአሰቃቂ ኹኔታ የመገደል አደጋ ማንዣበብ ፣ እና የሰው ህይወት ፤ ብቸኛ ፣ ነዳያን ፣ አስቀያሚ ፣ አውሬመሰል እና አጭር ትሆናለች ።”
“In such condition there is no place for industry, because the fruit thereof is uncertain: and consequently no culture of the earth; no navigation, nor use of the commodities that may be imported by sea; no commodious building; no instruments of moving and removing such things as require much force; no knowledge of the face of the earth; no account of time; no arts; no letters; no society; and which is worst of all, continual fear, and danger of violent death; and the life of man, solitary, poor, nasty, brutish, and short [26]“
ይኽን መሰሉ የአንድ ማሕበረሰብ አባላት በስጋት በመወጠር ተረጋግተው እለታዊ ኑሮዋቸውን መኖር ከአለመቻላቸው የተነሳ ሕይወት ፦ ብቸኛ ፣ ነዳያን፣ አስቀያሚ ፣ አውሬመሰል እና አጭር የእምትሆንበትን ኹኔታ የእሚያስከትለው ማሕበራዊ አለመረጋጋት ፤ ለምን እንደ እሚከሰት ከእላይ ያየናቸው ርዕዮትን ገሚሶቹ የራሳቸው ትንታኔ እና መፍትኼ ሲሰነዝሩ ከፊሎቹ ደግሞ ስለ ጉዳዩ ይኽ ነው የእሚባል ትንታኔ በአይኖራቸውም በእሚከተሉት የተሳሳተ ፖሊሲ ምክንያት የችግሩ አባባሽ ይሆናሉ ።
እንደ አምባገነናዊ ማሕበራዊ ውልተኞቹ[3] ፤ በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ ማሕበራዊ አለመረጋጋት እና ግጭት በዘላቂነት የእሚከሰተው ፤ በኹሉም ዘንድ እኩል የእሚፈራ እና ፍጽማዊ የሆነ ሕግ አስከባሪ መንግሥት በአለመኖሩ ነው፦
“ሰዎች በጋራ የእሚያስተዳድራቸው እና የእሚፈሩት ኃይል (መንግሥት) በሌለበት ወቅት ፤ የእሚገኙበት ኹኔታ የጦርነት ኹኔታ መሆኑ ግልጽ ነው ፤ ይኽ ዓይነቱ ጦርነት ደግሞ እያንዳንዱ ሰው በእያንዳንዱ ላይ የእሚነሳበት ዓይነት ጦርነት ነው።”
“Hereby it is manifest, that during the time men live without a common Power to keep them all in awe, they are in that condition, which is called warre, and such a warre, as is of everyman, against everyman. [26]”
ስለ እዚኽ ማሕበረሰብ ከዘላቂ አለመረጋጋት እንዲወጣ ከአስፈለገ ፤ ኹሉም ፈርተው የእሚገዙለት አምባገነናዊ መንግሥት ያስፈልጋል ፤ እንደ አምባገነናዊ ማሕበራዊ ውልተኞቹ።
ለማርክሲስቶች የማሕበራዊ አለመረጋጋት ምንጭ በማሕበረሰብ ውስጥ የእሚገኝ የኢከነሚያዊ ደረጃ ልዩነት ነው ፦
“ከእዚኽ በፊት የነበሩ ማሕበረሰባት ታሪክ ኹሉ የመደብ ትግል ታሪክ ነው ። ነፃ እና ባሪያ ፣ ባላባት እና ጭሰኛ ፣ ጌታ እና ሎሌ ፣ አለቃ እና ምንዝር ፤ በአጭሩ ጨቋኝ እና ተጨቋኝ ፤ ማብቂያ በሌለው ተፃራሪነት ተፋጠው ፤ አንዳንዴ በግልፅ አንዳንዴ በስውር እየተጋጩ ፤ ግጭቱ አብዮታዊ የሆነ ማሕበራዊ አዲስ አወቃቀር የፈጠረበት ወይንም ተቃራኒ መደቦቹ በፍፁም የተጠፋፉበት ነው ።”
“The history of all hitherto existing society is the history of class struggles. Freeman and slave, patrician and plebeian, lord and serf, guild-master and journeyman, in a word, oppressor and oppressed, stood in constant opposition to one another, carried on an uninterrupted, now hidden, now open fight, a fight that each time ended, either in a revolutionary reconstitution of society at large, or in the common ruin of the contending classes. [18] “
ይኽም በመሆኑ ፤ እንደ ማርክሲስቶች በማሕበረሰብ ውስጥ የኢከነሚ ደረጃን መሠረት የአደረገ መደብ እስከ አለ ፤ በማሕበረሰብ ውስጥ ዘላቂ ግጭት ወይንም ማሕበራዊ አለመረጋጋት የእማይቀር በመሆኑ ፤ ማሕበረሰብ ወደ ዘላቂ መረጋጋት እንዲገባ ፤ ሰፊው እና ድኃው የማሕበረሰብ ክፍል ፤ ሶሻሊስታዊ አብዮት አድርጎ የኢከነሚያዊ ልዩነት ኹሉ ምንጭ የሆነውን የግል ንብረት ባለቤትነት መብትን በመሻር ፤ ሰዎች ኹሉ የእኔ የእሚሉት ኃይማኖት ፣ ሐገር ፣ ንብረት ፣ ቤተሰብ ፣ ወዘተ ፤ ሳይኖራቸው ፤ ኹሉንም ነገር በጋራ ባለቤትነት ይዘው የእሚኖሩበት ማሕበራዊ ስረዓት መፈጠር አለበት።
የነጻነቱ ዴሞክራሲ ከአምባገነናዊ ማሕበራዊ ውልተኞቹ እና ከማርክሲስቶቹ በተለየ ፤ ማሕበራዊ ውልተኞቹ እንደ እሚሉት ሕግ አስከባሪ መንግሥት የመኖሩን አስፈላጊነት ቢቀበለም ፤ በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ የዘላቂ ግጭት እና አለመረጋጋት ምንጭ ፤ የእሚፈራ ሕግ አስከባሪ መንግሥት አለመኖር ወይንም በዜጎች መካከል የአለ የኢከነሚ ደረጃ ልዩነት መኖሩ ሰአይሆን ፤ መንግሥትን ጨምሮ በሌላው በማንኛውም አካል እና በማንኛውም ምክንያት የዜጎች ተፈጥሮዋዊ በሕይወት የመኖር እና ንብረት የማፍራት መብት ያለ ተፈጥሮ ሕግ አግባብ አደጋ ውስጥ ሲገባ ነው ፤ በአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ውስጥ ዘላቂ የሆነ ግጭት እና ማሕበራዊ አለመረጋጋት የእሚፈጠረው።
ስለ እዚኽ ፤ እንደ ነጻነቱ ዴሞክራሲ ፤ በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ ማሕበራዊ መረጋጋት እንዲሰፍን ፤ የዜጎች ተፈጥሮዋዊ ነጻነት እና ንብረት የማፍራት መብት ፤ ከተፈጥሮ ሕጉ አግባብ ውጭ ፤ በመንግሥትም ቢሆንም መሻር የለበትም።
በአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ውስጥ የማሕበራዊ አለመረጋጋት ወይንም የጦርነት ኹኔታ ምንጭ ፤ በግለሰብ ይኹን በቡድን ምክንያት ፤ የማሕበረሰቡ አህድ የሆኑ ግለሰቦች የተፈጥሮዋዊ እኩል ነፃነታቸው ግብ የሆነውን ፤ በህይወት የመቆየት እና ህይወትን ማሻሻል ግብ በአንድም በሌላም ምክንያት አደጋ ውስጥ እንደ አይገባ መከላከል ሳይችል ሲቀር ፤ ማሕበራዊ አለመረጋጋት ወይንም የጦርነት ኹኔታ ይከሰታል ፤ እንደ ነጻነቱ ዴሞክራሲ ።
ሰዎች ኹሉ በተፈጥሮ እኩል ነጻ በመሆናቸው ፤ ይኽ ተፈጥሮዋዊ እኩል ነጻነታቸው በተፈጥሮ ሕግ ብቻ ሲገደቡ ፤ በእሚመስላቸው መንገድ እውቀታቸውን እና ጉልበታቸውን አውለው ሕይወታችውን ለማቆየት እና ኑሯቸውን ለማሻሻል የመንቀሳቀስ መብት ስለ አጎናጸፋቸው ፤ መንግሥት ይኹን አንዳች ዓይነት ባሕላዊ ፣ ኃይማኖታዊ ወይንም ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ፤ ከእዚኽ ተፈጥሮዋዊ ፍላጎታቸው እና መብታቸው ከአገዳቸው ፤ ሰዎች በአንድም በሌላም መንገድ ሕይወታቸውን እና ንብረታቸውን ለመታደግ መነሳታቸው ስለ እማይቀር ፤ ከተፈጥሮ ሕግ አግባብ ውጭ የሆነ ፤ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ ነጻነት የእሚገድብ ማንኛውም ኃይል የተፈጥሮ ኹኔታ ወይንም የሰዎች ህይወት ፦ ብቸኛ ፣ ነዳያን ፣ አስቀያሚ ፣ አውሬመሰል እና አጭር የሆነችበትን ማሕበራዊ አለመረጋጋት ይጋብዛል።
ሰዎች ወይንም ዜጎች በተፈጥሮ ስለ እሚገኙበት የተፈጠሮ እኩል ነጻነት ጆን ሎክ እንደ እዚኽ እንደ አለ እናስታውሳለን ፦
“ . . . በተፈጥሮ ሰዎች ኹሉ ፤ የእሚመስላቸውን ለማድረግ ፣ ራሳቸውን ወይንም ንብረታቸውን በወደዱት አግባብ ለመምራት ፤ በተፈጥሮ ሕግ ብቻ ተገደብው የማንንም ፈቃድ ሳይጠይቁ እና በማንም ላይ ሳይደገፉ ለመኖር ፍፁም ነፃነት አላቸው ።”
« ... all men are naturally in, and that is, a state of perfect freedom to order their actions, and dispose of their possessions and persons as they THEY THINK FIT, within the bounds of the law of Nature, without asking leave or depending upon the will of any other man. [71]»
ሰዎች ግን ፤ ይኽን ተፈጥሮ ለኹሉም ያጎናፀፈችውን ፤ እኩልነት እና ነፃነት ፤ በኃይማኖት ፣ በፋሺስታዊ የፖለቲካ ርዕዮት ወይንም በሌላ በማንኛውም ምክንያት ፤ ከተፈጥሮ ሕጉ አግባብ ውጭ ከተነፈጉ ወይንም ሲነፈጉ ፤ ሰብዓዊ እኩልነቱ እና ነፃነቱ የተገፈፈበት ሰው ተፈጥሮዋዊ መብቱን ከጥቃት መከላከል ይጀምራል ፤ ይኽም ጦርነትን ያስከትላል።
ምንም እንኳን ሰዎች ወደ ጦርነት በተለያየ ምክንያት እና አንዳንዴም በአልባሌ ምክንያት የእሚገቡ ቢሆንም ፤ ህይወታቸውን እና ለህይወት የእሚያስፈልጋቸውን ነገር ከጥቃት ለመከላከል የእሚገቡበት ጦርነት ፤ ተገደው እና በትክክለኛ ምክንያት የእሚገቡበት ጦርነት ነው የእሚሆነው። ስለ እዚኽ ፦ የትኛውም ኃይል በአንድ ማሕበረሰብ ውስጥ የእሚገኙ ዜጎችን ፤ በአንድም በሌላ ምክንያት በሕይወት እና በንብረታቸው ላይ የዋስትና አደጋ ሲደቅን ፤ ሰዎቹን ተፈጥሮዋዊ እና ፍትሐዊ ወደ ሆነው ራስን ወደ መከላከል ኹኔታ ውስጥ እያስገባቸው ነው።
ይኽን ዜጎች ፤ ተገደው ራስን እና ንብረትን ከጥቃት ለመከል የእሚገቡበትን ኹኔታ ፤ ጆን ሎክ እንደ እዚኽ ያስቀምጠዋል፦
“የተፈጥሮን ሕግ የእሚተላለፍ ማንም ሰው ፤ እኔ የእምመራው በምክንያት እና በፍትሕ ሰአይሆን በሌላ ሕግ ነው ብሎ በግልፅ እያወጀ ነው ። … ይኽ ደግሞ ለሰው ዘር በሙሉ አደገኛ ያደርገዋል … ይኽ በእሚሆንበት ግዜ ፤ የሰው ልጅ በሙሉ በአለው ራስን የማዳን መሠረታዊ መብት ፤ ይኽንን ሰው ማሳደብ ሲያስፈልግም አደጋ የእሚደቅነውን ኃይል ማጥፋት ይችላሉ ፤ በእዚኽ ይኽን ሕግ የእሚተላለፈው ሰው ይኽን ክፋት በራሱ ላይ ያመጣል ።”
“In transgressing the law of nature, the offender declares himself to live by another rule than that of REASON and EQUITY,…, and so he becomes dangerous to mankind … every man upon this score, by the right he has to preserve mankind in general, may restrain, or where it is necessary, destroy things noxious to them, and SO MAY BRING SUCH EVIL ON ANYONE WHO HAS TRANSGRESSED THE LAW [71]“
ስለ እዚኽ ፦ እንደ ነጻነቱ ዴሞክራሲ ፤ የማሕበራዊ አለመረጋጋት ምንጩ ፤ በማሕበረሰብ ውስጥ ያሉ ማንቸውም ዓይነት ቡድናዊ ወይንም መደባዊ ልዩነቶች ወይንም ቆፍጣና መንግሥት የአለመኖሩ ጉዳይ ሰአይሆን ፤ ሰዎች በሰውነታቸው በተፈጥሮ የአላቸው በሕይወት የመኖር እና ንብረት የማፍራት መብታቸው ፤ በግለሰቦች ፣ በተቋማት ፣ በመንግሥት ወይንም በሌላ በማንኛውም አካል በቋሚነት አደጋ ውስጥ የመግባቱ ጉዳይ ነው።
