ሕ ገ ክ ራ ሲ

marketing-image

በፖለቲካ ሳይንስ ምርምር ቀዳሚያዊ አንጋፋ እንደ ሆነ የእሚነገርለት አርስታትል ፤ የሰው ልጆች ስለ እሚያቋቁሙዋቸው የፖለቲካ ማሕበረሰባት ይኽን ይላል ፦

“እያንዳንዱ ብሔራዊ መንግሥት አንድ የሆነ ዓይነት ጋርዮሽ(ማሕበር) ነው ፤ የትኛውም ጋርዮሽ(ማሕበር) ደግሞ አንድ መልካም ነገርን ግብ የእሚያደርግ ነው ፤ ምክንያቱም ፦ የሰው ልጅ ግብር ፤ ል ግዜ መልካም ነው ብሎ ያሰበውን ነገር ማግኘትን ታሳቢ የአደረገ ስለ ሆነ ።”

 “Every state is a community of some kind, and every community is established with a view to some good; for mankind always act in order to obtain that which they think good. [1]“

መላው የሰው ልጅም በእዚኽ አርስታትል “አንድ መልካም የእሚለውን ግብ ለማሳካት” በአለው ሰብዓዊ በኃሪው እየተነዳ ፤ ከ5 ሺ ዓመታት በጥቂት በእሚበልጠው ፖለቲካዊ እድሜ ውስጥ ብሔራዊ መንግሥትን ወይንም ሐገርን ለመገንባት እና ለማሳደግ የተጓዘበትን ፖለቲካዊ ዝግመት ስንቃኝ ፤ ዋነኛ ነበሩ የእምንላቸው ኹለት ክስተቶችን እናገኛለን። እነርሱም ፦

  • ከሕዝብነት ወደ ብሔራዊ መንግሥትነት የተሸጋገረበት እና
  • ብሔራዊ መንግሥቱን ወደ ሕዝባዊ መንግሥት የአሸጋገረበት

ናቸው።

የሰው ልጅ ፤ በተበታተነ ኹኔታ ፤ ይኽ ነው የእሚባል የተማከለ መንግሥታዊ አስተዳደር ሳይኖረው ፤ በቤተሰብነት ፣ በመንደርነት ፣ በጎጥነት ፣ በነገድነት ከእሚኖርበት ኹኔታ ወጥቶ ፤ ሰፊ ቦታዎችን እና የተለያዩ ዓይነት ሕዝብን የአካተተ ፤ በአብዛኛው በንጉሣዊ አስተዳደር አማካኝነት የተጠናከረ ብሔራዊ መንግሥትን የፈጠረበት ክስተት ፤ በሰው ልጅ ፖለቲካዊ ዝግመት ውስጥ የመጀመሪያው ዋነኛ ክስተት ነው።

ከእዛም ይኽንን በሰፊ ቦታ የእሚኖር ሕዝብ በአንድነት የእሚመራው ፤ በአብዛኛው ንጉሣዊ የሆነውን መንግሥት ፤ በሰብዓዊ አስተሳሰብ ቃኝቶ ወደ ሕዝባዊ መንግሥት የለወጠበት ኺደት ወይንም ክስተት ደግሞ ኹለተኛው ወሳኝ ክስተት ነው።

እነ እዚኽን ኹለት ፖለቲካዊ ክስተቶች ፤ በተለይ ክርስቲያናዊ ስልጣኔ በኹኑት የዓለማችን ሕዝብ ዘንድ ፤ በአግባቡ በእሚስተዋሉበት ኹኔታ እንመለከታቸዋለን።

ሐገረ ፈረንሳይን እንደ ማሳያ ብንወስድ ፤ ፈረንሳይ በሻርሌመን (Charlemagne) በ8ኛው ምዕተ ዓመት አከባቢ እንደ አንድ በንጉሣዊ አስተዳደር ስር እንደ አለ ሐገር ተዋቅራ ከጨረሰች በኋላ ፤ በ19ኛው ምዕተ ዓመት ወይንም በግርድፉ ከ1 ሺ ዓመታት በኋላ ፤ በተካኼደ አብዮት ሕዝባዊ መንግሥት ለመመሥረት የጀመረችው ጉዞ ፤ መጀመሪያ ላይ ብዙ መሰናክል ቢያጋጥመውም ፤ በቀጣይነት በተደረገ የተሳካ ትግል ፤ ዛሬ በዓለማችን ኃያል ከእሚባሉ እና ሕዝባዊ መንግሥት ከመሠረቱ ሐገራት መካከል የእምትመደብ ሐገር ሆናለች ።