ማርክሲዝም የመደብ ልዩነትን ማጥፋት በእሚል ፤ የመደብ በአላንጣዎች መጥፋት አለባቸው ሲል እና ይኽንም ተከትሎ ሰዎች የእኔ የእሚሉት እና በተናጠል ሕይወታቸውን ልክ ነው በእሚሉበት አግባብ መምራት የለባቸውም ፤ ይልቅ ከንብረታቸው አንስቶ ኹሉ ነገራቸው በመዓከላዊነት መመራት አለበት ብሎ ሲል ፤ ቀጥታ ኼዶ ከሰዎች ተፈጥሮዋዊ ነጻነት ከአጎናጸፋቸው በሕይወት የመኖር እና ሕይወትን የማሽሻል መብት ጋር እየተጋጨ ስለሆነ ፤ እንደ ነጻነቱ ዴሞክራሲ ፦ ማርክሲዝም በፍልስፍና ደረጃ ዘላቂ የሆነ የጦርነት ኹኔታ ወይንም የማሕበራዊ አለመረጋጋት ምንጭ ነው።
ማርክሲዝምም ብቻ ሰአይሆን ፤ ከነጻነት ዴሞክራሲ ውጭ የአሉት ሌሎቹ ርዕዮቶች በሙሉ ፤ የእየ ራሳቸው የተለያየ ምክንያት ቢኖራቸውም ፤ ፍልስፍናቸው ከእዚኽ ከዜጎች ተፈጥራዊ እኩል ነጻነታቸው ከአጎናጸፋቸው ፤ የማንንም መሰል ፍጥረታዊ ሰው ፈቃድ ሰአይጠይቁ ፤ ሕይወታቸውን ለማቆየት እና ለማሻሻል ፤ በተፈጥሮ ሕጉ ብቻ ሲገደቡ የአሻቸውን የማድረግ መብት ጋር ስለ እሚጋጭ ፤ ርዕዮቶቹ በስሪት ደረጃ የጦርነት ኹኔታ ወይንም የማሕበራዊ አለመረጋጋት ምንጭ ናቸው።
ከእላይ እንደ አልነው ፤ ኃይማኖታዊውን ርዕዮት ብንወስደው ፤ የዓምላክ እንደ አይቆጣ ማድረግ ወይንም ሰዎች መጪውን ዓለም እንዲወርሱ ማድረግ ቀዳሚው ጉዳዩ በመሆኑ ፤ እንደ እምነቱ አስተምህሮ ሰዎች ዓምላክን የእሚያስቆጣውን ነገር እንደ አያደርጉ ለማድረግ ወይንም ሰዎች ከመጻኢው ዓለም እንደ አይጎድሉ ለማድረግ ፤ ማንኛውንም ዓይነት የዜጎችን የተፈጥሮ ነጻነት ከተፈጥሮ ሕግ አግባብ ውጭ ለመጣስ ዝግጁ በመሆኑ ፤ የዜጎችን ሕይወት እና ንብረት አደጋ ውስጥ የእሚከት ስረዓት መሆኑ የእማይቀር ነው።
ለምሳሌ ፦ ሴት ልጅ ከወንድ ልጅ እኩል አይደለችም ወይንም ሴት ልጅ በወንድ ልጅ ቁጥጥር ስር መሆን አለባት ብሎ የእሚያስተምር ኃይማኖት ፤ አንዲት ሴት ሰብዓዊ ፍጥረት በመሆኗ በተፈጥሮ የተጎናጸፈችውን ፤ ሕይወቷን ለማቆየት እና ለማሻሻል በተፈጥሮ ሕግ ብቻ ተገድባ ፤ የአሻትን የማድረግ መብቷን እየገፈፈ ስለሆነ ፤ እንደ እዚኽ የአለው ኃይማኖታዊ ስረዓት ፤ ማሕበረሰቡን በማሕበራዊ አለመረጋጋት ውስጥ የዘፈቀ ነው የእሚሆነው። ሴቷም በአብዛኛው እንደ ወንዱ ብረት አንስታ ጫካ ልትገባ በአትችልም ፤ ሴት የላከው ሞት አይፈራምን ልትጠቀም ትችላለች ።
በተመሳሳይም ብሔራዊ ጽንፈኛው ፤ በሰዎች ባሕሪ ምክንያት የሕዝብ እና የባሕል መቀየጥ እና ከቦታ ቦታ ተንቀሳቃሽነት ሊቀሩ የእማይችሉ በመሆናቸው ፤ ጽንፈኛ ሆኖ በአንድ ፖለቲካዊ ማሕበረሰብ ውስጥ ፤ የእኔ ዓይነቱ የሕዝብ ንዑስ ቁጥራችን ብዙ ነው እና የበለጠ ፖለቲካዊ ውክልና ይሰጠን ፣ አናሳ ነንና እና እንደ ሕዝብ ንዑሳን እኩልነታችን እንዲከበር ከቁጥራችን በላይ እኩል የእሚያደርግ ውክልና ይሰጠን ወይንም ይኽ እና ይኽ አከባቢ የእዚኽ እና የእዚያኽ ሕዝብ ንዑሳን አባላት ብቻ መኖሪያ ነው በእሚል ሲንቀሳቀስ ፤ ሰዎች በሕዝባዊ ንዑስ ማንነታቸው ሳይወሰኑ ሰው በመሆናቸው ብቻ የእሚጋሩዋቸውን ተፈጥሮዋዊ የነጻነት መብቶች እየተጋፋ በመሆኑ ፤ እንደ ሌሎቹ ከነጻነቱ ዴሞክራሲ ውጭ እንደ አሉት ስረዓቶች ፤ መሐበራዊ አለመረጋጋትን እየጋበዘ ነው።
ከነጻነቱ ዴሞክራሲ ከማሕበራዊ አለመረጋጋት ምንጭ ትንታኔ አንጻር ሌላው በጥንቃቄ መታየት የአለበት ፤ የአምባገነን ማሕበራዊ ውልተኞች ፤ የጦርነት ኹኔታ ወይንም የማሕበራዊ አለመረጋጋት ምንጭ ፤ ዜጎችን በጋራ የእሚያስተዳድር እና ኹሉም ዜጎች የእሚፈሩት ቆፍጣና መንገሥት አለመኖሩ ነው የእሚለው ነው።
ምክንያቱም ፦ የነጻነቱ ዴሞክራሲ ከጦርነት ኹኔታ ወይንም ከዘላቂ ማሕበራዊ አለመረጋጋት ለመውጣት ፤ የተፈጥሮ ሕግ ነጸብራቅ የሆነውን ማሕበራዊ ውል አክብሮ የእሚያስከብር መንግሥት አስፈላጊ መሆኑን ቢያስቀምጥም ፤ ቆፍጣና ሕግ አስከባሪ መንግሥት መኖሩ በራሱ የጦርነትን ኹኔታ ያስቀራል ብሎ አይልም ። መንግሥት የእሚሆኑት ራሳቸው ሰዎች በመሆናቸው መንግሥት ራሱ በተፈጥሮ ሕጉ ከአልተገዛ ፤ የመንግሥት ባለ ስልጣናት ስልጣናቸውን ለራሳቸው በአደላ እና የሌሎችን ዜጎች ሕይወት እና ንብረት አደጋ ውስጥ በእሚያስገባ መልኩ ሊጠቀሙበት የእሚችሉ በመሆኑ ፤ ማሕበራዊ ውሉን የእሚያስፈጽም መንግሥት አስፈላጊ ቢሆንም ፤ መንግሥት ራሱ ለማሕበራዊ ውሉ ተገዢ ከአልሆነ የተፈጥሮ ኹኔታ ወይንም የማሕበራዊ አለመረጋጋት ምንጭ ሊሆን ይችላል ፤ እንደ ነጻነቱ ዴሞክራሲ።
የነጻነቱ ዴሞክራሲ ፤ መንግሥት የእሚያስፈልግበትን ምክንያት እንደ እዚኽ ያስቀምጠዋል ፦
“ … የተፈጥሮ ኹኔታ የሰዎችን ህይወት ቀጣይነት አደጋ ውስጥ የእሚጥል መሆኑ ፤ እያንዳንዱ ሰው በእዚኽ ኹኔታ ውስጥ እየኖረ ፤ በእዚኽ ኹኔታ ውስጥ ራሱን ከአደጋ መከላከል ከእሚችልበት ደረጃ አልፏል ። ስለ እዚኽ ይኽ ጥንታዊ ኹኔታ በአለበት መቀጠል አይችልም ፤ የሰው ዘርም በእዚኽ መልክ የመኖር መንገዱን ከአልቀየረ ይጠፋል … ስለ እዚኽ ፦ ብቸኛው መንገድ ኃይላቸውን አስትባብረው ሲገኙ ብቻ ይሆናል የህልውናቸውን እንቅፋት ማስወገድ የእሚችሉት ። ይኽም ደግሞ ሊሳካ የእሚችለው የተሰባሰበው ኃይል እንደ አንድ ሆኖ መተግበር ሲችል ነው ። ኃይሉ በእዚኽ መልኩ እንዲተባበር ደግሞ ብዙ ሰዎች አብረው መሥራት አለባቸው ። ነገር ግን ፤ እያንዳንዱ ሰው ለመኖር በዋናነት የእሚያስፈልገው ደግሞ ፤ ነፃነቱ እና ብርታቱ ናቸው ፤ ታዲያ ይኽ ሰው ነፃነቱን እና ኃይሉን የግል ጥቅሙን በእማይጎዳ እና ለእራሱ ሊያደርግ የእሚገባውን ጥንቃቄ ሳይአስቀር እንዴት አድርጎ ይኽንን የሕብረት አንድ ኃይል ይፈጥራል ? ይኽ ፈታኝ ኹኔታ ፤ አኹን በእማነሳው ርዕስ ላይ ፤ በእዚኽ መልኩ ሊቀመጥ ይችላል ፡
የኹሉንም ኃይል አስተባብሮ ፤ የእያንዳንዱን የማሕበር አባል ሰውነት እና ንብረት ከአደጋ የእሚከላከል ማሕበር መመሥረት ፤ ይኽንም ደግሞ እያንዳንዱ ራሱን ከሌሎቹ ከኹሉም ጋር ሲያስተባብር ፤ ነገር ግን የራሱ አለቃ ራሱ ብቻ የእሚሆንበት እና እንደ በፊቱ ነፃ የእሚሆንበት አግባብ ነው ።”
“…that men have reached the point at which the obstacles to their survival (in their naturally free and independent state) in the state of nature overpower each individual’s resources for maintaining himself in that state. So this primitive condition can’t go on; the human race will perish unless it changes its manner of existence… So their only way to preserve themselves is to unite a number of forces so that they are jointly powerful enough to deal with the obstacles. They have to bring these forces into play in such a way that they act together in a single thrust. For forces to add up in this way, many people have to work together. But each man’s force and liberty are what he chiefly needs for his own survival; so how can he put them into this collective effort without harming his own interests and neglecting the care he owes to himself? This difficulty, in the version of it that arises for my present subject, can be put like this:
Find a form of association that will bring the whole common force to bear on defending and protecting each associate’s person and goods, doing this in such a way that each of them, while uniting himself with all, still obeys only himself and remain as free as before. [47]“
ማሕበራዊ ውል በእሚለው መጽሐፉ ላይ ያስቀመጠው ፤ ከላይ የአለው የሩሶ ኃሳብ እንደ እሚያመለክትን ፤ ትክክለኛው የመንግሥት አመክንዮ ወይንም የነፃነት ዴሞክራሲ ስነ መንግሥት ፤ ለመመለስ የእሚጥረው አንኳር ጥያቄ ወይንም ሊፈታ የእሚፈልገው እንዴታ ወይንም እንቆቅልሽ ፦
‘ሰዎች እንደ ማሕበረሰብ በምን መልኩ ቢዋቀሩ ነው ፤ ተፈጥሮዋዊ ነፃነታቸውን ሳያጡ ነገር ግን ከጋራ ትብብራቸው የእሚመጣው ኃይላቸው ወይንም አቅማቸው ተጠቅመው ህይወታቸውን እና ንብረታቸውን ከአደጋ መከላከል የእሚችሉት ?’
የእሚለውን እንቆቅልሽ የእሚፈታ ፤ ይኽን አማካይ አደረጃጀት ማግኘት ነው ፤ የዲሞክራሲያው መንግሥት አወቃቀር መሠረት ።
ይኽንም ሚዛን የእሚመታው ወይንም የሰዎችን ተፈጥሮዋዊ ነፃነታቸውን አክብሮ የህይወት እና የንብረት ዋስትና የእሚሰጣቸው ወይንም የእነርሱ ነፃነት የሌላውን ሰው ነፃነት መጉጃ እንደ አይሆን እንዲሁም የሌላው ሰው ነፃነት የእነርሱን ነፃነት መጉጃ እንደ አይሆን የእሚያድርገውን እና እንደ ነጻነቱ ዴሞክራሲ መንግሥትም ሆነ ዜጎች ሊገዙበት የእሚገባው ሕግም ሰዎች በማመዛዘን የእሚደርሱበት ነው ፦
“ የተፈጥሮ ኹኔታ የእሚገዛው የተፈጥሮ ሕግ አለው ፤ አዕምሮዋዊ ማመዛዘን ፥ ማለትም ሕጉ ፤ ሊሰማው ፈቃደኛ የሆነውን ማንኛውንም ሰው ፤ ኹሉ ሰው ነፃ እና እኩል በመሆኑ ፥ አንዱ ሰው የሌላውን ሰው ህይወት ፣ ጤንነት ፣ ነፃነት እና ንብረት የእሚጎዳ ነገር ማድረግ እንደ ሌለበት ያስተምረዋል ።”
“The state of nature has a law of Nature to govern it, which obliges everyone, and reason, which is the law, teaches all men who will but consult it, that being all equal and independent, no one ought to harm another in his life, health and liberty or possessions; … [71]“
ይኽ ከማመዛዘን የእሚገኝ የተፈጥሮ ሕግ ዋናው ዓላማው ፤ የሰዎች ኹሉ ቋሚ ግብ ወይንም ፍላጎት የሆነውን ፤ በሕይወት የመቆየት እና ሕይወትን የማሻሻል ግብን ማክበር እና ማስከበር ነው ።
ይኽም በመኾኑ የመንግሥት ወይንም የመንግሥት ስልጣን የእሚይዙ ሰዎች ፦
“ የስልጣናቸው የመጨረሻ ገደቡ ለማሕበረሰቡ መልካም በማድረግ የተወሰነ ነው ። ኃይላቸው ደህንነትን ከማስጠበቅ ያለፈ ምንም ግብ የለውም ፤ ስለ እዚኽ ፦ ዜጎችን የማጥፋት ፣ ባሪያ የማድረግ ወይንም የማደህየት እቅድ ሊኖረው አይችልም ፤ ማሕበረሰብ ውስጥ ሲሆን የተፈጥሮ ሕግ መሥራት ያቆማል ማለት አይደለም ፤ ይልቁንም ከተፈጥሮ ሕግ ጋር የተቀራረበ እና በሰው ሕግ ተደንግጎ አጥፊው የእሚቀጣበት አግባብ የተደነገገበት ነው ። የተፈጥሮ ሕግ ለሰው ልጆች ኹሉ ፤ ለሕግ አውጭዎችም ጭምር ፤ የዘላለም ሕግ ሆኖ አለ ። ሕግ አውጭዎቹ ፤ ለሌሎች ሰዎች የእሚያወጡዋቸው ሕግጋት ፤ የራሳቸውንም ሆነ የሌሎች ሰዎችን ሕግጋት በእሚዳኝበት ግዜ ፤ ከተፈጥሮ ሕግ ጋር የእማይቃረን ሊሆን ይገባዋል ።”
“Their power in the ut-most bounds of it is limited to the public good of the society. It is a power that hath no other end but preservation, and therefore can never have a right to destroy, enslave, or designedly to impoverish the sub-jects; the obligations of the law of Nature cease not in society, but only in many cases are drawn closer, and have, by human laws, known pen-alties annexed to them to enforce their observation. Thus the law of Nature stands as an eternal rule to all men, legislators as well as others. The rules that they make for, other men’s actions must, as well as their own and other men’s actions, be conformable to the law of Nature. [71]“
ስለ እዚኽ በነጻነቱ ዴሞክራሲ ትንታኔ መሠረት ፤ መንግሥት ራሱ በተፈጥሮ ሕጉ የእማይገዛ ከሆነ ወይንም እንደ ማንኛውም ዜጋ ከተፈጥሮ ሕግ አግባብ ውጭ የሌሎችን ዜጎች ተፈጠራዊ ነጻነት በእሚጻረሩ መልኩ በሕግ ማስከበር ስም ፤ በዜጎች ሕይወት እና ንብረት ላይ አደጋ ከጋረጠ ፤ የጦርነት ኹኔታ ወይንም የማሕበራዊ አለመረጋጋት ምንጭ ይሆናል።
ይኽም በመሆኑ ፤ ማንኛውም ሕግ አስከባሪ መንግሥት የመኖሩ ጉዳይ ሰአይሆን አንድ ማሕበረሰብን ከተፈጥሮ ኹኔታ ወይንም ከማሕበራዊ አለመረጋጋት የእሚያወጣው ፤ በተፈጥሮ ሕግ የእሚገዛ ሕግ አስከባሪ መንግሥት ነው።
ስለ እዚኽ ፦ መንግሥት አልባነት ፣ በተፈጥሮ ሕግ የእማይገዛ መንግሥት ወይንም ፖለቲካዊ ኃይል ፣ የብሔር ፣ የባሕል ፣ የኃይማኖት ወይንም ሌሎች ፖለቲካዊ ጽንፈኝነቶች ፤ ዜጎች በተፈጥሮ የተጎናጸፉዋቸውን ነጻነት ፤ ሕይወታቸውን ለማቆየት እና ለማሻሻል ፤ በተፈጥሮ ሕግ ብቻ ተገድበው ፤ በአሻቸው መልኩ እንደ አይጠቀሙበት ሲከለክላቸው ፤ ከእላይ የጠቀስነው የተፈጥሮ ኹኔታ ወይንም ማሕበራዊ አለመረጋጋት ይከተላል ፤ እንደ ነጻነቱ ዴሞክራሲ ፦
“... በእዚኽ ኹኔታ ውስጥ ፤ ሰው ትርፍ በእሚያስገኝ ማንኛውም ሥራ ላይ አይሰማራም ምክንያቱም ትርፉን ለመጠቀም ዋስትና ስለ እማይኖረው ። በእዚኽም ምክንያት ፣ በምድር ላይ ምንም የባህል መዳበር አይኖርም ፣ በንግድ ከውጭ ተገዝቶ የእሚገባ ዕቃ አይኖርም ፣ ጥሩ ህንጻ አይገነባም ፣ ትላልቅ ነገሮችን ከስፍራ ስፍራ የእሚያንቀሳቅሱ ማሽኖች አይኖሩም ፣ በምድር ኹሉ ላይ እወቀት አይበዛም ፣ ግዜ ትሩጉም የለሽ ይሆናል ፣ ኪነጥበብ አያድግም ፣ ትምህርት አይበዛም ፣ ማሕበረሰብ አይሰነብትም ፤ ከእዚኽ ኹሉ የከፋው ደግሞ ፤ ማብቂያ የሌለው ስጋት ፣ በአሰቃቂ ኹኔታ የመገደል አደጋ ማንዣበብ ፣ እና የሰው ህይወት ፤ ብቸኛ ፣ ነዳያን ፣ አስቀያሚ ፣ አውሬመሰል እና አጭር ትሆናለች ።”
“In such condition there is no place for industry, because the fruit thereof is uncertain: and consequently no culture of the earth; no navigation, nor use of the commodities that may be imported by sea; no commodious building; no instruments of moving and removing such things as require much force; no knowledge of the face of the earth; no account of time; no arts; no letters; no society; and which is worst of all, continual fear, and danger of violent death; and the life of man, solitary, poor, nasty, brutish, and short [26]“
ምንም እንኳን ቶማስ ሆብስ የተፈጥሮ ኹኔታ የእሚለው በዋናነት ፤ ሰዎች ማሕበራዊ ውል ሳያስሩ ወይንም መንግሥት ሳያቆሙ በፊት የአለውን ህይወታቸው እና ንብረታቸው ዋስትና የሌለበትን ኹኔታ ቢሆንም ፤ ከላይ ባሉት ከጆን ሎክ በተወሰዱት ኃሳቦች እንደ አሳያነው መንግሥትም ሆነ ሌላው ማንኛውም ኃይል በአንድም በሌላ ምክንያት ፤ የዜጎች ህይወት እና ንብረት ዋስትና ስጋት በእሚሆንበት ግዜ ይኸው የጦርነት ኹኔታ ተመልሶ ይከሰታል ፤ ምክንያቱም ፦ የጦርነት ኹኔታ መነሻ መሠረታዊ ምክንያቱ ፤ መንግሥት ኖሮም ሆነ ሳይኖር ፥ በእዚኽ ወይንም በእዚያኛው ምክንያት የዜጎች ህይወት እና ንብረት ዋስትና ማጣቱ ነው ።
በእኔ እምነት ፤ እስከ አኹን ከአየናቸው ርዕዮትች በሙሉ ፤ በነጻነቱ ዴሞክራሲ የእሚቀርበው የማሕበራዊ መረጋጋት ምክንያት እና እንዴታ ፤ የተሻለው እና ለእውነታው የቀረበው ነው ከቲየሪ አንጻር ስንመዝነው።
ከእዛኽ በአሻገር ግን ፤ የነጻነቱ ዴሞክራሲ በተተገበረባቸው እና ከነጻነቱ ዴሞክራሲ ውጭ ያሉ ሌሎቹ ፖለቲካዊ ርዕዮቶች በተተገበሩባቸው ሐገራት መካከል የአለው ፤ የማሕበራዊ መረጋጋት ደረጃ ፤ የነጻነቱ ዴሞክራሲ የማሕበራዊ መረጋጋት ምንጭ እና እንዴታ ትንታኔ ፤ በተግባርም ተፈትኖ ትክክል ወይንም እጅግ የተሻለ አመርቂ ውጤት የአስመዘገበ መሆኑን ያረጋገጠ ነው።
በእርግጥ አኹን በእምንኖርበት ዘመን የተፈጥሮ ኹኔታን ወይንም ማሕበራዊ አለመረጋጋትን ፤ መኖር እና አለመኖሩን መመዘን ያለብን ፤ በግልጽ በእሚደረጉ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ብቻ ሰአይሆን ፤ ለምሳሌ ፦
በአጠቃላይ በተወለዱበት እና በአደጉበት ሐገር እነ እዚኽ እና ሌሎች መሰል ከፖለቲካዊ ስረዓቱ ጋር የተያያዙ ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች አስገድደዋቸው ፤ በተወለዱበት እና ሐገሬ በእሚሉት ቦታ ከመኖር ይልቅ ፤ በሌላ ሐገር ዝቅተኛ የእሚባለውን ኑሮ ለመኖር መርጠው ፤ በብዛት የእሚሰደዱ ከሆነ እና የአልተሰደዱትም መሰደጃው ጠፍቷቸው እንጂ እድሉን ከአገኙ እንደ መልካም አጋጣሚ እና እንደ ስኬት አይተውት በደስታ የእሚቀበሉት ከሆነ ፤ ያችኽ ሐገር የጦርነት ኹኔታ ወይንም ማሕበራዊ አለመረጋጋት ውስጥ ነች ማለት እንችላለን።
ለምሳሌ ፦ ከምኒዝም በኃብታም እና በነዳያን መካከል የአለውን የኃብት ልዩነት የማሕበራዊ አለመረጋጋት ምንጭ ነው እና እሱን ለማጥፋት የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ ዴሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶች ሽረን ወይንም ከተፈጥሮ ሕጉ በተቃራኒ የሆነ አብዮት በቀጣይነት ማድረግ አለብን የእሚለው የፖለቲካ ፕሮግራሙ ፤ የዜጎችን ህይወት እና ንብረት ዋስትና በማሳጣት የጦርነትን ኹኔታ እንደ እሚመልሰው እና ሰዎች በእግራቸው እንደ እሚመርጡ ወይንም ህይወታቸውን ፣ እውቀታቸውን እና ንብረታቸውን ይዘው ይኽን አደጋ ከእሚፈጥርባቸው ስረዓት እንደ እሚሸሹ ስለ ተገነዘበ ፤ በከምኒስት ማንፌስቶ ላይ ፤ የከምኒስት መንግሥታት ማድረግ አለባቸው ብሎ ከዘረዘራቸው አስር ነጥቦች በአራተኛነት ያስቀመጠው ፤ ሐገር ለቀው የእሚኼዱ ወይንም የእሚሰድዱ ዜጎች ኃብት መወረስ አለበት የእሚል ነው ፦
“ሐገር ለቀው የእሚኼዱ እና የዓመፀኞች ንብረት በሙሉ መውረስ ።”
“Confiscation of the property of all emigrants and rebels. [18]“
የከምኒዝምን ስሁት የሆነ ትንታኔ ብንቀበል እና ዜጎች ያፈሩዋቸው ኃብት ሙሉ በሙሉ የራሳቸው አይደሉም ብንል እንኳን ፤ በአንድ ሐገር ውስጥ ያለ ማንኛውም ኃብት ግን የዜጎች የጋራ እኩል ኃብት መሆኑን የግድ መቀበል አለብን ። ያም ማለት ሐገር ለቀው የእሚኼዱ ሰዎች ፤ በጋራ ባለቤት ከኾኑበት ኃብት በእኩልነት ስሌት ድርሻቸው የእሚኾነውን መጠን ይዘው የመኼድ መብት ያስፈልጋቸው ነበር ።
ዘራፊው እና ባሪያ አድራጊው ከምኒዝም ግን ፤ የራሱን ባሕሪ እና የእሚያስከትለውን የጦርነት ኹኔታ በደንብ ስለ እሚገነዘብ እና ሰዎች ህይወታቸው እና ንብረታቸው አደጋ ውስጥ ሲገባ ፤ ሲችሉ ከእነ ንብረታቸው ከአልሆነ ህይወታቸውን ይዘው እንደ እሚሰደዱ ስለ ተረዳ ፤ ምክንያተኝነትን ኹሉ ጥሶ ፤ ከሐገር የእሚለቁ ሰዎች ንብረት ኹሉ መወረስ አለበት ብሏል ።
ይኽ ደግሞ በየትኛውም ውስብስብ የሆኑ ፖለቲካዊ ቃላት ያሸብርቅ እና ይሽሞንሞን ፤ ተፈጥሮዋዊ የሆነው የዜጎችን ንብረት የማፍራት እና ባለቤት መብት የእሚጥስ ፤ ግልፅ መንግሥታዊ ዘረፋ ነው!
ዘረፋ ወይንም ከተፈጥሮ ሕግ አግባብ ውጭ የኾነ የሰው ኃብት ንጥቂያ ደግሞ ፤ በግለሰብ ተፈፀመ ፣ በተደራጀ የወንጀል ቡድን ወይንም ሕዝብ አስተዳድራለሁ በእሚል መንግሥት ተፈፀመ ወይንም ለድኃው ስለ ምራራ ነው የነጠኩት መባሉ አይደለም ጉዳዩ ፤ በማንም እና ለምንም ይፈፀም ፤ የዜጎችን ኃብት ከሕግ አግባብ ውጭ እስከ ነጠቀ ድረስ ፤ ዘረፋ ነው ።
እንዲኽ የአለው የማርክስዚም ርዕዮት አግባብ በእሚመሩ ሐገራት ፤ ዜጎች ሕይወታቸው እና ንብረታቸው ዋስትና ስለ ሌለው ፣ በፖለቲካዊ መዋቅሩ ውስጥ የአለው አስቸጋሪ እና አንዳንዴም ደም አፋሳሽ የስልጣን ሽቅድድም ፣ ከእነ እዚኽም የተነሳ የእሚሰተዋሉት የተለያዩ መጠን የአላቸው አፈናዎች እና መብት ረገጣዎች ፤ በከምኒስት ርዕዮት የእሚመሩ ሐገራት ዜጎች ፤ ከእዚኽ ከተፈጥሮዋዊ መብታቸው ጋር ተጻራሪ ከሆነ ስረዓት ስር ለመውጣት በእየግዜው ከፊልም የእማይተናነስ ጀብደኝነት እያሳዩ ሲሰደዱ ነው የኖሩት።
ከላቲን አሜርካዋ ኪውባ ወደ አሜሪካ የገቡ ዜጎች ቁጥር እና የገቡበት ኹኔታ ይኽን የእሚያሳይ ነው።
በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የምሥራቅ ጀርመን ነዋሪዎች ፤ በአይናቸው አማትረው ወደ እሚያዩዋት ምዕራብ ጀርመን ለመሻገር ፤ የራሳቸውን ሕይወት እና የቤተሰባቸውን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለው ፤ ድንበር ለመሻገር የህይወት ዋጋ ጭምር ይከፍሉ ነበር።
ዛሬም የሰሜን ኮርያ ዜጎች ደቡብ ኮርያ እና ቻይና ለመግባት ፤ የሐገሩን ድንበር ለቆ የእሚወጣ በተገኘበት ይገደል የእሚለውን ሕግ ተላልፈው ፤ እዚኽ ከመኖር ከእዚኽ ለመውጣት እየሞከርኩ ልሙት ብልው ፤ እጅግ ብዙ የሕይወት እና የንብረት ዋጋ እየከፈሉ በእየ እለቱ በብዙ እንግልት ይሰደዳሉ።
ይኽም ብቻ ሰአይኾን ፤ አኹንም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ ከምኒስት ኾነው ድንበራቸውን አልፎ ወደ ጎረቤት ሐገራት ለመኼድ የእሚነሳውን ዜጋቸውን በጥይት ለመረፍረፍ ከእሚፈልጉት ሐገራት ውጭ ያሉ ፤ ነዳያን የእሚባሉት የዓለማችን ሐገራት ፤ ከምኒስት ሳይኾኑ በአንድም ኾነ በሌላ መንገድ የዜጎችን ሕይወት እና ንብረት አደጋ ላይ የእሚጥሉ በመኾናቸው ፤ ከሐገራቸው የእሚስደደው የተማረ የሰው አቅምና እና ካፒታል በተለያየ ሪፖርት ሲቀርብ የእምናየው በመሆኑ ፤ መንግሥታዊ ወይንም ፖለቲካዊ አምባገነንነት የዜጎች የህይወት እና የንብረት ዋስትና ስጋት በሆነባቸው ሐገራት ፤ ሐገራቱ ቴክኒካሊ የጦርነት ኹኔታ ውስጥ እንደ አሉ ማሳያ ነው ።
ብዙ ሰው እንደ እሚመስለው ፤ ዜጎች ድህነትን ሽሽት ወይንም ዳጎስ ያለ ደሞዝ ፍለጋ አይደለም ሐገራቸውን ጥለው የእሚኼዱት ፤ ይልቁንም ‘የሰው ህይወት ፤ ብቸኛ ፣ ነዳያን ፣ አስቀያሚ ፣ አውሬመሰል እና አጭር’ የሆነበትን የጦርነት ኹኔታ ሽሽት ነው ።
ምክንያቱም ፦ የድኽነት ብቸኛ ማሸነፊያ መንገዱ መሥራት እና የሰሩትን ኃብት በባለቤትነት የማስተዳደር መብት ማግኘት ስለ ኾነ እና እነ እዚኽ ዜጎች በእሚስደዱበትም ሐገር ፤ ቤት ተሰርቶ እና ምግብ በስሎ ሰአይሆን የእሚጠብቃቸው ፤ ሰብዓዊነታቸውን እና ቤት ሰርቶ ምግብ አብስሎ የመኖር ተፈጥሮዋዊ መብታቸውን ወይንም ነፃነታቸውን የእሚያከብርላቸው ስረዓት ፍለጋ በመኾኑ ፤ እውነተኛው ዜጎች የእሚሸሹት ነገር በነፃነት እንደ አይሰሩ እና የሥራቸውን ውጤት በግል ኃብትነት እንደ አይዙ የእሚያጋድቸውን አፋኝ ስረዓት መኾኑ ግልፅ ነው ።