ሐገራችን ኢትዮጲያም ፤ ከፈረንሳይ በብዙ መቶ ከአልሆነም ወደ ሺ በእሚጠጋ ዓመት ቀደም ብላ ፤ በንጉሥ የእሚመራ የብሔራዊ መንግሥት የማቋቋም ኺደቷን በዘመነ አክሱም ብታጠናቅቅም ፤ ከአክሱም ውድቀት አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ ፤ ይኽንን ጠንካራ ብሔራዊ መንግሥቷን ሕዝባዊ መንግሥት ለማድረግ የእምታደርገው ትግል ፤ በመጥፎ ታሪካዊ ገጠመኞች እና ከግንዛቤ እጥረት በእሚመረጡ የተሳሳቱ የፖለቲካ አቅጣጫዎች ወይንም ፖሊሲዎች ምክንያት ፤ ብሔራዊ መንግሥታችንን ወደ ሕዝባዊ መንግሥት ለማሸጋገር የእምናደርገው ጥረት አመርቂ እና ሊቀለበስ የእማይችል የእሚባለው ደረጃ ላይ ያልደረሰ ሆኗል።

ይኽን በከፊል ብቻ ስኬታማ የሆነ ከ1,400 ዓመታት በላይ የቆየ የኢትዮጲያ ፖለቲካዊ ትግል ፤ በእዚኽ ኹኔታ ግማሽ ድል ብቻ ሆኖ እንዲቀር ያደረጉት ምክንያቶች ፦ ከአክሱም ውድቀት አንስቶ እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ እና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በይዘታቸው የተለያዩ ሆነው እናገኛቸዋለን። 

የመጀመሪያው ወይንም ከአክሱም ውድቀት አንስቶ እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ በነበረው ዘመን ውስጥ ፤ ብሔራዊ መንግሥታችንን ሕዝባዊ ለማድረግ የአካኼድነው ትግል አመርቂ የእሚባል ውጤት የራቀው ፤  በአብዛኛው ከኢትዮጲያን ቁጥጥር ውጭ የሆነ አስቸጋሪ ዓለም ዓቀፋዊ ፖለቲካዊ ኹኔታ የወለደው እና አባቶቻችን የሐገራችንን ሉዓላዊነት ከማስከበር ያለፈ ነገር ለማድረግ እንደ አይችሉ ከሰው ቁጥጥር ውጭ በሆኑ ኹኔታዎች የተገደዱበት ፤ ስለ እዚኽም ፦ በተለየ መጥፎ አጋጣሚነት ተፈርጆ ፤ አባቶቻችን ፥ በእዚኽ ፈታኝ ኹኔታ ውስጥ ሆነው ፤ በጥቁር አፍሪካም ብቻ ሳይሆን ፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃም ፤ ከብዙ የዓለማችን ሐገራት በተለየ ኹኔታ ፤ አስተዳደራዊ ነጻነቷን ወይንም ሉዓላዊነቷን ለብዙ ሺ ዓመታት አስከብራ መቆየት የቻለች ሐገር አቆይተውልን ከማለፍ ውጭ ይኽ ነው የእሚባል የተሻለ አማራጭ ነበራቸው የእማያስብል ነው።

በተነጻጻሪነት ፦ በኹለተኛው ማለትም በ20ኛው ክፍለ ዘመን ብሔራዊ መንግሥታችንን ሕዝባዊ ለማድረግ ያደረግነው ትግል ግን ፤ ምንም እንኳን ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ቀደም ከነበረው ኹኔታ በተቃራኒ ፤ በሐገር ውስጥ እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ፤ ኢትዮጲያ ራሷን ወደ ሕዝባዊ መንግሥት ባለቤት ሐገርነት  ለማሸጋገር ፤ የእሚያስችላት አመቺ ኹኔታ ቢኖርም ፤ የተለያየ ይዘት በአላቸው የተሳሳቱ ፖለቲካዊ ምርጫዎች ወይንም አስተሳሰቦች ምክንያት  ፤ ይኽንን ጥረታችንን የእሚፈለግበት ደረጃ ላይ ማድረስ ያልቻልንበት ሆኖ እናገኘዋለን።

ሕዝባዊ መንግሥት ምሥረታ ስንል ፤ የዜጎችን ተፈጥሮዋዊ ነጻነት አክብሮ ማስከበር ዋነኛ የመዋቀሪያው አንኳሩ የሆነ መንግሥት መመሥረት እያልን ነው።

በፖለቲካ ሳይንሱ ቋንቋ ደግሞ ፤ በነጻነት ዴሞክራሲ (Liberal Democracy) ርዕዮት አግባብ የተዋቀረ መንግሥት እያልን ነው።   

   የነጻነቱን ዴሞክራሲም ሐገርኛ ቃና በአለው ቃል ለማስቀመጥ በማሰብም ነው የመጽሐፉ ስያሜ የሆነውን ሕገክራሲ የእሚለውን ቃል ፤ ከአማርኛው ሕግ እና ከግሪኩ ክራሲያ ከእሚለው ቃል ጥምረት ፤ ለመቀመር የፈለግኹት ።