በእርግጥ ጥቂት ዜጎች በአጉል ቀቢጸ ተስፋ ወይንም በሰዎች አስተላላፊዎች እና በደላሎች ተታለው ወደ ሌላ ሐገር ለመሰደድ የእሚነሱበት ኹኔታ መኖሩ ግልጽ ቢሆንም ፤ ዞሮ ዞሮ ግን ፤ በዘመናችን የእሚታየው የዘጸዓት ዓይነት ስደት መነሻው ዜጎች በሐገራቸው መንግሥታት በርዕዮታዊ ስህተት የተፈጥሮ መብታቸው መገታቱ የፈጠረውን የጦርነት ኹኔታ ወይንም ማሕበራዊ አለመረጋጋት ሽሽት ነው።
ጎረቤታችን የአሉት ኬንያዊያን እንኳን እንደ አብዛኛው የአፍሪካ ሐገር ሕዝብ የዘጸዓት ዓይነት የስደት ዘመቻ ላይ አይደሉም።
በተነጻጻሪ የሰው እና የቁስ ኃብት ስደተኛ መዳረሻ የሆኑት ሐገራት ፤ የተረጋጉ እና የስደተኞች መስሕብ መሆን የቻሉት ፤ ማርክሲዝም እርሱ ከአልጠፋ መረጋጋት የለም የእሚለው በዜጎች መካከል የአለው የኃብት መጠን ልዩነት ስሌለቸው ወይንም ማሕበራዊ ስብጥራቸው የስደተኞች መነሻ ከሆኑት ሐገራት በተለየ መልኩ የኃይማኖት ፣ የዘር ፣ የነገድ ፣ የቋንቋ ፣ ወዘተ ፤ ወጥነት ስለ አለው አይደለም ፤ ይልቁንም እነ እዚኽ ኹሉ ማሕበራዊ ልዩነቶች ፦ የኢከነሚ ደረጃ ፣ የኃይማኖት ፣ የዘር ፣ የቋንቋ ፣ ወዘተ ፤ ልዩነቶች የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብቶች እንደ አይነፍጉ የእሚያደርግ ፤ ዜጎች ተፈጥሮዋዊ ነጻነታቸውን በእነ እዚኽ ማሕበራዊ ልዩነታቸው ሳይገደቡ ፤ ሕይወታቸውን ለማቆየት እና ለማሻሻል በእሚመስላቸው መንገድ መጠቀም ይችላሉ የእሚለውን መብታቸውን አክብሮ የእሚያስከብር መንግሥት ያለባቸው ሐገራት በመሆናቸው ነው።
ስለ እዚኽ ፦ የነፃነት ዴሞክራሲ እስከ አኹን ከእሚታወቁት ርዕዮቶች በሙሉ የጦርነትን ኹኔታ በሕግ አደብ የእሚያስገዛ እና ዜጎችን የህይወት እና የንብረት ዋስትና የእሚሰጥ በመሆኑ የማሕበራዊ መረጋጋት ምንጭ የሆነ የፖለቲካ ስረዓት ነው ።
ኹለተኛው የነፃነት ዴሞክራሲ ሰዎችን በፖለቲካዊ ስረዓት አህድነት በመቀበሉ የእሚያስችለው ማሕበራዊ ፋይዳ ፤ ፅኑ እና ቀጣይነት የአለው ማሕበራዊ እድገት ማስቻሉ ነው ።
የነጻነቱ ዴሞክራሲ ፤ ይኽን ማድረግ የእሚችለው ፤ ልክ መልካም የመፈለግ ፣ የፍትሕ ግንዛቤ ፣ የቋንቋ ክህሎት የሰውን ልጅ የፖለቲካዊ ደርዝ አህድ እንደ እሚያደርጉት ፤ የሰብዓዊ ፍጥረት በሆኑት የሰው ልጆች ጋር ብቻ የእሚገኙት ዘርፈ ብዙ ኢከነሚያዊ ሞያዎች እና ፍላጎቶች የሰውን ልጅ ፤ የማሕበረ ኢከነሚው አህድ እንደ አደረጉት የእሚቀበል በመሆኑ ነው።
ይኽም ማለት ፤ አንድ ማሕበረ ኢከነሚ ፤ የሰዎች ኢከነሚያዊ አህድነት ከአልተቀበለ እና ከአላከበረ ፤ የኢከነሚ ማሽኑ በአግባቡ ሰርቶ ፤ ማሕበራዊ የኢከነሚ እድገትን እና የግለሰቦች ወይንም የዜጎችን ተጠቃሚነት በተገቢ ኹኔታ ማረጋገጥ አይችልም ማለት ነው። የዜጎች የማሕብረ ኢከነሚው አህድነት የእሚረጋገጠው ደግሞ ዜጎች ንብረት የማፍራት እና የንብረት ባለቤትነት መብታቸው ፤ ያፈሩትን ንብረት በገበያ ለመሸጥ ወይንም በውርስ ለማስተላለፍ መብት እንደ አላቸው ሲታወቅላቸው ነው።
ከነጻነት ዴሞክራሲ ውጭ የአሉ የፖለቲካ ርዕዮቶች በሙሉ ፤ ልክ የግለሰቦችን ወይንም የዜጎችን የማሕበረሰብ አህድነት በተለያየ ምክንያት እንደ እማይቀበሉት ኹሉ ፤ የዜጎችንም የማሕብረ ኢከነሚያዊ አህድነት መገለጫ የሆነውን ፤ የግል ንብረት ባለቤት የመሆን መብት ባለቤትነት እና ይኽንንም ንብረታቸውን በነጻ ገበያ በፈቃዳቸው እንደ አሻቸው እንዲለዋወጡ አይፈቅዱም።
አኹን በዓለም ላይ የእሚታወቀው ሳይንሳዊው የኢከነሚክስ መርህ እንደ እሚያስተምረን ፤ የግል ንብረት እና ነፃ የገበያ ስረዓት በሌለበት ምህዳር ውስጥ ደግሞ የኢከነሚክስ ሳይንስ መርሆዎች በሙሉ መሥራት እንደ እማይችሉ ፤ ስለ እዚኽም ፦ የኢከነሚው ማሽን በአግባቡ ሰርቶ የእሚጠበቅበትን ውጤት ሊያመጣ እንደ እማይችል ያስተምረናል።
ያም ማለት ሰዎች እኩል ነፃ ናቸው ይኽንንም እኩል ነፃነታቸውን በህይወት ለመቆየት እና ህይወታቸውን በእሚመስላቸው መንገድ ለማሻሻል ይሰራሉ በእሚል መሠረታዊ አስተሳሰብ ላይ ተመስርቶ ፤ ዜጎች በሐገራቸው ውስጥ የሌሎችን ዜጎች ተመሳሳይ የመኖር እና ኑሮን የማሻሻል ህልም እስከ አልተጋፉ ድረስ ፤ በእሚመስላቸው መንገድ ራሳቸውን ማሰማራት እና ንብረት ማፍራት እንደ እሚችሉ ተቀብሎ ፤ በወደዱት የሥራ መስክ እንዲሰማሩ ፣ በወደዱት የሥራ መስክ ተሰማርተው በእሚያቀርቡት አገልግሎት ወይንም በእሚያመርቱት ምርት የእሚያገኙትን ኃብት በግላዊ ባለቤትነት ይዘው ፤ ሲፈልጉ ሊሸጡት ወይንም ሊያወርሱት እንዲችሉ ሕጋዊ ከለላ ከአልተሰጣቸው ፤ የኢከነሚክስ መርህዎች በሙሉ ሊሰሩ አይችሉም ወይንም የአንድ ማሕበረሰብ ኢከነሚ ‘በተፈጥሮዋዊ’ ባሕሪው ሰርቶ የእሚጠበቅበትን ውጤት ሊያመጣ አይችልም።
ያለ ግል ንበረት ባለቤትነት ኢከነሚ መሥራት አይችልም ብቻ ሰአይሆን ፤ የግል ንብረትን ለመከልከል ወይንም የኃብት ጣሪያ ለማበጀት የእሚያስገድድ ምንም አሳማኝ ምክንያት የለም ።
የግል ንብረት መፈቀድ የለበትም ተብሎ በተለያዩ ርዕዮቶች የቀረበው ኃሳብ ፤ ከእዚኽ በታች በጆን ሎክ የተቀመጡትን የግል ንብረት ባለቤትነት መብትን ማክበር ተገቢ ነው ብሎ የሞገተበትን ኹኔታ በተመሳሳይ ሳይንሳዊ ተቃራኒ ሙግት መርታት አይችሉም ፦
“ምንም እንኳን ምድር እና ሌሎች ፍጥረቶች በሙሉ የኹሉም ሰው የጋራ ንብረት ቢሆኑም ፤ እያንዳንዱ ሰው ግን ‘ራሱ’ የራሱ የግል ንብረት ነው[4] ። በእዚኽም አካሉ ላይ ከእርሱ በስተቀር ሌላ ማንም ሰው መብት የለውም ። የሰውነቱ ድካም እና የእጆቹ ሥራ ፤ በአግባቡ የእርሱ ናቸው ማለት እንችላለን ። ስለ እዚኽም ፦ ምንንም ነገር በተፈጥሮ ከእሚገኝበት ኹኔታ አንስቶ ፤ ከግል ድካሙ ወይንም ሥራው ጋር ሲቀላቅለው ፤ ያንን ነገር የእኔ ነው ማለት ይችላል በእዛም የግል ንብረቱ አድርጎታል ። በተፈጥሮ በጋራ ከእሚገኝበት ኹኔታ አንስቶ ፤ በግል ድካሙ ወይንም ንብረቱ አንድ የሆነ ነገር ስለጨመረበት ፤ ሌሎች ሰዎች የነበራቸውን የጋራ ባለቤትነት አስቀርቶታል ። ቢያንስ ቢያንስ ሌሎች ሰዎችም በድካማቸው እንደ እዚኹ ሊያደርጉት የእሚችሉት በቂ እና ተመሳሳይ የጋራ ተፈጥሮዋዊ ኃብት እስከ አለ ድረስ ፤ ይኽ የእርሱ ድካም ወይንም ሥራ ምንም ጥያቄ የሌለበት የሠራተኛው ንብረት በመሆኑ ፤ ይኽንን ድካሙን ወይንም ሥራውን የጨመረበት ነገርን ከእርሱ ውጭ የአሉ ሰዎች መብት ሊኖርበት አይችልም ።
ከበሉጥ ዛፍ የወደቀ ለውዝ አንስቶ ፤ ወይንም በደን ውስጥ ቱፋሀ (አፕል) ሰብስቦ የተመገበ ሰው ፤ በእርግጥም የራሱ ንብረት አድርጎዋቸዋል ። ማንም ሰው ምግቡ የእርሱ ሊሆን አይገባም ብሎም ሊቃወም ወይንም ሊክድ አይችልም ። እኔም ከእዛኽ ይኼን እጠይቃለሁ ፤ የእርሱ መሆን መቼ ጀመሩ? በሆዱ ውስጥ ሲፈጩ? ሲበላቸው? ሲያበስላቸው? ወደ ቤት ሲያመጣቸው? ሲለቅማቸው? ከእዚኽም ፤ መጀመሪያ ሲሰበስባቸው የእርሱ ከአልሆኑ ፤ ሌላ ምንም የእርሱ ሊያደርጋቸው አይችልም ። ሥራው ወይንም ድካሙ (የመሰብሰቡ) በእነርሱ እና በጋራ በእሚገኙት መካከል ልዩነት አድርጓል ። ይኽም ፤ የኹሉም እናት ከሆነችው ተፈጥሮ ሌላ የሆነ ነገር ደምሮበታል ፤ ይኽንንም በማድረግ ፤ የእርሱ የግል ንብረት ሆነዋል ። እናም አንድ ሰው ተነስቶ በድካሙ የራሱ ያደረጋቸውን ለውዝ እና ቱፋህ የሰው ልጆች ኹሉ የጋራ ይኹንታ ስለ አላገኘህ የእኔ ነው ማለት አትችልም ሊለው ይችላል? የኹሉም የጋራ ንብረት የሆነውን ነገር አንስቶ የእኔ ነው ማለቱ እንደ ዘረፋ ሊታይበት ይገባል? እንዲኽ ዓይነቱ የሰው ኹሉ ይኹንታ አስፈላጊ ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር ኹሉን አትረፍርፎ ሰጥቶት ሳለ የሰው ልጅ በጠኔ ይሆን ነበር ። የጋርዮሽ ሆኖ የእምናየው ነገር ፤ የግል ንብረትን በእሚያስጀምረው ፥ የጋራ ከሆነው ነገር መውሰድ ፤ በእርሱ የተተውን ፤ ስለ እዚኽም በስምምነት የጋራ እንዲ ሆን የተተወውን ነው ፤ ይኽ ባይሆን የጋራ ንብረት ምንም ጥቅም የለውም ። ከእዚኽ የጋራ ከሆነው ንብረት የመውሰድ ጉዳይ ግልፅ የሆነ የኹሉም ሰው ስምምነት የእሚያስፈልግበት አይደለም ። እንዲኽ በመሆኑ ፤ የጋራችን ከነበረው ላይ ፤ ፈረሴ የጋጠው ሳር ፣ ሰራተኞቼ የከለሉት አጥር ፣ ከማንኛውም ቦታ ከመሬት ውስጥ ቆፍሬ ያወጣሁት የብረት አፈር የማንም ሰው ፈቃድ በግልፅ ሳይሰጠኝ የግል ንብረቴ ነው ። የእኔ የሆነው ድካም/ሥራዬ ፤ በጋራ ከነበሩበት ኹኔታ አውጥቶ ፤ የእኔን የግል ንብረት አያይዞባቸዋል ።
በጋርዮሽ ከእሚገኘው ነገር ወስዶ የራስ ለማድረግ ፤ የእያንዳንዱ ሰው ፈቃድ ያስፈልጋል ስንል ፤ ልጆች ወይንም ሰራተኞች ፤ አባታቸው ወይንም አሰሪያቸው ለእያንዳንዳቸው የእሚገባቸውን መጠን ሳይሰጣቸው በፊት ፤ በጋራ ከአቀረበላቸው ስጋ ላይ ቆርጠው በእየ ግላቸው መውስድ አይችሉም እያልን ነው ። ምንም እንኳን ውኃው በፏፏቴው እየተንፏፏ ቢሆንም ፤ ከፏፏቴው ላይ በመንቀል የተቀዳው ውኃ የቀጂው መሆኑን ማን ይጠራጠራል? ድካሙ/ሥራው ፤ ውኃውን ተፈጥሮ ለኹሉም ልጆቿ በእኩልነት ካኖረችበት አውጥቶ ፤ የእራሱ እንዲሆን አድርጎታል። “
“He that is nourished by the acorns he picked up under an oak, or the apples he gathered from the trees in the wood, has certainly appropriated them to himself. Nobody can deny but the nourishment is his. I ask, then, when did they begin to be his? when he digested? or when he ate? or when he boiled? or when he brought them home? or when he picked them up? And it is plain, if the first gathering made them not his, nothing else could. That labor put a distinction between them and common. That added something to them more than Nature, the common mother of all, had done, and so they became his private right. And will anyone say he had no right to those acorns or apples he thus appropriated because he had not the consent of all mankind to make them his? Was it a robbery thus to assume to himself what belonged to all in common? If such a consent as that was necessary, man had starved, notwithstanding the plenty God had given him. We see in commons, which remain so by compact, that it is the taking any part of what is common, and removing it out of the state Nature leaves it in, which begins the property, without which the common is of no use. And the taking of this or that part does not depend on the express consent of all the commoners. Thus, the grass my horse has bit, the turfs my servant has cut, and the ore I have digged in any place, where I have a right to them in common with others, become my property without the assignation or consent of anybody. The labor that was mine, removing them out of that common state they were in, hath fixed my property in them.
By making an explicit consent of every commoner necessary to anyone’s appropriating to himself any part of what is given in common. Children or servants could not cut the meat which their father or master had provided for them in common without assigning to everyone his peculiar part. Though the) water running in the fountain be every one’s, yet who can doubt but that in the pitcher is his only who drew it out? His labor hath taken it out of the hands of Nature where it was common, and belonged equally to all her children, and hath thereby appropriated it to himself. [71]“
በእዚኽ ክፍል ላይ ፤ ጆን ሎክ የግል ንብረት ባለቤትነትን መከልከል ምክንያተቢስ ነው ብቻ እያለም ሰአይሆን ፤ የግል ንብረት የለም እና ምድር እና ሞላው የኹሉም የጋራ ንብረት ነች እና የግል ንብረት ለማፍራት የኹሉንም ሰው የጋራ ፈቃድ ማግኘት አለብን ስንል ፤ ተፈጥሮ ለኹላችንም የእሚበቃ ነገር አትረፍረፋ ሰጥታን ሳለ ፤ የዓለምን ወይንም የሐገራችን ሕዝብ ኹሉ የጋራ ይሁንታ ስንጠብቅ በረኃብ ማለቃችን ነው እያለን ነው ።
እውነትም ደግሞ ፤ አንድ ሰው ተነስቶ ምድሩም ሰማዩም የእኔ ብቻ ነው እስከ አላለ ድረስ ወይንም የተወሰኑ ሰዎች ተነስተው ፤ ሌሎቹን አግልለው ምድሩም ሰማዩም የእኛ ነው ካል አሉ ፤ እያንዳንዱ ሰው በእኩልነት በአንድ በጋራ መርህ ፤ በራሱ ግዜ በተፈጥሮ ከእሚገኘው የተትረፈረፈ ኃብት ላይ ፤ በመርሁ አግባብ እያንዳንዱ ለራሱ መውሰዱ ተገቢ ነው ወይንም ከእዚኽ የተሻለም የተፈጥሮውን ኃብት በጋራ በፍትኃዊነት የመከፋፈያ መንገድም የለም ።
ምድሩን እንድንኖርበት ፣ እርሻውን እንድ እናርሰው ፣ ማዕድኑን እንድናወጣው ፣ ከብቱን እንድናርደው ፣ እህሉን እንድንበላው ፣ ወዘተ ፤ ተፈጥሮ ለኹላችንም ከሰጠችን ፤ እያንዳንዳችን ተፈጥሮ በሰጠችን ክህሎት ተጥቅመን ፤ ለግላችን የእሚሆነን በአንድ የጋራ መርህ እየተመራን ከመውሰድ የተሻለ ፤ የተፈጥሮን ስጦታ ለእለት ኑሮዋችን የእምናውልበት መንገድ የለም ።
ከእዚኽ በተጨማሪም ፤ ሰው የእኔ የእሚለው ነገር በሌለበት እና ይኽን የእኔ የእሚባለው ነገር የእሚታወቅበት መርህ በአልተዘረጋበት ወይንም የግል ንብረት ባለቤትነት መብት በአልተረጋገጠበት ማሕበረሰብ ውስጥ ምንም ዓይነት ስረዓት እና መረጋጋት እንደ እማይኖር ግልፅ ነው ። ሰዎች ጉልበታቸውን እና ክህሎታቸውን ያዋሉበትን ነገር ፤ በሕጋዊነት የእነርሱ አድርገው ከሌላ ሰው (ወይንም ከመላው ማሕበረሰብ) መለየት ከአልቻሉ እና እነርሱ የዘሩትን ማንም ማጨድ ከቻለ ፣ እነርሱ በገነቡት ቤት ማንም መኖር ከቻለ ፣ እነርሱ በአፈሩት ኃብት ማንም ማዘዝ ከቻለ ፣ ወዘተ ፤ ማሕበራዊ ትርምስ ፣ አለመረጋጋት ብሎም ልማት እንደ እሚጠፋ ምንም ጥያቄ የለውም ፤ ይኽም ነው የጦርነት ኹኔታ ማለት።
ይኽም በመሆኑ ፤ ሳይሰሩ በላተኞች እንደ አይሆኑ ፤ ይኽም ሳይሰሩ መብላት የስረዓት አልበኝነት መገለጫ ሆኖ መሐበረሰብን ሥራ በመፍታት ከማዝበጡ እና ማሕበራዊ ቀውስ ከማስከተሉ በፊት ፤ ጆን ሎክ እንደ አለው ሰዎች ጉልበታቸውን ፣ እውቀታቸውን ወይንም ካፒታላቸውን ቀላቅለው ከተፈጥሮ ኹኔታ ያወጡት ማንኛውም ነገር የግል ንብረታቸው መሆኑ በሕግ መታወቅ እና መከበር አለበት ።
ለእዚኽም ነው ጥንታዊው ፈላስፋ አርስታትል የጋራ ንብረት ባለቤትነት የጋራ ስራፈትነት እና አሳባቢነትን ከማስከትል ውጭ ፋይዳ የለውም የእሚል ምክር የመከረው ፦
“ለአብዛኛው የጋራ የሆነው ነገር በጣም ዝቅተኛውን እንክብካቤ ነው የእሚያገኘው። እያንዳንዱ በቀዳሚነት ለእራሱ ጉዳይ ነው የእሚያስበው ፤ ራሱን በቀጥታ እሚመለከተው ከአልሆነ በአብዛኛው የጋራ ጥቅም ለእሚወክለው ነገር ብዙም ቦታ አይሰጥም። ከሌላዎቹ ጉዳዮች በአሻገር ፤ እያንዳንዱ ሰው ሌላ ሰው ይፈጽመዋል ብሎ ለእሚያስበው ተግባር ምላሹ ቸልታ ነው።”
“For that which is common to the greatest number has the least care bestowed upon it. Everyone thinks chiefly of his own, hardly at all of the common interest; and only when he is himself concerned as an individual. For besides other considerations, everybody is more inclined to neglect the duty which he expects another to fulfill; [1]”
ለእዚኽም ነው ካፒታሊስቶች ፤ በእንግሊዘኛው (Common ownership is common neglect ወይንም የጋራ ንብረት የጋራ ቸልታ ነው) የእሚሉት።
ምድር ለህይወት በእሚያስፈልገው ነገር ተሞልታ ፤ አንድ ሰው ከእዚኽ የተፈጥሮ አቅርቦት ላይ ወይንም ከተፈጥሮ ባንክ ለህይወቱ የእሚያስፈልገውን ነገር በመውሰዱ ፤ ሌላው ዜጋ ማለት የእሚችለው እኔም ለእኔ የእሚያስፈልገኝ እወስዳለሁ ማለት እንጂ ፤ ከመውሰድህ በፊት የሰውን ልጆች ኹሉ ፈቃድ ማግኘት አለብህ ማለት ከሐገር ድንበር ጀምሮ እስከ ግለሰብ ቤት አጥር የአለውን ለማካለል ፤ እያንዳንዱ ሐገር እና ግለሰብ የዓለምን ሕዝብ ይኹንታ ማግኘት አለበት ማለት ስለ እሚኾን ፤ ይኽ ደግሞ ሊተገበር የእማይችል እና አስፈላጊነት የሌለው ቅድመ ኹኔታ መኾኑ ግልፅ ነው ።
አስቀድመን እንደ አልነው ፤ በሰብዓዊነት ላይ የተመሠረተው ዴሞክራሲ ፤ የሰዎችን በህይወት የመቆየት እና ህይወትን የተሻለ ለማድረግ ተፈጥሮዋዊ እኩል ነፃነታቸው የሌሎችን ሰዎች ተመሳሳይ እኩል ነፃነት እስከ አልገታ ድረስ ሙሉ ሕጋዊ እውቅና እና ከለላ አለው በእሚለው የነፃነት ዴሞክራሲ ላይ የተመረኮዘው ፤ የንብረት ባለቤትነት መብት ፤ ከላይ ፕሌቶን እና አዳም ስሚዝን ጠቅሰን ከአሳየነው የሥራ ክፍፍል ጋር ሲያያዝ ፤ የሰዎችን ማሕበራዊ የማምረት አቅም በመቶዎች እጥፍ ይጨምራል ።
ሰዎች ግን ይኽን በመቶዎች የተባዛውን የጋራ የማምረት አቅማቸውን ፤ የግል ንብረት ባለቤትነትን ባከበረ ስረዓት ውስጥ ፤ የንብረታቸው ሕጋዊ ባለቤት ሆነው ፤ በገበያ ነፃ ልውውጥ ከአልተቀያየሩት ምንም ጥቅም የለውም ። ወርቅ ቆፋሪው ብዙ ወርቅ ቢሰበስብ እና እህል አምራቹ ብዙ እህል ለእራሱ ቢሰበስብ ፤ እነ እዚኽ አምራቾች እጅግ ከተባዛው የተናጠል ምርታቸው በጣም ጥቂት የሆነውን ለራስ ፍጆታ ከመጠቀም ውጭ የቀረው ለእነርሱ ምንም ጥቅም የለውም ፤ ምክንያቱም ፦ ገበሬውም ለአንድ ሰው ከእሚበቃዉ በላይ መመገብ አይችልም ፥ ወርቅ ቆፋሪውም ወርቁን ሸጦ ከወርቁ ሽያጭ በእሚያገኘው ገቢ ሌላውን የሕይወት ፍላጎቱን ቢያሟላበት እንጂ ወርቁን ብቻ ይዞ መኖር አይችልም ።
በእዚኽም ምክንያት ፤ በሞያ ክፍፍል እና በአደረጃጀት በመቶ እጥፍ የተባዛው የማምረት አቅም ፤ በተባዛበት አግባብ በነፃ ገበያ ስረዓት ለማሕበረሰቡ ሲከፋፈል ነው ፤ ከተባዛው ተረፈ ምርት ዜጎች በጠቅላላው ተጠቃሚ የእሚሆኑት ።
እንደ እሚታወቀው ፤ እንደ ማርክሲስት ፣ ፋሺዝም ፣ ሶሻሊዝም ፣ የልማታዊ መንግሥት አስተሳሰቦች ፤ ገበያ ምርት የማከፋፈል ሥራ እንደ እሚሰራ ቢቀበሉም ፤ ገበያ ፍትሐዊ የሆነ ክፍፍል አያደርግም ስለ እዚኽ ገበያ በመዓከላዊ እቅድ ሙሉ በሙሉ መተካት አለበት ከማለት ጀምሮ ገበያ ክፍተት የአለው በመሆኑ የገበያን ክፍተት ለመሙዋላት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል እስከ ማለት ድረስ ይለያያሉ ።
ለእዚኽ የገበያ ትችታቸው ከእሚያቀርቡዋቸው ምክንያቶች ዋነኛው ፤ ሰው ግለኛ እና የራሱን ጥቅም ብቻ የእሚያሳድድ ስግብብ ስለ ሆነ ፤ በሞያ ክፍፍል እና በአደረጃጀት ሰብዓዊ ባሕሪ እጅግ የተባዛው የማምረት አቅም በፍትኃዊነት አይከፋፈለም የእሚል ነው ።
ከማንኝውም የፖለቲካ ርዕዮት የተላቀቀው የኢከነሚክስ ሳይንስ እንደ እሚያስተምረን ግን ፤ ነፃ የገበያ ውድድርን ማረጋገጥ የራሱ ፈተና ቢኖረውም ፤ በሳይንሳዊ መርህ የእሚመራ መንግሥት በሕግ እና በመዋቅር አቅም ነፃ ገበያን እንዲሰራ ከአስቻለው ፤ ከመዓከላዊ እቅድ አመራርም ሆነ ክፍተትን ለመሙላት መንግሥታዊ ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል በእሚል በገበያ ላይ ከእሚደረግ መንግሥታዊ ጣልቃ ገብነት በላይ ፤ በማሕበረሰብ ውስጥ ፍትሐዊ እና ውጤታማ የኃብት ክፍፍል በማድረግ ገበያን የእሚደርሰው እስከ አሁን አልተገኝም ።
ከላይ እንደ አልነው ፤ ፀረ ገበያ እምነት የአላቸው ሰዎች ፤ ገበያ አይሰራም ብለው ከእሚቃወሙበት ምክንያት አንዱ ፤ ሰዎች በተፈጥሮዋቸው ግለኞች ስለ ሆኑ እና ትርፍ አሳዳጅ ስለ ሆኑ ፤ የራሳቸውን ግላዊ ጥቅም ወይንም ትርፍ በእሚያሳድዱበት ግዜ ሌላውን ይጎዱታል የእሚል ነው ።
የኢከነሚክስ አባት የእሚባለው አዳም ስሚዝ እንደ አሳየን ግን ፤ እንዲያውም የሰዎች ግለኝነት እና ትርፍ የመፈለግ ባሕሪ ፤ እርሱ የእማይታይ እጅ በእሚለው መርህ ፤ በእቅድ ከእሚመራው በላይ በማሕበረሰብ ውስጥ ፍትሕዊ እና ውጤታማ የኃብት ስርጭት እንደ እሚያድርግ አስቀምጧል ።
እንደ ነጻ እና ሕጋዊ ገበያ በሥራ ድህነትን ማሸነፍ ለእሚፈልግ ነዳያን ኢከነሚያዊ ዋስትና የእሚስጠው መዋቅር የለም!