በእርግጥ የእዚኽ አዲስ ቃል አፈጣጠር ያልተለመደ እና አዲስ አይደለም ፤ ክራሲያ የእሚለውን የግሪክ ቃል የእሚጠቀሙ ብዙ ፖለቲካዊ ቃላት አሉ ፦

  • ዴሞክራሲ (Democracy) = ዴሞ + ክራሲ ፣
  • ቢሮክራሲ (Bureaucracy) = ቢሮ + ክራሲ ፣
  • ቲዖክራሲ (Theocracy) = ቲዖ +ክራሲ ፣
  • ክሌፕቶክራሲ (Kleptocracy) = ክሌፕቶ + ክራሲ ፣ ወዘተ።

ክርሲያ የእሚለው የግሪክ ቃል አገዛዝ (rule or dominion) የእሚል ትርጉም የአለው በመሆኑ ፤ ዴሞክራሲ (Democracy) ማለት የሕዝብ አገዛዝ ፣ ቢሮክራሲ (Bureaucracy)  ማለት የቢሮ አገዛዝ ወይንም የስልጣን ተዋረድ እና የሥራ ኺደት አገዛዛ ፣ ቲዖክራስ (Theocracy) አምላካዊ አገዛዝ ፣ ክሌፕቶክራሲ (Kleptocracy) የሌቦች መንግሥት ወይንም የሌቦች አገዛዝ ፣ ወዘተ ፤ ማለት ናቸው።

ከእዚኽ በተመሳሳይም ፤ ሕገክራሲ ማለት ፤ የሕግ አገዛዝ ወይንም የሕግ የበላይነት ማለት ነው።

የነጻነቱ ዴሞክራሲም የሕዝብ ወይንም የብዝኃኑ አገዛዝ ከመሆኑ በፊት የሕግ አገዛዝ ወይንም የሕግ የበላይነት የሰፈነበት አገዛዝ ነው።

የነጻነቱ ዴሞክራሲ የሕዝብ አገዛዝ ከመሆኑ በፊት የሕግ አገዛዝ ነው ሲባል ፤ በዘመናዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ውስጥ ሕግ ቁልፍ ቃል መሆኑን ያመለክተናል ። ሆኖም በዘመናዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰብ ውስጥ የሕግ የበላይነት ዋነኛ የስረዓት አንኳር ነው ስንል ፤ የተለመዱትን የፍታብሔር ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ፣ የንግድ ፣ ወዘተ ፤ ሕግጋት እየ አልን ሰአይሆን ፤ የእነ እዚኽ ኹሉ ዘመናዊ ሕግጋት እና የዘመናዊ ዴሞክራሲ መሠረት የሆነው እና በፖለቲካ ሳይንቲስቶች የተፈጥሮ ሕግ የእሚባለው ሕግ ነው።

ይኽን የተፈጥሮ ሕግ ጽንሰ ኃሳብ ለማስረዳት ፤ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች ፦

  • የተፈጥሮ ነጻነት እና
  • የተፈጥሮ ኹኔታ (የጦርነት ኹኔታ)

ከእሚሉዋቸው ጽንሰ አሳቦች ጋር ተዋዶ መቅረብ አለበት ።

የሰው ልጅ በተፈጥሮ ነጻ ሆኖ ተፈጥሯል ፤ ይኽም ማለት ይበጀኛል የእሚለውን ነገር ለማግኘት የአዕምሮ እና አካላዊ ብቃቱ የእሚፈቅድለትን ለማድረግ ተፈጥሮዋዊ ነጻነት አለው ፤ ይኽ ተፈጥሮዋዊ ነጻነት ግን ለተወሰኑ ግለሰቦች ተመርጦ የተሰጠ ሰአይሆን ፤ ኹሉም ሰዎች ፥ ሰዎች በመሆናቸው ብቻ በጋራ የእሚጋሩት ወይንም ኹሉም ሰዎች ጋር በእኩለነት ያለ ነጻነት ነው ። ይኽም በመሆኑ ፦ ይኽ የነጻነት እኩልነት በአንድ ዓይነት ሕግ ከአልተገራ እኩል ነጻ የሆኑ እና የእየራሳቸው አቅም የአላቸው ሰዎችን ፤ ኹሉም የራሳቸውን ፍላጎት በእሚሹበት ወቅት ወደ ግጭት እንዲያመሩ የእሚያደርጋቸው ነው።

ሰዎች በአንድ ዓይነት ሕግ ሰአይገሩ ፤ በእኩል ተፈጥሮ ነጻነታቸው ምክንያት ፤ እየ አንዳንዳቸው የራሳቸውን የግል ፍላጎት ብቻ በእሚሹበት ወቅት ፤ አንዳቸው በአንዳቸው ላይ የእሚፈጥሩት ፤ የሕይወት እና የንብረት ስጋት በፖለቲካ ሳይንቲስቶች የተፈጥሮ ኹኔታ ወይንም የጦርነት ኹኔታ ይባላል።