እንደ አዳም ስሚዝ ፤ የእማይታየው እጅ የአለው መርህ ፤ ሰዎች የራሳቸውን የግል ፍላጎት ለማሙዋላት በእሚንቀሳቀሱበት ግዜ ፤ ምንም እንኳን የስግብግብነት አካኼድ ቢመስልም ፤ ውጤቱ ማሕበራዊ እድገት እንዲሆን የእሚያደርገውን ‘ስውር’ ኃይል ነው ።
ምንም እንኳን ፤ ይኽንን የስውር ወይንም የእማይታይ እጅ አሰራር ፤ አዳም ስሚዝ ከዓለም ዓቀፍ የገቢ እና የወጪ ንግድ አንፃር ቢያስቀምጠውም ፤ ገበያ ዓለም ዓቅፋዊ ሆነ ሐገራዊ በኃሪው አንድ በመሆኑ ፤ መርሁ በገበያ ውስጥ የእሚሰራበትን አግባብ ያሳያል ፦
“የማንኛውም ማሕበረሰብ አመታዊ ገቢ ኹል ግዜ ያ ማሕበረሰብ ለመለዋወጥ የእሚያመርተው ምርት ዋጋ ጋር እኩል ነው ወይንም የበለጠ ትክክል ለመሆን በንግድ የእሚለዋወጠው ዋጋ ጋር አንድ ነው ። እያንዳንዱ ግለሰብም ፤ ይኽንን ሐገራዊ ኢንደስትሪ ለማገዝም ሆነ የኢንደስትሪውን ምርታማነት ለመጨመር ካፒታሉን በእሚያፈስበትም ግዜ ፤ እያንዳንዱ ግለሰብ እየአደረገ የአለው ይኽን ዓመታዊ ማሕበራዊ ገቢ ለማሳደግ እየሰራ ነው ። በእርግጥ ፤ በጠቅላላው ይኽን ሲያደርግ ማሕበራዊ ገቢውን ለማሳደግ ብሎ አቅዶ ወይንም ምን ያህል እንደ እሚያሳድገውም አውቆ አይደለም ። የውጭውን ሐገር ኢንደስትሪ ከማገዝ ይልቅ የሐገሩን ኢንደስትሪ ለማገዝ ሲነሳ ፤ የራሱን ደህንነት ታሳቢ አድርጎ ነው ፤ በተመሳሳይም የእሚሳተፍበትን ኢንደስትሪ በእሚችለው መጠን ምርታማነቱን ለማሳደግ ሲሰራ ፤ በልቡ የአለው እቅዱ የራሱን ጥቅም ማሳደግ ብቻ ነው ፤ በእዚኽ ግን ልክ ብዙ ግዜ እንደ እሚሆነው ፤ በእማይታየው እጅ እየተመራ ፤ ዓላማው ያልሆነውን ሌላ ግብ ያግዛል ። ... የራሱን ጥቅም ብቻ እያሳደደ ብዙ ግዜ አስቦ እና አቅዶ ከእሚያደርገው በላይ ማሕበራዊ እገዛ ያደርጋል ። ለሕዝብ አገልግሎት ነው የእምንነግደው ብለው የእሚነግዱ ሰዎች ለራሱ ጥቅም እንደ እሚነግደው ሰው ማሕበረሰብን ሲጠቅሙ አይቼ አላውቅም ።”
“But the annual revenue of every society is always precisely equal to the exchangeable value of the whole annual produce of its industry, or rather is precisely the same thing with that exchangeable value. As every individual, therefore, endeavors as much as he can both to employ his capital in the support of domestic industry, and so to direct that industry that its produce may be of the greatest value; every individual necessarily labors to render the annual revenue of the society as great as he can. He generally, indeed, neither intends to promote the public interest, nor knows how much he is promoting it. By preferring the support of domestic to that of foreign industry, he intends only his own security; and by directing that industry in such a manner as its produce may be of the greatest value, he intends only his own gain, and he is in this, as in many other cases, led by an invisible hand to promote an end which was no part of his intention. Nor is it always the worse for the society that it was no part of it. By pursuing his own interest, he frequently promotes that of the society more effectually than when he really intends to promote it. [48]“
ይኽን በሐገር ደረጃ የተቀመጠ የስውሩ እጅ አሰራር በግለሰብ ደረጃ እና በራሳችን አባባል (Paraphrased) ስናስቀምጠው ይኽን ነው የእሚመስለው ፦
የ
አንድ ግለሰብ ዓመታዊ ገቢ ፤ በዓመት ውስጥ ከአመረተው እና ለሽያጭ ወደ ገበያ ከአመጣው ምርቱ ጋር እኩል ነው። በአንዱ የኢንደስትሪ መስክ ተሰማርቶ በእዚኽ መልኩ ዓመታዊ ገቢውን የእሚያገኘው አንድ ዜጋ ፤ የራሱን ግላዊ ዓመታዊ ገቢውን ለማሳደግ በእዚኽ መልኩ ሲሰራ ፤ በእሚኖርበት ሐገር በተሰማራበት ኢንደስትሪ ላይ ቀጥተኛ የሆነ ጠቅላላ የኢንደስትሪ ምርት እና የምርት ሽያጭ ገቢ እንዲመጣ እየአደረገ ነው። በእርግጥ ሰውየው ወይንም ዜጋው አመታዊ ገቢውን ለማሳደግ ሲሰራ ፤ የሐገራዊ ኢንደስትሪውን እድገት ታሳቢ አድርጎ ሳይሆን ፤ በግለኝነት የራሱን ዓመታዊ ገቢ ማሳደግ ታሳቢ አድርጎ ነው ፤ በእዚኽ መልኩ የራሱን ገቢ ለማሳደግ በግለኝነት ሲሰራ ግን ፤ በእማይታየው እጅ አማካኝነት ፤ የሐገሬን ኢንደስትሪ አመታዊ እድገት ላሳድግ ብሎ ሲሰራ ከእሚያበረክተው በላይ በማበርከት ሐገራዊ ኢንደስትሪውን ያሳድጋል። በአዳም ስሚዝ ቃላት ፡
“የራሱን ጥቅም ብቻ እያሳደደ ብዙ ግዜ አስቦ እና አቅዶ ከእሚያደርገው በላይ ማሕበራዊ እገዛ ያደርጋል” ።
ከእዚኽ በተቃራኒ ግን ዜጎች ፤ በአንዳች ዓይነት የእዝ ኢከነሚ ስር ሆነው ፤ ለራሳቸው ሳይሆን የማሕበራዊ ምርት አካል እንዲሆኑ ተደርገው ያለ ግል ጥቅም እሳቤ ሲሰሩ ፤ አብዛኛዎቹ የፈረሱት የከምኒስት ኢከነሚ ሐገር የፋብሪካ ሰራተኞች ይቀልዱ እንደ ነበሩት “እነርሱም የእሚከፍሉን ይመስላሉ እኛ የእምንሰራ እንመስላለን” እንደ ሆነ የታየ ነው።
በከምኒስት ሐገራት ውስጥ ብቸኛ ቀጣሪ የሆነው መንግሥት ፤ በተሳሳተው የኢከነሚ ፖሊሲው ምክንያት ፤ በስፋት በተለያየ መስክ በተቀጣሪነት ለያዛቸው ዜጎቹ ይኽ ነው የእሚባል አመርቂ ደሞዝ መክፈል የእሚያስችለው ገቢ የሌለው በመሆኑ ፤ አብዛኛዎቹ ሰራተኞቹ ፤ ደሞዝ ቢከፈላቸውም ደሞዙ አመርቂ ሰለ አልሆነ ፤ መንግሥት ደሞዝ እንደ እሚከፍል በመምሰል ያንን ቀጭን ደሞዝ ይከፍላቸዋል ፤ ሰራተኞቹም ፤ ከመንግሥት ሥራ ውጭ አማራጭ ስለ ሌላቸው እና ይኽንንም ሥራ አልፈልግም ማለት ብዙ ፖለቲካዊ ችግር ውስጥ ስለ እሚያስገባቸው ፤ እነርሱም እንደ እሚሰሩ ይመስላሉ ግን ይኽ ነው የእሚባል አርኪ ሥራ አይሰሩም ፤ ስለ እዚኽ ፦ መንግሥትም እንደ እሚከፍላቸው ይመስላል እነርሱም እንደ እሚሰሩ ይመስላሉ።
ከእላይ እንደ አልነው ፤ ከሌሎች እንሳስት የላቁ ማሕበራዊ ወይንም ፖለቲካዊ ፍጥረት የአደረገን ፤ እጅግ የተለያዩ ፍላጎቶች ያሉን መሆኑ እና ምንም እንኳን ኹሉንም ፍላጎታችንን የእሚያረኩ ምርቶች በራሳችን ማምረት በአንችልም ፤ ኹላችንም የተለያየ ክህሎት እና ኃላፊነት የመወጣት ብቃትን ስለ ተላበስን ፤ ይኽ የተለያየው ክህሎታችን ምርት በገበያ ልውውጥ መርህ ሲተሳሰር ፤ ማለትም ወንበር አምራቹ ያመረተውን ወንበር ፤ ወንበር ለእሚፈልግ ሸጦት በብሩ ጤፍ ሲገዛበት ፤ ጤፍ አምራቹ ጤፉን በሸጠበት እንዲሁ ሌላውን ምርት ሲገዛበት ፤ ፈረጀ ብዙ የሆነው ማሕበራዊ ምርታችን ፈርጀ ብዙ የሆነውን ግላዊ ፍላጎታችንን በልውውጥ ወይንም በገበያ አማካኝነት ያቀርብልናል ፤ ያቀርብልናል ብቻ ሰአይኾን ነፃ ገበያ እያደገ ሲኼድ የእሚያቀርባቸው እቃዎች ጥራት ፣ ብዛት ፣ ዓይነት እየጨመረ እና ዋጋቸውም እየረከሰ ነው የእሚኼደው ።
አዳም ስሚዝ የእማይታየው እጅ የአለውም ይኽ ‘ስውር’ ኃይል እያንዳንዳችን የራሳችንን ጥቅም ስናሳድድ ፤ ሳናስበው የሌላውን ሰው ፍላጎት እንድ እናረካ እየአደረገን ፤ ጠቅላላ ማሕበራዊ ምርትን በብዛት እና በጥራት የእሚጨምርም ብቻ ሰአይሆን ፤ እያንዳንዱን ግለሰብ በተናጠል በልመና ሰአይሆን በተዋናይነት ከፍተኛ ተጠቃሚ የእሚያደርገን መሆኑን ፤ እንደ እዚኽ አስቀምጦታል ፦
“ከሰው በስተቀር በአሉት ኹሉም የእንስሳት ዝርያዎች ውስጥ ፤ አድገው ሲጎልብቱ ፤ ሙሉ በሙሉ ነፃ በመሆን ፤ በተፈጥሮዋዊ ኹኔታቸው ከሌላ ህያው ፍጡር ምንም ዓይነት እገዛ የእማይፈልጉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ ፤ የሰው ልጅ ግን በቋሚነት የባለንጀራውን እገዛ የእሚፈልግበት ገጠመኝ ያለ ሲሆን ፤ ይኽንን እገዛ ግን ከሰዎች ቸርነት ብቻ መጠበቁ ከንቱ ነው ። ምክንያቱም ፦ ሰዎቹ እርሱ የእሚፈልገውን ነገር ማድረጋቸው ለእነርሱ ጥቅም እንደ አለው ፤ ከግል ፍላጎታቸው አንፃር ከአሳያቸው ፤ ከሰዎች የእሚፈልገውን የማግኘት እድሉ ይጨምራል ። የስምምነት ወይንም የድርድር ኃሳብ የእሚያቀርብ ማንኛውም ሰው እየአደረገ የአለውም ይኼንን ነው ። እኔ የእምፈልገውን ይኼን ስጠኝ ፤ አንተ ደግሞ የእምትፈልገውን ይኽን ታገኝለህ ማለት ነው ድርድር ኹሉ ፤ በእዚኽም አግባብ ነው ሰዎች ከአላቸው እና እኛ ከእምንፈልገው መልካም ችሎታ ተጠቃሚ የእምንሆነው ። ከባለ ስጋ ቤቱ ፣ ከባለ ዳቦ ቤቱ ወይንም ከቢራ ጠማቂው ርህራኼ አይደለም ራታችንን እንድ እናገኝ የእምንጠብቀው ፤ ነገር ግን እነርሱ ለጥቅማቸው ከአላቸው ፍላጎት ነው ። ፍላጎታችንን የእምናሟላው የእነርሱ ሰብዓዊ ርህራኼ ላይ ተደግፈን ሰአይሆን ሰብዓዊ የግል ፍላጎታቸውን ተመርኩዘን ነው ፤ የእምናቀርብላቸው ፍላጎታችንን አይደለም የእሚፈልጉትን ነው ። ለማኝ ብቻ ነው በዋናነት በባለእንጀራው ርህራኼ ላይ መደገፍን የእሚመርጠው ። እርሱም ቢሆን ሙሉ በሙሉ አይደለም ። በእርግጥ መልካም ስብዕና የአላቸው ሰዎች ቸርነት ፤ ለመቆየት የእሚሆነውን ቀለብ ይሰጠዋል ። ይኽ ቸርነታቸው ምንም እንኳን ለህይወት የእሚያስፈልጉትን ነገሮች የእሚያቀርብለት ቢሆንም ፤ በራሱ ግን ኹሉንም ነገር አያቀርብለትም ሊያቀርብለትም አይችልም ። አብዛኛው ፍላጎቱ ፤ ልክ እንደ ሌላው ሰው በተለመደው የስምምነት ፣ የልውውጥ እና የግዢ አግባብ ነው የእሚሟላው ። አንዱ ሰው በእሚሰጠው ገንዘብ ምግብ ይገዛል ። አንዱ ሰው በእሚሰጠው አሮጌ ልብስ ፤ ልኩ በሆነው ሌላ አሮጌ ልብስ ይቀይረዋል ወይንም ማደሪያ ፣ ምግብ ወይንም ገንዘብ ለማግኘት አሮጌውን ልብስ ይሰጣል በምላሽ ፤ በእሚያገኘው ነገር እንደ ፍላጎቱ ልብስ ፣ ምግብ ወይንም ማደሪያ ይገዛበታል ።”
“In almost every other race of animals each individual, when it is grown up to maturity, is in-tirely independent, and in its natural state has occasion for the assistance of no other living creature,s But man has almost constant occasion for the help of his brethren, and it is in vain for him to expect it from their benevolence only.° He will be more likely to prevail if he can interest their self-love in his favour, and shew them that it is for their own ad-vantage to do for him whathe requires of them. Whoever offersto another a bargain of any kind, proposes to do this. Give me that which I want, and you shall have this which you want, is the meaning of every such offer; and it is in this manner that we obtain from one another the far greater part of those good offices which we stand in need of. It is not from he benevolence of the butcher, the brewer, or the baker, that we expect our dinner, but from their regard to their own interest. We address ourselves, not to their humanity but to their self-love, and never talk to them of our own necessities but of their advantages. Nobody but a beggar chuses to depend chiefly upon the benevolence of his fellow-citizens. Even a beggar does not depend upon it entirely. The charity of well-disposed people, indeed, supplies him with the whole fund of his subsistence. But though this principle ultimately provides him with all the necessaries of life which he has occasion for, it neither does nor can provide him with them as he has occasion for them. The greater part of his occasional wants are supplied in the same manner as those of other people, by treaty, by barter, and by purchase. With the money which one man gives him he purchases food. The old cloaths which another bestows upon him he exchanges for other old cloaths which suit him better, or for lodging, or for food, or for money, with which he can buy either food, cloaths, or lodging, as he has occasion. [48]“
ይኽ ከተፈጥሮዋዊ የክህሎት ክፍፍል እና ከነፃ የልውውጥ መርህ የእሚገኘው ማሕበራዊ ቁሳዊ እድገት እና የግለሰቦች ተጠቃሚነት ፤ አንድ መሐበረሰብ ወይንም መንግሥት በማዕከላዊ እቅድ ላሳካው ቢል ፤ መዓከላዊ እቅድ በነጻ ገበያ ከእሚከውኑ ፈረጀ ብዙ ሥራዎች ውስጥ ፤ ለምሳሌ ፦ በገበያው ውስጥ የአለውን የአገልግሎት እና የምርት ፍላጎት በሐገሪቱ ውስጥ ከእሚገኘው የማምረት ክህሎት ጋር ማጣጣም የእሚባል እጅግ ፈታኝ የሆነ ፤ ምናልባትም የእማይችል ሥራ ይጠብቀዋል ።
በሆነ ተዓምርም ይኽንን ፍላጎት እና የማምረት አቅም ማጣጣም ቢችልም ፤ ዞሮ ዞሮ ገበያም የእሚሰራው ይኽንኑ በመሆኑ ፤ ገበያ በእማይታየው እጅ አማካኝነት ‘በነፃ’ የእሚሰራውን ሥራ መንግሥት የሐገርን ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ኃብት አፍስሶ ደግሞ እንደገና መሥራቱ ፤ ምንም ፋይዳ የለውም ብቻ ሰአይሆን ኃብት ማባከንም ነው ።
ጎማ ተፈጥሯል ደግመኽ ጎማ ለመፍጠር አትላላጥ እንደ እሚለው የእንግሊዘኛ አባባል (Do not reinvent the wheel) ፤ ገበያ በራሱ ግዜ የእሚሰራውን በሰው ሰራሽ ስረዓት ለመተካት መሞከር ፤ ያለ እና በተሻለ ኹኔታ የእሚሰራን ነገር ለመድገም የእሚደረግ ከንቱ ጥረት ነው የእሚሆነው።
ከእዚያኽም በአሻገር ፤ መዓከላዊ እቅድም ሆነ የገበያን ክፍተት ለመሙላት የእሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች ፤ የዜጎችን የኃብት ወይንም የንብረት ባለቤትነት መብት በአንድም በሌላም መንገድ ፤ የእማይታየው እጅ በውጤታማነት እንደ አይሰራ ሊያደርግ በእሚችል መልኩ ስለ እሚጎዱት ፤ የዜጎች የንብረት ባለቤትነት መብት የእማይነካ ‘ቅዱስ’ መብት በአልሆነበት የፖለቲካ ስረዓት ውስጥ ፤ ፍትኃዊው እና ውጤታማው የማሕበረሰብ የኃብት አከፋፋይ ፥ ገበያ ፤ በአግባቡ መሥራት ስለ እማይችል ፤ ውጤቱ መልሶ የሰዎች ህይወት እና ንብረት ዋስትና የእሚያጣበት የጦርነት ኹኔታ እና ከተሰባበረ ገበያ የእሚመነጭ ማለቂያ የሌለው የኢከነሚያዊ ድህነት ነው የእሚሆነው።
ከነፃነት ዴሞክራሲ ውጭ የአሉት ርዕዮቶች በሙሉ ፤ በአንድም በሌላ ምክንያት ፥ የግለሰብን ማሕበራዊ አህድነት ፤ በመርህ ደረጃ ስለ እማይቀበሉ ፤ ከግለሰበ የማሕበራዊ አህድነት የእሚመነጩትን ፣ የግለሰብን የንብረት ባለቤትነትም መብት ፥ በጣም ለዘብተኛ ከሆኑ በመርህ ደረጃ ሰአይሆን እንደ ኹኔታው የእሚያከብሩት ሲሆኑ ፤ በፅንፉ ጥግ ከሆኑ ደግሞ እስከ እነ አካቴው የስግብግብ ቡርዣ በኃሪ ወይንም ሌላ ስያሜ ሰጥተው በመከልከል ፤ ማሕበረሰብን ለአመረጋጋት ከመዳረግ በአሻገር ፤ የገበያ ስረዓቱን በመበጣጠስ የማሕበረሰብን ኢከነሚያዊ ምርታማነት እና የግለሰቦችን ተጠቃሚነት በከፍተኛ ደረጃ ይጎዳሉ።
ይኽም በመሆኑ ፤ የነፃነት ዴሞክራሲ ግለሰቦችን የፖለቲካ ማሕበረሰብ አህድነት ተቀብሎ በማክበሩ ፤ ማሕበራዊ ደህንነትን ከማረጋገጡ በተጨማሪ በእሚታወቀው የኢከነሚክስ ሳይንስ መሠረት የግል ንብረት ባለቤትነትን በማክበር እና ዜጎች በነፃነት በገበያ እንዲለዋወጡ በማድረግ የፀና እና ቀጣይ ኢከነሚያዊ እድገትን ያስችላል ።
በነፃነት ዴሞክራሲ አግባብ የተዋቀረች ሐገር ለዜጎቿ የእምትስጠው ሦሥተኛ ፋይዳ ፤ ዜጎች ከዝበት የፀዳ ብሔራዊ ፍቅር እንዲኖራቸው ማድረግ ነው ።
ብሔራዊ ወይንም የሐገር ፍቅር ፤ ሰዎች ሰብዓዊ ባሕሪያቸው ባአላበሳቸው ክህሎት ፤ በደስታ ለማሕበራዊ እድገት ፥ ጥቅም የአለው አስተዋፅዖ እንዲ ያደርጉ በማድረግ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለሐገራቸው ደህንነት የተለያየ ዓይነት እና መጠን የአለው መስዕዋትነት እንዲከፍሉ የእሚያደርግ በመሆኑ ዜጎች ለሐገራቸው ልኩን የጠበቀ ፍቅር እንዲኖራቸው ይገባል ።
የነፃነት ዴሞክራሲ ይኽንን ዓይነት ብሔራዊ ፍቅር እንዲኖራቸው የእሚያደርገው ፤ ዜጎች ከማንነታቸው ውስጥ ትልቁን እና ዋነኛውን ሰብዓዊነታችውን የሐገራቸው ተግባራዊ ትርጓሜ አንኳር እንዲሆን በማድረጉ ነው ።
የነፃነት ዴሞክራሲ ከሐገር ፍቅር አንፃር የአለውን ፋይዳ ለማስቀመጥ ፤ ሐገራት መደ መሆን የእሚመጡበትን ፣ የሐገር ፍቅር የእሚዳብርበትን እና የእሚገለፅበትን እንዲሁም የሐገር ፍቅር የእሚሸረሸርብተን አግባብ መቃኘቱ ያግዛል ።
ኹላችንም እንደ እምናውቀው ፤ ዛሬ በዓለም ያሉ ወደ 200 የእሚጠጉ ሐገራት ፤ ሰማይ እና ምድር ሲፈጠሩ አንስቶ የነበሩ ሐገራት እንደ አልሆኑ እንረዳለን ። አይደለም ሰማይ እና ምድር ከተፈጠሩበት ግዜ አንስቶ ፤ የሰው ልጅ ቁጥር በምድር ላይ በጣም ጥቂት በነበረበት ግዜ ሐገራዊ ድንበር የእሚባል ነገር አልነበረም ።
የዛሬዎቹ ኢትዮጵያ ፣ ህንድ ፣ ቻይና ወይንም ሌላ በአለ ድንበር ሐገራት ወደ መኾን የመጡት የሰው ልጅ ፖለቲካዊ ታሪክ የራሱ ረዥም ፖለቲካዊ ዝግመት ውስጥ ከአለፈ በኋላ ነው ።
ያም ማለት ፤ ሐገራት በራሳቸው ፖለቲካዊ እና ኢክኖሚያዊ ምክንያት በታሪክ ኺደት የተፈጠሩ ታሪካዊ ክስተቶች ናቸው ማለት ነው ።
ሐገራት ወደ መሆን የመጡበትን ኺደት ስናይ ፤ ሐገራት በሰዎች በህይወት የመቆየት እና ህይወትን የተሻለ የማድረግ ፍላጎት እና ልዩ ሰብዓዊ ክህሎት እየተዘወሩ ዛሬ የእምናውቃቸው ሐገራዊ ቁሳዊ አካላቸውን ፥ የድንበር ክልል እና የሕዝብ ስብጥር ፤ ለመያዝ እንደ ቻሉ እንረዳለን።
የሐገር አካል ፤ በእዚኽ መንፈሳዊ ወይንም በሰዎች በህይወት የመቆየት እና ህይወትን የተሻለ የማድረግ ፍላጎት እና ልዩ ሰብዓዊ ክህሎት ምክንያት እየተነዳ ፤ በጎታች እና ገፊ ፤ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ምክንያቶች በታሪካዊ ኺደት የእሚገነባ ነገር ነው ። የይትኛውም ሐገር ዜጎች ፤ በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ በሙሉ ተሰብስበው ፤ ሐገራችን ስሟ እንዲህ ይባል ፣ የድንበር ክልሏም ከእዚኽ እስከ እዚኽ ይኹን ብለው በእሚታወቅ ስምምነት ሐገራቸውን አልፈጠሩም ።
በተፈጥሮዋዊው ዓለም ፤ ተራሮች ፣ ወንዞች ፣ ተፋሰሶች ፣ ደሴቶች ፣ ወዘተ ፤ እስከ ዛሬ ድረስ ሳይንስ ሊያብራራው በአልቻለው አንድ የመፍጠር መርኽ እየተነዱ እንደ ተፈጠሩት ፤ ሐገራትም በዜጎቻቸው ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፍላጎት እና በተመሳሳይ የሌሎች የዓለም ሕዝብ ፍላጎት መካከል በአለ የኃይል መሳሳብ እና መገፋፋት የተፈጠሩ ክስተቶች ናቸው ።
ምንም እንኳን ሐገራት መፈጠር ከጀመሩ በሺ የእሚቆጠሩ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም እና በሺ የእሚቆጠር እድሜ የአላቸው ሐገራት ያሉ ቢሆንም ፤ በመቶ እና በአስርት ዓመታት የእሚቆጠር እድሜ የአላቸው ሐገራትም ቢሆኑ ፤ ፋይዳ እና ቀጣይነት የአለው የረጋ ሐገር መሆን የእሚችሉት ፤ ሐገር እንዲሆኑ የአስቻላቸው ረዥም ዘመን የቆየ ጎታች (በሐገር ውስጥ) እና ገፊ (ከሐገር ውጭ) ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ምክንያት የአለ እንደሆነ ነው ።
ምክንያቱም ፤ የአንዲት ሐገር ሕልውና በዓለም ዓቀፍ ፣ በከባቢያው እና በሐገር ውስጥ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ የኃይል አሰላለፍ የእሚወሰን ነገር በመሆኑ ።
አጠር በአለ አገላለፅ ፤ ከመቶ እና ከእዚያኽ በላይ እድሜ ያላት ሐገር በታሪክ አጋጣሚ ተሰርታ የእምትገኝ ታሪካዊ ክስተት ወይንም ስጦታ ነች ። ከእዚኽ የተነሳ ሐገራት የተለያዩ የዓለም ሕዝብ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ፍላጎቶች በረዥም ታሪካዊ ዑደት ያመጡዋቸው ታሪካዊ ክስተቶች እንጂ ገጠመኝ ወይንም ቀቢፀ ተስፋ ያመጣቸው የዘፈቀደ አደረጃጀት ወይንም ግንባታዎች አይደሉም ማለት ነው።
ያም ማለት ፤ ሉዓላዊ የሆኑ ፣ ዓለም ያወቃቸው ሐገራት ለመሆን ያበቁዋቸው ፤ በመቶዎች አንዳንዴ ደግሞ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የተካኼዱ ፖለቲካዊ ፣ ኢከነሚያዊ ፣ ወታደራዊ ፣ ውስጣዊ (በሐገር) ፣ ዓለማ ዓቀፋዊ ፤ ብዙ ገፊ እና ጎታች ምክንያቶች ወይንም ኃይላት (push and pull factors) አሉ ማለት ነው ።
በሐገር ውስጥ ወይንም በጎታች ምክንያትነት ፤ ዜጎች በጋራ ውጤታማ ሆነው ለመኖር የእሚያስፈልጋቸውን የሕዝብ ብዛት እና የመሬት ስፋት ለማግኘት ሲሰባሰቡ እና ሲስፋፉ ፤ ከሐገር ውጭ ወይንም በገፊ ምክንያትነት ደግሞ የሐገር ውስጥ ለመኖር የእሚያስፈልጋቸውን የሕዝብ ብዛት እና የመሬት ስፋት ለማግኘት በእሚንቀሳቀሱበት ግዜ ፤ በተመሳሳይ ኹኔታ ከእሚንቀሳቀስ ሌላ ሕዝብ ጋር የኃይል መመጣጠን መስፋፋቱን እየገደበው ፤ በእዚኽ ውስጣዊ መሳሳብ እና ውጫዊ መገፋፋት ኺደት ነው ፤ ሐገራት ሐገራት ሆነው መቆም የእሚችሉት።
ከላይ እንደ አልነው ፤ ሐገራት በእዚኽ መልኩ የእሚመጡ ታሪካዊ ክስተት በመሆናቸው ፤ ውስጣዊ ወይንም ጎታች የእምንላቸው ፤ ለነዋሪዎቿ በቂ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኃብት አቅርቦት ማድረግ የእምትችል እና ይኽንን ለማሕበራዊ መስተጋብሩ ፋይዳዊ ህልውና (Viable existence) የእሚያስፈልጉ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኃበት ፤ ከውስጣዊ እና ውጫዊ ጥቃት (ገፊ ምክንያት) መከላከል መቻል ፤ ሐገራት በረጅሙ የታሪክ ኺደት ዛሬ የያዙትን ሐገራዊ ማዕቀፍ ብሎም አቋም እንዲይዙ አድርጎዋቸዋል ።
ሐገራት በእዚኽ መልኩ በረዥም የታሪክ ኺደት ለህልውና በእሚያስፈልግ የመስፋፋት ኺደት እና ይኽንን መስፋፋት በእሚገድቡ እና የያዙትን ይዞ የማቆየት ውስጣዊ አቅም በማዳበር ኺደት የእሚፈጠሩ በመሆኑ ፤ አብዛኛው ሐገራት አንዳንድ ሰዎች እንደ እሚሉት ፤ ሐገራት ማለትም ቁሳዊ ወይንም ዉጫዊ አካላቸው (የሕዝብ ስብጥራቸው እና ድንበራቸው) ኹሉ የተመሠረተው ፤ ምንም እንኳን የጋራ ተጠቃሚነትን ታሳቢ ማድረግ ቢሆንም መነሻው አተገባበሩ ግን በቀዳሚው ሐጥያት (Original Sin) እርሱም በወታደራዊ ኃይል በተገኘ ድል ነው ።
ከእዚኽ እና ከሰዎች ሰብዓዊ ባሕሪ የተነሳ ፤ አኹን በዓለማችን ላይ ያሉ ሐገራት በሙሉ በኃማኖት ፣ በዘር ፣ በነገድ ፣ ወዘተ ፤ ወጥነት የላቸውም ሊኖራቸውም አይችልም።
ከ1 ሚልየን ትንሽ የእሚበልጥ ነዋሪ ያላት ጅቡቲ በውስጧ ወደ አራት ዓይነት ነገዶች አሉባት ፣ ኬንያ ከ20 የእማያንሱ የተለያዩ ቋንቋዎች የእሚናገሩ ነገዶች ፥ የተለያዩ ዓይነት ኃይማኖት የእሚከተሉ ሕዝብ አሏት ፣ ናይጄሪያ ከ280 በላይ ነገዶች እና እስልምና ፣ ክርስትና ፣ ጁዳይዝም ፣ ባሕላዊ እምነት የእሚከተሉ ሰፊ ሕዝብ አላት ፣ ህንድ ከ2 ሺ በላይ ነግዶች አሉባት ፣ ቻይና በውስጧ ከ30 በላይ ነገዶች ይዛለች ።
ከእዚኽም የተነሳ ፤ እነ እዚኽ የሐገራት አካላዊ ቁመናዎች ፥ በነዋሪዎቹ ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፍላጎት እየተነዱ በረዥም ዘመን ውስጣዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ ትግል መመሥረታቸው ፤ ሐገራት በእዚኽ ኺደት በውስጣቸው የያዙዋቸው ፦ ኃይማኖት ፣ የቆዳ ቀለም ወይንም ዘር ፣ ነገዳዊ ፣ የቋንቋ ፣ ወዘተ ፤ ልዩነቶች ፤ በሐገሪቱ ውስጥ ነዋሪ በሆኑት ሕዝብ ሰብዓዊ በሆነው (እንደ ኃይማኖት ፣ ዘር ፣ ነገድ ፣ ወዘተ ፤ የቅርጽ ልዩነት) በእሚሻገሩ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ፍላጎቶች መሳሳብ እና ዓለም ዓቀፉ አሰላለፍ እና ኃይል በእሚያደርስባቸው ግፊት ምክንያት ፤ በአንድ ሐገር ውስጥ ለእሚኖሩ ሕዝብ የአላቸው ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ፋይዳ እምብዛም ነው።
በሌላ አገላለጽ ፤ ሰዎችን ማሕበራዊ ፍጥረት የአስባላቸው ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ፍላጎታቸውን ተከትለው የመንቀሳቀስ አካኼድ ፤ በሌላ አስገዳጅ ኃይል ከአልተገደበ በስተቀር ፤ ከሌላው ግዜ አመጣሽ ፤ ማለትም ፦ ከኃይማኖታዊ ፣ የዘር ፣ የነገድ ፣ ወዘተ ፤ ልዩነታቸው በላይ ለብሔራዊ ህልውናቸው የበለጠ ፋይዳ የአለው ነው።
የሐገራትን አካላዊ ቁመና በተመለከተ አንድ ልንገነዘበው የእሚገባው ሌላ ጉዳይ ጉዳይ ፤ ምንም እንኳን የሐገራት የአፈጣጠር ኺደት ሐገራትን በአስገዳጅነት የልዩነት ቋት ቢያደርጋቸውም ፤ የማሕበራዊ ስብጥር ልዩነት ሐገራት ከተፈጠሩ በኋላም የእሚቀር ነገር አይደለም። ያም ብቻ ሳይሆን አንድን ማሕበረሰብ እንዴትም አጥብበን ብንወስደው ሊታረቁ የእማይችሉ ማሕበራዊ ተቃርኖዎች መፈልፈላቸው የእማይቀር መሆኑ ትንሽ ከአሰብንበት ለኹላችንም ወገግ ብሎ ይታየናል ። ከእነ ተረቱም ፤ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው!