የተፈጥሮ ሕግም ፤ ሰዎችን ከእዚኽ የተፈጥሮ እኩል ነጻነታቸው ከአስገባቸው የተፈጥሮ ኹኔታ ውስጥ የእሚያወጣቸው ሕግ ነው። ሕገክራሲ በእሚለው ቃል ውስጥም ፤ ሕግ የእሚለው ቃል ፤ ይኽንን ሰዎችን ከተፈጥሮ ኹኔታ ውስጥ የእሚያወጣቸውን ሕግ የእሚወክል ነው።

ዴሞክራሲ ያለ እዚኽ የተፈጥሮ ሕግ ገሪነት ከሌሎች አምባገነናዊ ስረዓቶች ኹሉ የከፋ የመንጋ ስረዓት መሆን የእሚችል የፖለቲካ ስረዓት ነው።

እንደ እሚታወቀው ዴሞክራሲ ፤ የሕዝብ አገዛዝ በመሆኑ ፤ ሰዎች ልዩነት በእሚኖራቸው ጉዳይ ላይ ፤ በድምጽ ብልጫ በአብዛኛው ሕዝብ የተደገፈው ኃሳብ እንዲገዛ ከማድረግ የተሻለ የእሚታወቅ ሰላማዊ አማራጭ ስለ ሌለ ፤ አብዛኛው ሕዝብ በድምጽ ብልጫ የእሚፈልገውን ኃሳብ የእሚያነግስበት አሰራር ነው ። በአጭሩ ዴሞክራሲ ከዘማናዊ ማሻሻያዎቹ ውጭ የብዙኃን መንግሥት ወይንም አገዛዝ ማለት ነው።

የብዙኃን አገዛዝ ሰፍኗል ማለት ግን የሕግ የበላይነት ወይንም ፍትሕ ሰፍኗል ማለት አይደለም። ምክንያቱም ፦ በተለያየ ምክንያት የብዙኃንን ድጋፍ የአገኘው ኃሳብ ፤ ሕገ ወጥ የሆነ ኃሳብ ሊሆን ይችላል ወይንም ዴሞክራሲ ወይንም የሕዝብ አገዛዝ የመንጋ አገዛዝ ሊሆን ይችላል።

ስለ እዚኽ ፦ ተወዳጁ ዴሞክራሲ ፤ የመንጋ አገዛዝ ወይንም ብዙኃን አናሳዎችን የእሚጨቁኑበት እና ከሌሎች መጥፎ ስረዓቶች ኹሉ የከፋ ስረዓት ከመሆን የእሚታደገው ፤ ዴሞክራሲ የሕዝብ አገዛዝ ከመሆኑ በፊት ፤ ዴሞክራሲ የሕግ የበላይነት የሆነ እንደ ሆነ ነው።

ይኽም በመሆኑ ፤ በዘመናዊ አውዱ ፤ ለተፈጥሮ ሕግ የተገዛው የሕዝብ ወይንም የብዙኃን አገዛዝ ነው ዴሞክራሲ። ይኽንን ለተፈጥሮ ሕግ የተገዛውን ዴሞክራሲ ወይንም የሕዝብ አገዛዝ ነው የፖለቲካው ሳይንስ የነጻነት ዴሞክራሲ የእሚለው ወይንም በእኔ ስያሜ ሕገክራሲ ።

ሕገክራሲም ፦ የኢትዮጲያ ሕዝብ ፤ ሕዝባዊ መንግሥት የመመሥረት ትግል ፤ በአመርቂ ኹኔታ እስከ እሚሳካ ድረስ የእማይቆም ትግል በመሆኑ ፤ የኢትዮጲያ ሕዝብ ፤ በታሪኩ ሕዝባዊ መንግሥት ለመመሥረት የአደረገውን ረዥም እና ጽኑ ትግል በማስቃኘት ፣ የሕዝባዊ መንግሥትን አይቀሬነት በማስገንዘብ ፤ በእዚኽ ታሪካዊ ትግል እንደ ሕዝብ የአጋጠሙን ፈተናዎች ፣ ስኬቶች እና ስሕተቶች በመቃኘት እና ይኽን የረዥም ዘመን የኢትዮጲያዊያን ትግል ለማሳካት ፤ ቀዳሚ እና መተኪያ የሌለው በተፈጥሮ ሕግ አግባብ የተቃኘው የማሕበረሰብ እና የፖለቲካ ስልጣን አወቃቀር ድንጋጌ ወይንም ሕገመንግሥት ምን እንደ እሚመስል የእሚያስቀምጥ መጽሐፍ ነው።