ስለ እዚኽ ፦ በጤናማው የሐገር ግንዛቤ መሠረት ፤ ግዜ አመጣሽ ማሕበራዊ ቅርጻቸው (ኃይማኖት ፣ ነገድ ፣ አፍ የፈቱበትን አንዱ ቋንቋ ፣ ወዘተ ) ፤ ተፈጥሮዋዊ ከሆኑት ፦ በህይወት የመኖር መብት ፣ ኃሳብን የመግለጽ መብት ፣ የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብት ፣ ንብረት የማፍራት መብት ፣ ወዘተ ፤ የእማያግዳቸው እና እንደ ግለሰብ ወይንም እንደ ዜጋ በማሕበራዊ የቅርጽ ልዩነታቸው ሳይወሰኑ ፤ ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን በነጻነት መከተል እና መጨበጥ የእሚችሉ ከሆኑ ፤ ሊወገድ የእማይችለው የማሕበራዊ የቅርጽ መዥጎርጎር ፤ የአንዲት ሐገር የአለመረጋጋት ምንጭ ሊሆን አይችልም።
ሆኖም ግን ፤ በተለይ የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ፤ ሰዎች ከአሉዋቸው እንደ ኃይማኖት ፣ ዘር ፣ ነገድ ፣ ወዘተ ፤ በተሻገረ ኹኔታ የእሚያከብርላቸው እንደ ነጻነቱ ዴሞክራሲ የአለ ስረዓት ውስጥ ዜጎች በእማይኖሩበት ግዜ እና የነጻነቱን ዴሞክራሲ ከማክበር ይልቅ እነ እዚኽን ማሕበራዊ የቅርጽ ልዩነቶች ፦ የእንትን ኃይማኖት ተከታይ ሆይ በኃይማኖትህ ምክንያት እየተበደልክ ነው እና ተነስ ፣ የእዚኽ የእዚኽ ነገድ አባል ቁጥርህ አናሳ በመሆኑ እየተጨፈለቅክ ነው ወይንም ቁጥርህ ብዙ ስለሆነ ብዙ መብት ያስፈልግኃል ፣ ወዘተ ፤ በእሚሉ ዓይነት ቅስቀሳዎች ከተራገቡ ፤ በዜጎች መካከል ቅራኔን አባዝተው ፤ ሐገር መበጥበጥ በአይችሉ እንኳን የሐገር ፍቅርን ማዳከም ይችላሉ።
የነፃነቱ ዴሞክራሲ ርዕዮት ልህቀትም ፤ እነ እዚኽን የሐገር ምሥረታ ውጤት የሆኑ እና ከማንኛውም ማሕበረሰብ ውስጥ ሊጠፉ የእማይችሉ ማሕበራዊ ልዩነቶች ተሻግሮ ፤ ዜጎችን የጋራ በእሚያደርጋቸው እና በታሪክ አጋጣሚ ፦ ከወራሪው ወገን ይሁኑ ከተወራሪው ፣ ከአሸናፊው ወገን ይሁኑ ከተሸናፊው ፣ የእዚኽኛው ቋንቋ ተናጋሪ ይሁኑ የእዛኛው ፣ የእዚኽኛው ኃይማኖት ተከታይ ይሁኑ የእዛኛው ፣ ባለ ኃብት ይኹኑ ነዳያን ፤ በአጠቃላይ ሊታረቅ የእማይችል ቡድናዊ ወይንም ማሕበራዊ ልዩነታቸውን ተሻግሮ ፤ የእዚኽ የማሕበራዊ ልዩነት ኹሉ ተሻጋሪ የሆነው እና ኹሉም ሰብዓዊ ፍጥረት በጋራ የእሚጋራው ሰብዓዊ ባሕሪያቸው ላይ ተመርኩዞ ፤ የሐገራቸውን ህልውና መሠረት ሰብዓዊነታቸው የእሚያደርግ በመሆኑ ፤ የዓዕምሮ ብርሀኑ እና ፋላጎቱ ለአላቸው ሰዎች ፤ የእማይታረቀው እና ብዙም የእማይፈይደው የቅርፅ ልዩነታቸው ላይ ተንጠልጥሎ ከመብሰልሰል ፤ አንድ አድርጎ በእሚያስተባብራቸው እና ብዙ በእሚፈይደው ሰብዓዊነታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ማድረግ የእሚችል በመሆኑ ፤ ዜጎች በጥረታቸው ብዙም ሊለውጡ በእማይችሉት የሐገር ቁሳዊ አካል ውስጥ የተሻለ ብሔራዊ ስሜት እንዲኖራቸው ያስችላል ።
የሐገር ቁሳዊ አካል ከእሚባሉት ውስጥ ፤ አንዱን የባንዲራ ጉዳይ እንኳን ብንወስድ ፤ የባንዲራዉ ዓይነት ግድ ከእማይሰጠው አንስቶ ባንዲራው ይኽ መሆን አለበት ብሎ በስሜት እስከ እሚከራከረው ድረስ የተለያዩ ብዙ አንጃዎች አሉ ብቻ ሰአይሆን ፤ ጉዳዩ ርዕስ መሆኑ እስከ ቀጠለ ድረስ ውኃ ሰማያዊ የነበረው ባንድራ ፤ በቀኝ በኩል በላይኛው ጫፍ ላይ ነጭ ርግብ ትኑርበት ወይንም አትኑርበት የእሚለው አከፋፍሎ እና አነታርኮ ሲያበቃ ፤ በሌላ ግዜ እና አጋጣሚ ደግሞ ርግቧ በዘንባባ ዝንጣፊ ትተካ በእሚል ታድሶ እንደገና አከፋፍሎ ማነታረኩን ይቀጥላል ።
ስለ እዚኽ ፦ በባንዲራው ጉዳይ ፤ ኹሉም ሰው የእሚስማማበት እና ቋሚ የሆነ ባንዲራ ሊኖር አይችልም ፤ ይኽም በመሆኑ ፤ የትኛውም ዓይነት ባንዲራ ቢሆን አንዱን አንጃ ማስድሰቱ እና የተቀሩትን ቅር ማሰኘቱ አይቀርም ። ስለ እዚኽ ፦ የእሚበጀው ፤ ከተቻለ የእሚበልጥ ቁጥር የአለው ማሕበርሰብ የእሚደግፈውን ባንዲራ መቀበል ፤ ከአልሆነም የትኛውንም ባንዲራ በስምምነት ተቀብሎ ወደ ዋናው ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያ ጭብጥ ማምራት ነው ። ምክንያቱም ፦ የባንዲራ እና መስል ጉዳዮች ውለው ቢያድሩባቸው በቋሚነት በኹሉም ስምምነት ሊወሰኑ አይችሉም ።
ኹሉም ፖለቲካዊ አጀንዳዎች እንደ እዚኽ ከፋፋይ ናቸው ሊባል ይችላል ፤ ነገር ግን በሐገር ቁሳዊ አካላት ላይ የእሚደረጉት የአንጃ ንትርኮች ፤ በአብዛኛው ከእሚያስነሱት ግርግር በአሻገር ለአሸናፊው አንጃ ራሱ የእሚሰጡት ይኽ ነው የእሚባል ተጨባጭ ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ጥቅም የለም ።
አንድ አንጃ እርሱ የእሚፈልገው የባንዲራ ዓይነት በእሚውልበለብበት ሐገር ውስጥ ፤ ሕይወቱ ዋስትና የእማያገኝበት ፤ በፈለገው ሰዓት ወጥቶ የእማይገባባት ፣ በእሚያዋጣው እና በእሚፈልገው ሥራ ላይ ተሰማርቶ ለኑሮ የእሚያስፈልገውን ገቢ የእማያገኝበት ፣ ኃሳቡን በእሚመስለው መንገድ የእማይገልፅባት እና በኃሳብ ከእሚመስሉትም ጋር የመደራጀት መብት ከሌለው ወይንም ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ጥቅሙ የእማይከበርባት
እና እርሱ የእሚወደው ዓይነት ባንዲራ የእሚውለበለብባት ሐገር ምን ታድርግለታለች?
ይልቁንስ ፤ እርሱ የእማይወደው ወይንም ብዙም ስሜት የሌለው ባንዲራ በእሚውለበለብበት ሐገር ፤ ህይወቱ ዋስትና ኖሯት ፣ በነፃነት ወጥቶ እና ገብቶ ፣ በእሚወድው እና በእሚያዋጣው የሥራ መስክ ተሰማርቶ በህይወት ለመቆየት እና ህይወቱን ለማሻሻል የእሚያስችለውን ገቢ አግኝቶ ፣ ለወደደው ፖለቲከኛ እና ኃሳብ ድጋፉን ሰጥቶ ወይንም በወደደው መልኩ በፖለቲካው ተሳትፎ ፤ የእሚኖርበት ሐገርን ቢመርጥ አይበጀውም?
ከላይ ለቀረበው ጥያቄ መልሱ አዎንታዊ ከሆነ ፤ በአንድ ሐገር ውስጥ ፤ እንደ ባንዲራ ያሉ ፤ ኹሉም ሰው ሊስማማባቸው በእማይችል እና ቢስማማባቸውም እንኳን ፤ ለተስማሚዎቹ ከግዜያዊ ስሜታዊ እርካታ ውጭ ምንም ተጨባጭ ኢከነሚያዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳ በሌላቸው አጀንዳዎች ላይ ወይንም በዜሮ ድምር ፖለቲካዊ አጀንዳዎች የፖለቲካዊ ምህዳሩ ሲቃኝ እና ዜጎች ሊታሪቁ በእማይችሉ ፋይዳቢስ አጀንዳዎች ተከፋፍለው ሲሸካከሩ ፤ ከእዛኽም አልፎ እነ እዚኽ እርባናቢስ አጀንዳዎች የሐገር ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ተቋሟት የእሚዋቀሩባቸው መርህዎች ሲሆኑ ፤ ሐገር የዜጎች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት የእሚከበረባት በእዛኽም የዜጎች ፖለቲካዊ እና ኢከነሚያዊ ተጠቃሚነት የተረጋገጠባት ልትሆን አትችልም ።
የልዩነት ቋት በሆነው የሐገር ቁሳዊ አካላት ላይ የአተኮረ ፖለቲካዊ አቅጣጭ እየተከተሉ ብሔራዊ አንድነትን ማበራታት አይቻልም።
ይኽም የዜጎችን ብሔራዊ ስሜት በግዜያዊነት እና ከላይ ከላይ ሰአይሆን ፤ በቀጣይነት እና ስር በሰደደ ኹኔታ እንዲ ሸረሸር ያደርጋል ።
በዴሞክራሲያዊት ወይንም የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲ መብት ማክበር የፖለቲካ መዋቅሯ የማይነቀነቅ አንኳር በሆነባት ሐገር ግን ሰዎች (ዜጎች) በሐገራቸው ፤ ቁሳዊ እና ግዜያዊ በሆኑት ፦ የኃይማኖት ፣ የፖለቲካ እምነት ፣ የቋንቋ ፣ የነገድ ፣ የዘር ፣ ወዘተ ፤ ልዩነታቸው ሳይወሰኑ የሰብዓዊ እና የዴሞክራሲያዊ መብታቸው ባለቤት እና ተጠቃሚ ስለ እሚሆኑ ፤ ከብዙው ውጫዊ ልየነታቸው የተሻገረ ሐገራቸውን እንዲወዱ እና እንዲያከብሩ የእሚያደርጋቸው ፤ የኢከነሚያዊ እና የፖለቲካዊ ተጠቃሚነታቸውን የእሚያረጋግጥላቸው ምክንያት እንዲኖራቸው ይሆናሉ።
በዴሞክራሲያዊት ሐገር ዜጎች ፦
ይኽም የዴሞክራሲ እሴት ሕዝብ በአግባቡ ሲረዳው እና በሕዝቡ ውስጥ ሲሰርፅ ወደ ጤናማ ብሔራዊ ስሜትነት ያድጋል ።
ስለ እዚኽ ፦ በነፃነት ዴሞክራሲ መርሕ ሐገር ስትዋቀር ፤ ዜጎች በሰብዓዊነት ታንጸዉ ፤ ለወገን ዜጎቻቸው ህይወት እና ንብረት አክብሮት የአላቸው እና ይኽ ለሆነባት ሐገራቸው ጤናማ ብሔራዊ ፍቅር የያዙባት ፤ እነ እዚኽም እሴቶች በተራቸው ፦ ሐገራቸው የተረጋጋች እና ቀጣይነት የአለው ማሕበራዊ እና ኢከነሚያዊ እድገት ያላት እንድትሆን ያደርጋሉ ።
[2] በእሳት የእሚሰራው ሞተር እንደ ተፈጠረ አከባቢ ፤ በማብላያ ቤቱ እና ፒስተኑን በያዘው ቤት መሐከል ያለውን በር ፤ በእየግዜው እንዲከፍት የተቀጠረ ልጅ ፤ ለጨዋታ ከአለው ጉግት ፤ በሩን ከቫልቭ ጋር በገመድ በማያያዝ በራሱ ግዜ እንዲከፈት በማድረግ ፤ ማሽኑ ከተፈጠረ በኋላ በማሽኑ ላይ የተደረገውን ትልልቅ መሻሻል አንድ ብላቴና እንደ አስተዋወቀ በመተረክ ፤ የስራ ክፍፍል ወደ ማሽን ፈጠራ እንዴት እንደ እሚያመራ አዳም ስሚዝ ይተርካል።
[3] በዋናነት በቶማስ ሆብስ የተቀነቀነው እና አምባገነናዊ ማሕበራዊ ውልተኝነት የአልኹትን ይኽን የስነ መንግሥት ትርክት ፤ ምንም እንኳን ከእዚኽ በላይ በአለው ዴሞክራሲያዊነት እና ሐገር በእሚለው ንዑስ ስር ኃሳቡን ብናነሳውም ፤ ጉዳዩን ዘርዘር አድርገን በእሚቀጥለው ምዕራፍ እንመለከተዋለን።
[4] አንድ ግለሰብ ቢያንስ ለአቅመ አዳም እስኪ ደርስ የቤተሰቡ ነው ሊባል ቢችልም ፤ ቤተሰቦቹ ራሳቸው በተመሳሳይ መንገድ የመጡ በመሆናቸው ፤ ማለትም ቤተሰቦቹ ራሳቸው ፤ ከቤተሰቦቻቸው የወጡ በመሆናቸው ፤ ወጪ እና ገቢ ተሰልቶ ሲያበቃ ፤ አንድ ሰው ራሱ የራሱ የግል ንብረት ነው የእሚሆነው ፤ ፈጣሪ ወይንም ተፈጥሮ የኹላችንም ባለቤት ነው ከአልተባለ በስተቀር ። ፈጣሪ ወይንም ተፈጥሮ የሁላችንም ባለቤት ነው ቢባልም እንኳን ፤ ፈጣሪ ወይንም ተፈጥሮ ደግሞ በማሕበረ ኢኮኖሚው ረገድ የራሳችን ባለቤት እንድንሆን ነጻ ትቶናል።